'የኢንተርሃምዌይ አባት' ፌሊሺየ ካቡጋ ተላልፎ ሊሰጥ ነው

ፈሊሴ ካቡጋ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፈሊሴ ካቡጋ

ከ26 ዓመታት አደን በኋላ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋለው ፌሊሺየ ካቡጋ ሄግ ለሚገኘው ዓለም አቀፉ ፍድር ቤት ተላልፎ ሊሰጥ ነው።

በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወቅት በእራሱ የሬዲዮ ጣቢያ ጥቃቱን ለማበረታታት በተጨማሪ መሳሪያ ያቀርብ እንደነበር የሚከሰሰው የ84 ዓመቱ ካቡጋ፤ ባለፈው ወር ነበር ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ ሰፈር ውስጥ ነበር በቁጥጥር ሥር የዋለው።

በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ እጅግ ተፈላጊው ሰው ፌሊሺየ ካቡጋ እንዴት ለ26 ዓመታት ሊደበቅ ቻለ የሚለው ዓለምን ሲያነጋግር ሰንብቷል።

ካቡጋ ፓሪስ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ምናልባት በኬንያ ናይሮቢና በማዳጋስካር የተወሰኑ ዓመታትን ተደብቆ እንደቆየ ጥርጣሬ አለ።

በጎርጎሳውያኑ 1994 የሁቱ ሚሊሻዎች የቱትሲ ዘርን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨፈጭፉና ከምድረ ገጽ እንዲያጠፉ የገንዘብ እርዳታ ሲያደርግ እንደነበር የሚጠረጠረው ካቡጋ በወቅቱ የሩዋንዳ ቁጥር አንድ ሚሊየነር ነበር።

በተለይም በሻይ ቅጠል ንግድ በአፍሪካ ቀዳሚው ሀብታም እንደነር ይነገራል።

ካቡጋ ለኢንተርሃምዌይ ሚሊሻ ቱትሲዎችን መጨፍጨፍያ እንዲሆን በሚል በርካታ ቆንጨራ ከውጭ አገር ጭምር እንዲገባ በማድረግ ከመጠርጠሩም ባሻገር የዘር ፍጅቱ እንዲያካሄድ ዜጎችን በማነሳሳት ትልቁን ሚና የተጫወተውን ሊብሬ ዴስ ሬዲዮ ኮሊንስ የተባለውን ራዲዮ ጣቢያ በባለቤትነት ይቆጣጠር ነበር ተብሎ ይከሰሳል።

በአጠቃላይ የሩዋንዳን ጭፍጨፋ "ስፖንሰር" ያደረገ ሰው ተብሎ ነው ካቡጋ የሚጠረጠረው።

በዚህ የፕሮፓጋንዳ ራዲዮ ከፍተኛ መነቃቃትና ብርታት ያገኙ የሁቲ ሚሊሻዎች የበመቶ ቀናት ውስጥ ብቻ 800 ሺህ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች ተገድለዋል።

የዘመኑ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ሃቢያሪማና አውሮፕላን ተመትቶ እርሳቸው መገደላቸውን ተከትሎ ነበር የዓለማችን እጅግ ሰቅጣጩ የዘር ፍጀት በሩዋንዳ የተከሰተው።

ካቡጋ በዚያን ጊዜ ከተገደሉት ፕሬዝዳንት ሃቢያሪማና ቤተሰብ ጋር በጋብቻ ተሳስሮ እንደነበረም ይታወቃል።

ለ26 ዓመታት ፖሊስ ሲያድነው የነበረው ካቡጋን ያለበትን ለጠቆመ አሜሪካ 5 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ ብላ ነበር።

ፊሊሲየ ካቡጋን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ተላልፈው እንዲሰጡ የወሰነው የፓሪስ ፍርድ ቤት ነው።

የካቡጋ ጠበቃ የደንበኛቸው ፍርድ ሂደት በዚያው በፓሪስ እንዲሆን ይፈልጋሉ።