ኮሮናቫይረስ ፡ እሽቅድድም ለኮቪድ-19 ክትባት፡ የማይደርሳቸው አገሮች ይኖራሉ?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዓለም ዙሪያ ከ57 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
ይህንን ወረርሽኝ ለማስቆም መላው ዓለም እየተጠባበቀ ያለው ብቸኛ ተስፋው ክትባት ነው። ነገር ግን ድሃ አገሮች ክትባቱ ላይደርሳቸው ይችላል የሚል ስጋት ተስተጋብቷል።
አሁን ላይ ሁለት ክትባቶች ውጤታማነታቸው ሲረጋገጥ፤ ሌሎች በርካታ ክትባቶች ደግሞ የመጨረሻ የሙከራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ክትባቶቹ እስካሁን ፍቃድ ባያገኙም አንዳንድ አገሮች ከወዲሁ እያዘዙ ነው።
የአሜሪካው ዱክ ዩኒቨርስቲ በሠራው ጥናት መሠረት፤ እስካሁን ወደ ለ6.4 ቢሊዮን የክትባት ጠብታዎች ግዢ ተፈጽሟል።
በተጨማሪም በድርድር ላይ ያሉ ወይም በተጠባባቂነት የተያዙ 3.2 ቢሊዮን ጠብታዎች አሉ።
ቀድመው ክትባቱን ያዘዙ አገሮች
በመድኃኒት ሽያጭ ዓለም ውስጥ መድኃኒቶችንና የክትባት ጠብታዎችን ቀድሞ ለመግዛት መስማማት የተለመደ ነው። በለንደን የምጣኔ ሀብት መምህርት ክሌር ዊንሀም እንደሚሉት ይህ ለግዢ ቀድሞ መዋዋል አምራቾቹን ያበረታታል ተብሎ ይታመናል።
በሌላ በኩል ቀድሞ የከፈለ ቅድሚያ አገልግሎት ያገኛል ማለት ነው።
የዱክ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ቀድመው ክትባት ለመግዛት የተስማሙት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ናቸው።
ማምረት የሚችሉ ጥቂት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች በከፍተኛ መጠን ክትባቱን ለማግኘት መደራደር ችለዋል።
የክትባት ሙከራ ማስተናገድ የሚችሉ እንደ ብራዚል እና ሜክሲኮ ያሉ አገሮች መስተንግዷቸውን ክትባት ለማግኘት ይጠቀሙበታል።
የሕንዱ ሰረም ተቋም አገር ውስጥ ከሚያመርተው ክትባት ግማሹን እዚያው ሕንድ ውስጥ እንደሚያስቀር ተናግሯል።
ኢንዶኔዥያ ከቻይና ጋር ብራዚል ደግሞ ከኦክስፎርዱ መድኃኒት አምራች አስትራዜንካ ጋር ተጣምረዋል።
ሕንድ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት የተለያየ የክትባት አማራጭ ያስቀመጡ አገሮች ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ "መሪዎች ዜጎቻቸውን እንደሚያስቀድሙ ጥያቄ የለውም። ነገር ግን ወረርሽኙን ለመግታት ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል"።
ውስን ክትባትን ለዓለም ሕዝብ ማከፋፈል
የዱክን ጥናት የመሩት አንድርያ ቴይለር እንደሚሉት፤ ቀድመው ክትባቱን የሚገዙ አገሮች መኖራቸው እና የክትባት መጠን ውስን መሆኑ ድሃ አገሮች ክትባቱን እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆናል።
ምን ያህል ክትባት፣ መቼ ገበያ ላይ እንደሚውል ገና አልታወቀም። ስርጭትን በተመለከ የሚነሱ ጥያቄዎችም ገና መልስ አላገኙም።
ቻንድራካት ላህርያ እንደሚሉት፤ አቅመ ደካማ አገሮች ክትባት የማግኘት እድላቸው የሚወሰነው ምን ያህል ክትባት በምን ያህል ፍጥነት ይሠራል በሚለው ነው።
"ሕንድ ውስጥ ባለው የማምረት አቅም ዋጋው እንደሚቀንስና ተደራሽነቱ እንደሚሰፋ እገምታለሁ። ስለዚህም ክትባቱን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ያገኛሉ" ይላሉ።
ተስፋ ሰጪዎቹ ክትባቶችን ለመግዛት እየተስማሙ ያሉት ሀብታም አገሮች ናቸው የሚሉት ፖሊሲ ተንታኟ ፌቸል ሲልቨርማን ናቸው።
"ብዙ ውጤታማ ክትባቶች ካሉ ሀብታም አገሮች ብዙ አማራጭ ስለሚኖራቸው ክትባቶች ይተርፋሉ ማለት ነው" ይላሉ።
