እየተቀየረ ያለው በህወሓት ቁጥጥር ሥር የነበረው የትግራይ ፖለቲካ ምኅዳር

የትግራእ ሰማዕታት ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, SM

በኢትዮጵያ ሆነ በትግራይ ፖለቲካ ታሪክ በጉልህ የሚጠራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ህወሓት በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ አውራ ፓርቲ ሆኖ ከዘለቀ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ትግራይ ላይ ብቻ ተወስኖ ቀርቶ ነበር።

ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ የነበረው ህወሓት ግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የትግራይ የፖለቲካ ምኅዳር ከዓመታት ግጭት እና የህወሓት የበላይነት በኋላ ትልቅ ለውጥ እያሳየ ነው።

በክልሉ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ተዋናዮች እየተፈጠሩ የረዥም ጊዜ የበላይነት የነበረውን የህወሓት የፖለቲካ አስተሳሰብ እየተገዳደሩ እና ሕዝባዊ ውይይቶችን እና መስተጋብሮችን እየቀረጹ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን በህወሓት፣ በፌደራል መንግሥት እና በተቀናቃኝ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን መካከል በአስተዳደር፣ በፀጥታ እና በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ አለመግባባት ቀጥሏል።

የእነዚህ ትግሎች ውጤት የትግራይን የወደፊት ሚና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ ይቀርፃል።

አሁን በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ከ15 በላይ ፓርቲዎች ግን በህወሓት ተይዞ የነበረውን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ምኅዳር ለመሙላት እየተንቀሳቀሱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ ገና ምዝገባ ያላካሄዱ ደግሞ አራት ያህል መኖራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች ይናገራሉ።

ቢቢሲ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቁጥር እየበዛ የመጣበትን ምክንያት የጠየቃቸው የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርሀ፣ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ አስተዳድሮ እንደማያውቅ እና "ከአንድ አካባቢ" በተውጣጡ ሰዎች "ይጨቆን" ነበር ይላሉ።

አክለውም በተለይ ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በኋላ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች "ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ማነሳት ጀምረዋል። ይህ ደግሞ በየአካባቢው ፓርቲዎች እንዲወለዱ እያደረገ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

የውድብ ወለዶ ትግራይ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ትኩእ በበኩላቸው ከጦርነቱ በፊትም ሆነ በኋላ የሚቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን በማስታውስ በተለይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልሉን መምራት ከጀመረ ወዲህ "የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በትግራይ ብዙ አስተሳሰቦች" እንዲመጡ መንገድ ከፍቷል ይላሉ።

አቶ ሰለሞን በትግራይ የተለያየ አቋም የሚያራምዱ ኃይሎች እየመጡ መሆናቸውን እና ይህንንም ህወሓት እንዲሁም ሕዝቡም እየተረዳው መሆኑን ይጠቅሳሉ።

"ብዙ ፓርቲዎች የተለያዩ ፕሮግራሞችን እና የተለያዩ አስተሳሰቦችን ይዘው መጥተዋል። ይህ ደግሞ ለትግራይ ፖለቲካ አዲስ ምዕራፍ እና አዲስ የዲሞክራሲ ልምምድ መሆኑን እናምናለን።"

የስምረት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ከዚህ ቀደም "ትግራይ ውስጥ የተለየ አስተሳሰብ ይዞ መንቀሳቀስ ከማኅበራዊ መስተጋብርም መገለል ያደርስ ነበር" በማለት ህወሓት የክልሉ አውራ ፓርቲ በነበረበት ወቅት የተለያዩ አስተሳሰቦችን በድፍረት ማራመድ አስቸጋሪ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ላለፉት 50 ዓመታት በትግራይ ውስጥ "የተወጠረ ፖለቲካ" የነበረ መሆኑን በማስታወስ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ አልደረሰም ነበር ይላሉ።

