የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚሞከርባቸው ፈቃደኞች እየተፈለጉ ነው

ምርምር

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ከተሰጣቸው በኋላ ለቫይረሱ በመጋለጥ በሽታው መልሶ ይይዛቸው እንደሆነ ለማወቅ በሚደረገው ሙከራ ውስጥ የሚሳተፉ ፈቃደኛ ግለሰቦች እየተፈለጉ ነው።

በሙከራው ውስጥ ለሚሳተፉ በጎ ፈቃደኞች ጥሪውን ካስተላለፉ ባለሙያዎች መካከል የኖቤል ሽልማትን ያገኙ ባለሙያዎች ይገኙበታል ተብሏል።

ባለሙያዎቹ ለአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ምርምር ተቋም በጻፉት ደብዳቤ ላይ "ይህ ሙከራ ለወረርሽኙ ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ያፋጥነዋል" ሲሉ ገልጸዋል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ-19 ክትባት ፕሮግራም ዳይሬክተር እንዳሉት እንዲህ ያለው ምርምር "አዋጪና ጠቃሚ መረጃን የሚያስገኝ" መሆን አለበት።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 23 የኮሮናቫይረስ ክትባቶች በክሊኒካል ሙከራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

እነዚህ ክትባቶች መስራታቸውን ለማወቅ የሚቻለው በቂ ቁጥር ላላቻው ፈቃደኞች ክትባቱ ተሰጥቶ መደበኛ ህይወታቸውን እያካሄዱ ለበሽታው ተጋላጭ እንዲሆኑ በማድረግ ቫይረሱን መቋቋም ከቻሉ ብቻ ነው።

አብዛኞቹ የክትባት ምርምሮች እየተከናወኑ ያሉት በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ባለባቸው አገራት ውስጥ በመሆኑ ይህም ሙከራ እስከሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ተገምቷል።

ይህ የክትባት ሙከራ በ140 አገራት ውስጥ የሚገኙ ከ30 ሺህ በላይ ፈቃደኞች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።

የዚህን የክትባት ሙከራ ዘመቻን 15 የኖቤል ሽልማትን ያገኙ ሰዎች ያሉበት ከ100 በላይ ታወቂ ሰዎች ደግፈውት ፊርማቸውን አኑረዋል።

በዚህ ሙከራም የሚሳተፉት ወጣትና ጤናማ በጎ ፈቃደኞች ሲሆኑ የወረርሽኙ መከላከያ ክትባት ከተሰጣቸው በኋላም ሆን ተብሎ ለኮሮናቫይረስ እንዲጋለጡ ይደረጋል ተብሏል።

በፈቃደኛ ግለሰቦቹ ላይ በሚደረገው በዚህ የክትባት ሙከራ በጤናቸው ላይ የሚከሰተው ጉዳት ዝቅተኛ ሲሆን ለማኅበረሰቡ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ ተገልጿል።