ሆኖም ግን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገሮች በቀጣዩ ዓመት መገባደጃ ላይ ክትባቱ በስፋት የመድረሱ እድሉ ውስን ነው።
ፋይዘር በ2020 እስከ 50 ሚሊዮን ክትባት፤ እስከ 2021 ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ክትባት እንደሚያመርት አስታውቋል።
ይህ በመላው ዓለም ይዳረሳል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
ምናልባትም እንደ ሞደርና ያሉ ተቋሞችም ተስፋ ሰጪ ክትባት ማግኘታቸው ተደራሽነቱን ያሰፋው ይሆናል ብለው ይጠብቃሉ።
አዲስ የክትባትስርጭት እቅድ
የዓለም የጤና ሥርዓት እኩል ደረጃ ላይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው።
እአአ 2009 ላይ ለተከሰተው ወረርሽኝ ክትባት ሲገኝ በዋነኛነት የገዙት ሀብታም አገሮች ነበሩ።
90 በመቶው የዓለም መድኃኒት አምራቾች 10 በመቶውን ሕዝብ እንደሚያገለግሉ ባለሙያዋ ይናገራሉ።
ኮቫክስ የክትባቶችን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በጋቪ ክትባት አቅራቢና የዓለም ጤና ድርጅት የተመሠረተ ጥምረት ነው።
ጥምረቱ ለአባል አገሮቹ 20 በመቶ ዜጎች ክትባት የማዳረስ አቅድ አለው።
ሀብታም አገሮች ክትባት ሲገዙ ለድሃ አገሮች የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግበት እቅድም አለ።
2 ቢሊዮን ዶላር አሰባስበው ለ92 አገሮች ክትባት ገዝተው ያከፋፍላሉ።
ኮቫክስ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ጠብታዎች አስቀድሞ አዟል። ይህም ለአባል አገራት ይከፋፈላል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ክትባት የሚሠራው አስትራዜንካ የዚህ ጥምረት አንድ አካል ነው።
ኃላፊው ፓስካል ሶሪት በሁሉም አገር ያሉ ዜጎች ክትባቱ እንዲደርሳቸው ለማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ፋይዘር እስካሁን በኮቫክስ ስምምነት ውስጥ አልገባም። ሆኖም ውይይት እየተደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።
መድኃኒት አምራቹ ክትባቱን ለሁሉም ለማከፋፈል እንደሚፈልግም ገልጿል።
በሌላ በኩል የኮቫክስ ስምምነት ውስጥ ካሉ አገሮች መካከል እንደ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ያሉት በቀጥታ ከመድኃኒት አምራቾች ጋር እየተደራደሩ መሆኑ መሰማቱ ስጋት ፈጥሯል።
የዱክ ተመራማሪው እንደሚሉት፤ አገሮቹ ለኮቫክስ ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ ቢያደርጉም ጎን ለጎን ክትባቱን ቀድመው ለመግዛትም እየሞከሩ ነው።
እምነስቲ፣ ኦክስፋም እና ሌሎችም ተቋሞችም ክትባቱ ለመላው ዓለም ተደራሽ እንዲሆን ከወዲሁ እያሳሰቡ ነው።
መድኃኒት አምራቾች በዓለም ጤና ድርጅት አማካይነት መረጃ እንዲለዋወጡም ጠይቀዋል።
የኦክስፋም የጤና ፖሊሲ አማካሪ አና ማርዮት "የትኛውም ድርጅት ብቻውን በቂ ክትባት ማምረት አይችልም። አቅርቦቱ ካልሰፋ ሀብታምና ድሃ አገሮች ፉክክር ውስጥ ይገባሉ። ሁሌ የሚያሸንፉት ሀብታም አገሮች ናቸው" ይላሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ማሸነፍ የሚቻለው ሁሉም አገሮች ክትባቱን ማግኘት ከቻሉ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።
"በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭ ቫይረስ ነው። በተሳሰረች ዓለም ውስጥ ሁሉም አገር ከወረርሽኙ ነጻ ካልሆነ በስተቀር የትኛውም አገር ብቻውን ነጻ አይሆንም" ሲልም አሳስቧል።
















