ኮሮናቫይረስ፡በአሜሪካ በኮቪድ የሞቱ ዜጎች ቁጥር ሩብ ሚሊዮን አለፈ

ህመምተኛ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሐዝ እንደሚያሳየው አሜሪካ በኮቪድ ያጣቻቸው ዜጎቿ ብዛት 250ሺ ደርሷል።

በኮቪድ የተያዙ ዜጎች ቁጥር ደግሞ 11 ሚሊዮን ተኩል አልፏል።

በዓለም ላይ በዚህ ቁጥር ተህዋሲው ጉዳት ያደረሰበት ከአሜሪካ ሌላ አንድም አገር የለም።

ባለፉት ሳምንታት ተህዋሲው በአዲስ መልክ አገርሽቶ መላው የአሜሪካ ግዛቶችን እያመሰ ይገኛል።

በቀን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በማሻቀቡ ባለፉት ቀናት ከ180ሺ ሰው በላይ በቀን በተህዋሲው የተያዘበት ዕለት ተመዝግቧል።

ባለፈው ረቡዕ ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡት የተዛማጅ በሽታዎች ሊቅ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ "አገሪቱ በአስቸጋሪ ወቅት በተሳሳተ መንገድ እየሄደች ነው" ሲሉ አሜሪካ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ገልጸው ነበር።

ይህ ወረርሽኝ የጀመረ ሰሞን የተህዋሲው ዋና መናኸሪያ የነበረችው ኒውዯርክ የተሳካ ሥራ በመስራት የተህዋሲውን ግስጋሴ መግታት ችላ ነበር። አሁን ችግሩ በማገርሸቱ ከሐሙስ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ውሳኔ ላይ ደርሳለች።

ዶ/ር ፋውቺ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰዎች ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን የተህዋሲውን መዛመት የሚገቱ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያመነታሉ፤ ይህ ደግሞ የተህዋሲውን መዛመት እጥፍ አድርጎታል።

ጭምብል ማጥለቅ፣ እጅን ደጋግሞ መታጠብ፣ ሰዎች በበዙባቸው ቦታዎች አለመገኘት፣ ርቀትን መጠበቅ የተህዋሲውን የወረርሽኝ ግስጋሴ ይገታዋል ይላሉ ፋውቺ። ሆኖም ዜጎች ይህን ለማድረግ ተሰላቹ፣ ተህዋሲው ግን ለመዛመት አልሰለቸውም።

ከወራት በፊት በመጋቢት ወር አሜሪካ 2ሺ200 ሰዎች በተህዋሲው ሞቱባት ጊዜ ከፍ ያለ ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር። ዶናልድ ትራምፕም ነገሩን ቢያጣጥሉትም አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ነበር።

በዚያ ወቅት ዶ/ር ፋውቺ በዚህ ተህዋሲ በአሜሪካ 200ሺ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ በሚል በመተንበያቸው ቀኝ አክራሪዎችና የትራምፕ ደጋፊዎች ሰውየውን ክፉኛ ሲተቿቸው ነበር። ይህ ሊሆን አይችሉም ያሉ በርካታዎች ነበሩ። አሁን ቁጥሩ እሳቸው ከገመቱት በ50ሺ ልቋል።

ክትባት ለመፍጠር የሚጣጣሩት ፊዘር እና ባይንቴክ ትናንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫ የፈጠሩት አዲስ ክትባት ዕድሜያቸው ከ65 እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች የፈውስ ምጣኔው 94 ከመቶ መሆኑን ለዓለም አብስረዋል።

ይህን ተከትሎም ሌላ የብስራት ዜና ከዚያ ከአሜሪካ ተሰምቷል። ሞደርና መድኃኒት አምራች የፈውስ ስኬት ምጣኔው 95 ከመቶ የሆነ ክትባት አግኝቻለሁ ብሏል።

የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከመግባቱ በፊት እነዚህ ክትባቶች ፍቃድ አግኝተው የአሜሪካንንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ ይታደጉት ይሆን?የሚለውን የብዙዎች ተስፋ ነው።