ዓለም በወረርሽኝ በተጨነቀበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋን ቀጥላለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ "ግዙፍ" የተባለ ሮኬት ማስወንጨፊያ መሞከሯን ተከትሎ ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተጨነቀችበት ጊዜ የጦር መሳሪያ ሙከራ ማድረግ "ተገቢ አይደለም" ስትል ደቡብ ኮሪያ አወገዘች።
ትናንት እሁድ ደቡብ ኮሪያ እንዳለችው ሰሜን ኮሪያ ሁለት የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች፤ ይህም በዚህ ወር ውስጥ እያደረገቻቸው ካሉት ሙከራዎች አንዱ ነው ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ የኮሮናቫይረስ የዓለም ጭንቀት በሆነበት ወራት ውስጥ የሚሳኤል ሙከራዋን የቀጠለች ሲሆን ወረርሽኙ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ አላደረጋትም ተብሏል።
እስካሁን ድረስ ሰሜን ኮሪያ ምንም አይነት የኮሮናቫይረስ ክስተት ሪፖርት ያላደረገች ቢሆንም፤ ባለሙያዎች ግን ጥርጣሬያቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
የሰሜን ኮሪያ የአጭር ርቀት ተወንጫፊ የሚሳኤል ሙከራ ተደረገው ከአገሪቱ ምሥራቃዊ ከተማ ዎንሳን ሲሆን፤ አረሮቹ ባሕር ላይ ከመውደቃቸው በፊት በ50 ኪሎ ሜትር ከፍታ 410 ኪሎ ሜትሮችን መጓዛቸውን የደቡብ ኮሪያ ጦር ሠራዊት ገልጿል።
ዛሬ የሰሜን ኮሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ተቋም አገሪቱ "ግዙፍ" ያለውን ሚሳኤሎች በማስወንጨፍ የተሳካ ሙከራ ማድረጓን ዘግቧል።
ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ሙከራውን ከማሳወቁ በፊት ደቡብ ኮሪያ ድርጊቱን ጠንከር ባሉ ቃላት አውግዛው ነበር።
"ዓለም በኮቪድ-19 ወረርሸኝ ምክንያት ከባድ ችግር ውስጥ በገባበት ሁኔታ ውስጥ የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ድርጊት በጣሙን ተገቢ ያልሆነና በአስቸኳይ መቆም ያለበት ነው" ሲል የደቡብ ኮሪያ ጦር ኃይል አውግዞታል።
አሁን ሰሜን ኮሪያ ያደረገችው ሚሳኤል የማስወንጨፍ ሙከራ በዚህ ወር ብቻ በአራት ዙሮች ውስጥ ከተተኮሱት ስምንተኛውና ዘጠነኛው መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህም እስካሁን በሰሜን ኮሪያ በአንድ ወር ውስጥ ከተተኮሱት ሚሳኤሎች ከፍተኛው የተመዘገበበት መሆኑን ተንታኞች ተናግረዋል።












