ዝነኛው ሩዋንዳዊ ዘማሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለ ሕይወቱ ማለፉ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኪቲቶ ሚሂጎ በመባል የሚጠራው ዝነኛው ዘማሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለ ሕይወቱ ማለፉ በሩዋንዳ ቁጣን ቀስቅሷል።
የሩዋንዳ መንግሥትን በመተቸት የሚታወቀው ኪቲቶ ከሦስት ቀናት በፊት ቡሩንዲ ድንበር አቅራቢያ በሩዋንዳ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውሎ እንደነበር ተነግሯል።
ፖሊስ ዘማሪው በቡሩንዲ የሚገኙ የሩዋንዳ መንገሥትን የሚወጉ አማጺ ቡድኖችን ለመቀላቀል ሊሄድ ሲል ነው በቁጥጥር ሥር ያዋልኩት ብሏል።
ኪቲቶ ከዚህ ቀደም ተመሥርቶበት በነበረው ክስ መሠረት አገር ጥሎ እንዳይወጣ ተበይኖበት ነበር።
ፖሊስ ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ ዘማሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ በነበረበት እስር ቤት የተለመደው ቁጥጥር ሲደረግ በእስር ክፍሉ ውስጥ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል ከማለት ውጭ በኪቲቶ አሟሟት ላይ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጥ ቀርቷል።
የሩዋንዳ መገናኛ ብዙኃን ኪቲቶ ሚሂጎ በሙስና እና በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማቋረጥ በሚል ክስ ተመሥርቶበት እንደነበር ዘግበው ነበር።
ከቀናት በፊት ከቲቶ ሚሂጎ በቁጥጥር ሥር ሲውል የተመለከቱ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዘማሪው ምንነቱ ባልታወቀ ነገር የተሞላ ቦርሳ ይዞ ወደ ቡሩንዲ ድንበር ሊሻጋር ሲል በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።
የዘማሪው አድናቂዎች የመሞቱን መንስዔ መንግሥት እንዲያስረዳ እየጠየቁ ይገኛሉ።
እአአ 2015 ዘማሪው ፕሬዝደንት ፕል ካጋሜን ለመግደል በማሴር እና በመንግሥት ላይ የጥላቻ ዘመቻ በመክፈት የ10 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት በፕሬዝደንቱ ምሕረት ተደርጎለት የነበረ ሲሆን፤ ከአገር መውጣት የሚችለው ከፍርድ ቤት ፍቃድ ሲያገኝ ብቻ ነበር።














