ኮሮናቫይረስ፡ የኦክስፎርድ ክትባት የአረጋውያንን የበሽታ መከላከያ 'ያነቃቃል' ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Oxford University
የኦክስፎርድ ኮሮናቫይረስ ክትባት በ60 ዎቹ እና በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም ጠንካራ በሆነ መልክ ማነቃቃቱ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑና በዕድሜ የገፉ ሰዎቸን ሊጠብቅ ይችላል የሚል ተስፋን ፈንጥቋል።
እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ 560 ጤናማ በጎ ፈቃደኞችን መሠረት ያደረጉት የምዕራፍ ሁለት ግኝቶች "አበረታች" ናቸው።
በምዕራፍ ሦስት ደግሞ ክትባቱ ኮቪድ -19 የያዛቸው ሰዎችን ይከላከል እንደሆነ ይጥናል፡፡
የዚህ ምዕራፍ ወሳኝ ውጤቶች በሚቀጥሉት ሳምንታት ይጠበቃሉ፡፡
ፋይዘር-ባዮኤንቴክ፣ ስፑትኒክ እና ሞደርና የተሰኑ ሦስት ክትባቶች በሦስተኛ ምዕራፍ ሙከራዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገባቸውን ሪፖርት አድርገዋል።
አንዱ ክትባት ደግሞ ከ65 ዓመት በላይ ከሆኑ ሰዎች መካከል 94 በመቶ የሚሆኑት ከኮቪድ -19 ሊጠበቁ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡
የኦክስፎርድ ሪፖርት የክትባቱን ደህንነት እና የሰውነት ምላሽን በሚፈትሽበት ቀዳሚ ምዕራፍ የተገኘ ነው። ለማከማቸት ማቀዝቀዣ ስለማይፈልግ ክትባቱ በረዥም ጊዜ በቀላሉ ሊዳረስ ይችላል ተብሏል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አንድሪው ፖላርድ ለቢቢሲ ከ70 ዓመት በላይ ለሆኑት ጠንካራ የመከላከል አቅም መፍጠሩ "ፍፁም ደስ ብሎኛል" ብለዋል፡፡
ክትባቱ ሰዎችን ከኮቪድ -19 መከላከሉን በተመለከተ አለመታወቁን ገልጸው፤ ቀጣይ ሪፖርት "ከገና በፊት" ይለቀቃል ብለዋል፡፡
ከሌሎች ክትባቶች ጋር "ፉክክር የለም" ያሉት ፕሮፌሰር ፖላርድ፤ በርካታ ክትባቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ይፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ለመጠበቅ ሁሉንም እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ክትባት የማዘጋጀት ተግዳሮት የሚሆነው በየትኛውም ዕድሜ ላይ ያለ ሰው የሰውነቱን በሽታ የመከላከል አቅም አዳብሮ ቫይረሱን እንዲዋጋ ማነቃቃቱ ነው፡፡
በዕድሜ የገፉ ሰዎች ደካማ የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት ስላላቸው ክትባቶች በወጣቶች ያላቸውን ውጤማነት ያህል አይደሉም ማለት ነው፡፡
የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ሙከራዎች ተመሳሳይ ችግር ላይገጥማቸው ይችላል ማለት ነው፡፡
ዕድሜያቸው ከ56-69 እና ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ከ18-55 ዕድሜ ካላቸው አዋቂዎች ጋር ተመሳሳይ የመከላከል አቅም እንዳላቸው መረጃዎቹ አሳይተዋል፡፡
"ቀጣዩ እርምጃ [ክትባቱ] ከበሽታው እንደሚከላከል ማየት ነው" ሲሉ በኦክስፎርድ የክትባት ቡድን መርማሪ የሆኑት ዶ/ር ማሄሺ ራማሳሚ ገልጸዋል፡፡
በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ቀለል ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን የማያሳዩ ሲሆን ካሳዩም ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡
ChAdOx1 nCov-2019 የተባለው ክትባት ከባድ የደኅንነት ስጋቶች የሉትም ተብሏል፡፡
የኦክስፎርድ ክትባት ቫይረሱ ተዳክሞ በሰው ልጆች ውስጥ ማደግ እንዳይችል ሆኖ የተሠራ ነው።
ክትባቱ ጥር ተጀምሮ ከሦስት ወር በታች በሆነ ጊዜ የተሠራ ሲሆን፤ ሰዎች ላይ ሙከራዎችን በማድረግ በአውሮፓ የመጀመሪያው ነው፡፡
ሰዎችን ከኮቪድ -19 የመከላከል አቅሙ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ የሚመለከተው የክትባቱ ሦስተኛ ዙር ሙከራ ነሐሴ መጨረሻ ላይ ተጀምሯል፡፡















