ሩዋንዳ ፡ በውጭ የሚኖሩ ሩዋንዳውያንን ለመቆጣጠር እየዋለ ያለው 'ቃለ መሃላ'

የፎቶው ባለመብት, -
በለንደን የሩዋንዳ ቆንስላ የ'ቃለ መሃላ' ሥነ ሥርዓት ሲፈጸም የሚያሳይ ቪድዮ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
የሩዋንዳ መንግሥት እንደ ሰሜን ኮርያ ሆኗል ብለው የኮነኑም ነበሩ።
ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ሩዋንዳውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ይህ 'ቃለ መሃላ' ሩዋንዳውያንን ለማሸበርና ለማፈን ያለመ ነው።
አንድ ግለሰብ እንደሚናገረው፤ ከመንግሥት ጋር እንዲተባበር ጫና ለማሳደር ሲባል ሩዋንዳ ያሉ ቤተሰቦቹ ታግተዋል። ተገድለውም ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራል።
መንግሥት ይህንን ክስ አጣጥሏል።
በዋትስአፕ ብዙዎች የተቀባበሉት ቪድዮ ላይ 30 ሰዎች ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሚገኘው የሩዋንዳ ኤምባሲ ይታያሉ።
እጃቸውን ከፍ አድርገው ከገዢው ፓርቲ ሩዋንዳን ፓትሪዮቲክ ፍሮንት (አርፒኤፍ) ጎን ለመቆም ቃል ይገባሉ።
"አርፒኤፍን ከከዳሁ መላው ሩዋንዳውያንን መክዳት ስለሆነ በስቅላት መቀጣት አለብኝ። የሩዋንዳን ጠላቶች ባሉበት ገብቼ ለመዋጋት ቃል እገባለሁ" ብለው ቃለ መሃላ ይገባሉ።
"በጣም ይፈራሉ"
ቃለ መሃላው እአአ 2017 ላይ እንደተካሄደ ይታመናል። አንዳንዶቹ ተሳታፊዎች የእውነትም የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ናቸው።
የተቀሩት ግን ሥነ ሥርዓቱን የታደሙት ጫና ተደርጎባቸው ነው።
አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰው "አብዛኞቹ ቃለ መሃላውን የሚፈጽሙ ሰዎች አያምኑበትም። ሩዋንዳ ያሉ ቤተሰቦቻችንን ደኅንነት ለመጠበቅ ስንል ነው የምንዋሸው" ብለዋል።
የፖል ካጋሜ ከፍተኛ አማካሪ የነበረው ዴቪድ ሂምባራ "ቃለ መሃላው ሁሉም ቦታ ይከናወናል። ያልፈጸመ ሰው እንደ ጠላት ይቆጠራል" ብሏል።
ካናዳዊው ምሁርና የመብት ተሟጋች በተደጋጋሚ ከሩዋንዳ መንግሥት ዛቻ ደርሶበታል።
እንግሊዛዊ-ሩዋንዳዊ የመብት ተሟጋች ረኔ ሙጋንዚ "ብዙዎቹ ቃለ መሃላውን ካልፈጸሙ ሩዋንዳ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ያምናሉ። ስለዚህ ይፈራሉ። ለዘብተኛ ሰው ቢሆንም እንኳን አርፒኤፍ ውስጥ እንዲሳተፍ ይጠበቃል። አለበለዚያ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል" ይላል።
የሩዋንዳ ቆንስላ ስለ ቃለ መሃላው ሲጠየቅ በኢሜል በሰጠው ምላሽ፤ ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ሩዋንዳውያን ለተለያዩ የባህል ክንውኖች እንደሚሰባሰቡ አስታውቋል።
ለፓርቲው ድጋፍ መጠየቅ ሕጋዊ እንደሆነና የሚሳተፉት ሰዎች በገዛ ፍቃዳቸው የሥነ ሥርዓቱ አካል እንደሚሆኑም ገልጿል።
"ወንድሞቼ ታግተዋል"
ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሠረት፤ የሩዋንዳ መንግሥት ከአገር ውጪ ሆነው ድጋፍ ያላሳዩ ሰዎችን የሚቀጣው ሩዋንዳ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ በማነጣጠር ነው።
አውስትራሊያ የሚኖረው ኖኤል ዚሀብውሜ "እኔን ለማስፈራራት ወንድሞቼን አግተዋቸዋል" ይላል።
የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ በመሸሽ ነበር ከአገሩ ወጥቶ ጥገኝነት የጠየቀው።
ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ ባለማሳየቱ አንድ ዲፕሎማት የግድያ ዛቻ ሲያደርጉበት ለአውስትራሊያ መንግሥት ጠቁሟል።
አምና ወንድሞቹ ከአውቶብስ ውስጥ በፖሊስ እንደታገቱና እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ይናገራል።
"ቤተሰብን ማስፈራራትና ማገት ማቆም አለባቸው። የሩዋንዳ መንግሥት የሰዎችን መብት ማክበር አለበት። እንደእኔ ውጪ አገር የሚኖሩ ዜጎችን ማስፈራራትም ተገቢ አይደለም" ይላል።
"ክሱ መሠረተ ቢስ ነው"
ለንደን ያለው ቆንስላ የኖኤል ዚሀብውሜን ክስ አይቀበልም።
"የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ ተራ የፖለቲካ ጨዋታ ነው" ይላል።
በሌላ በኩል አጥኚዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሩዋንዳ መንግሥት ላይ የሚሰነዘሩት ክሶች እውነት እንደሆኑ ያስረዳሉ።
አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት የሩዋንዳ መንግሥትን ቢተቹም በጎላ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ አልተቋረጠም።
አንዳንድ ከአገራቸው ውጪ የሚኖሩ ሩዋንዳውያን እንደተገደሉ ቢገለጽም፤ እምብዛም በአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ላይ ጫና ሲያሳድር አይታይም።
ሩዋንዳ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍም አላት። ሩዋንዳን የማበልጸግ፣ ድህነትን የመቅረፍ ትርክቱም ተቀባይነት አግኝቷል።
በሌላ በኩል 'ሆቴል ሩዋንዳ' የሚል ፊልም የተሠራለት እና በዘር ጭፍጨፋው ጊዜ ሰዎችን በመታደግ የሚታወቀው ግለሰብ ሩዋንዳ ውስጥ በሽብር መከሰሱ ብዙዎችን አነጋግሯል።
ኪዚቶ ሚሂጎ የተባለ ሙዚቀኛ በፖሊስ እጅ ሳለ መሞቱም ጥያቄ አጭሯል። መንግሥት ድምጻዊው ራሱን እንዳጠፋ ቢናገርም በርካቶች አልተዋጠላቸውም።
የአምንስቲ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን "ሩዋንዳዊ ከሆንክ ዝምታ ነው የሚያዋጣህ። ባለሥልጣኖች ዜጎችን ለማፈን ብዙ መንገዶች አሏቸው። ይህም ሕገ ወጥ እገታ፣ እንግልት፣ ቤተሰብ ማስፈራራት እና ከሌሎች አገሮች ወደ ሩዋንዳ እንድትመለስ ማስገደድን ይጨምራል" ትላለች።
ለንደን የሚገኘው ቆንስላ እነዚህ ውንጀላዎች በአጠቃላይ "መሠረተ ቢስ ናቸው። ወሬውን የሚነዙት ተቃዋሚዎች ናቸው። አላማቸው የአገሪቱን ገጽታ ማጠልሸትና እድገታችንን ማደናቀፍ ነው" ይላል።
ጭቆና
ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ምርጫ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ በ99% ድምጽ ምርጫውን ማሸነፋቸው ይፋ ተደርጓል።
ለንደን የሚኖረው ተቃዋሚ አብዱልከሪም አሊ "ለአርፒኤፍ ድጋፍ ያላሳየ ሰው እንደ ጠላት ይቆጠራል። ይሄ እንደ ሰሜን ኮርያ መሆን ነው" ይላል።
ካናዳ የሚኖረው ዴቪድ ሂምባራ፤ የሩዋንዳ መንግሥት "አምባገነን ነው። የሩዋንዳውያንን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ይሞከራል። ከአገር ውጪ ያሉትንም ጭምር ለመቆጣጠር ይፈልጋሉ" ሲል ይገልጻል።
በለንደን የሩዋንዳ ቆንስላ፤ "የሩዋንዳ መንግሥት ዋነኛ ግብ አገሪቱን ከድህንት ማውጣት ነው። ለሁሉም ጥሩ ሕይወት መፍጠር እንፈልጋለን። የሩዋንዳን እድገት ለማደናቀፍ ጥቂቶች ሐሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት ቢፈልጉም ትኩረት አንሰጣቸውም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።