አሁን ላለው ተጨባጭ ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ "ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን ለመወሰን፣ በራስ ኃይል መጨቆን እና ወደ ኋላ እንዲቀር መደረግ" የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰቦች እና አደረጃጀቶች እንዲፈጠሩ ማድረጋቸውን ያብራራሉ።

የትግራይን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ተክሊት ገብረ መስቀል በበኩላቸው ህወሓት ከሁለት ዓመቱ ጦርነት በፊትም በክልሉ ያለው ተቀባይነት እያጣ እንደነበር በመጥቀስ "ይህ ደግሞ ግን ከጦርነቱ በኋላ በስፋት ተስተውሏል" ሲሉ ይናገራሉ።

በዚህም የተነሳ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል እየተመሠረቱ ያሉት መመሥረታቸው "ህወሓት ቅብሉነቱን ስላጣ፤ አስተሳሰቡም በጣም ስለደረቀ፣ ከጊዜው ጋር ሊራመድ ስላልቻለ" ሊሆን እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ጠቅሰዋል።

ፓርቲዎች የሚመሠረቱበት ምክንያት በዋናነት ጭቆና ነው የሚሉት የባይቶናው ተወካይ አቶ ዮሴፍ "በአካባቢያችን እየተጨቆንን ነው፤ ከሌላ አካባቢ እየመጡ እየጨቆኑ እየገዙን ነው። እየረገጡን ነው። ወደኋላ እያስቀሩን ነው የሚል አስተሳሰብ ፓርቲዎች እንዲበዙ እያደረገ ነው" ባይ ናቸው።

በክልሉ የፓርቲዎች ቁጥር ለመብዛት ካለው ውስጣዊ ግፊት በተጨማሪ ውጪያዊ ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚናገሩት የፓርቲዎቹ አመራሮች "ልዩነቱ የርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ጭቆና እና የትግራይ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ነው" ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ ተክሊት "ህወሓት ሲሄድበት በነበረው መንገድ የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ እና ፍላጎት ሊመለስ አይችልም ያሉ፣ ኅልውናው ሊከበር አይችልም የሚሉ፣ የትግራዋይነት የማንነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው ብለው የሚያስቡ ኃይሎች" ሌላ አማራጮችን መሞከር አለብን በሚል ፓርቲዎችን ወደ መመሥረት መግባታቸውን ይናገራሉ።

ፈትለወርቅ፣ ደብረ ጽዮን እና አማኑኤል

የፎቶው ባለመብት, TPLF

የምስሉ መግለጫ, የህወሓት መሪዎች

በትግራይ የሚታዩት የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት የሕግ ባለሙያው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሦስት ምድቦች ከፍለው ማየትን ይመርጣሉ።

በትግራይ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ስም ቢመዘገቡ አስተሳሰባቸው ግን ከኢትዮጵያ ጋር መቀጠል፣ ነጻ አገር መሆን ወይንም በኮንፌዴሬሽን መኖር የሚሉ መሆናቸውን አቶ ዮሴፍ ያስረዳሉ።

አቶ ተክሊት ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ከኤርትራ ጋር አንድ መሆን አለብን ብለው የሚያስቡ መኖራቸውን ተናግረዋል።

አሁን በክልሉ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ከ15 የማያንሱ ፓርቲዎች በየትኛውም ስም ቢደራጁም እናሳካዋለን የሚሉት በክለሉ "የሥርዓት ለውጥ" ማምጣት የሚለው ዋነኛው ነው።

የባይቶናው አቶ ዮሴፍ "ከሥርዓታዊ ለውጥ በኋላ ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ ሲጠበቅለት እነዚህ ፓርቲዎች እየተሰበሰቡ እንደሚሄድ እና ምናልባት ከበዙ ወደ ሦስት ሊመጡ እንደሚችሉ ያምናሉ።

በትግራይ ፓርቲዎቹ አሁን እየተመሠረቱ ያሉት ርዕዮተ ዓለምን መሠረት አድርገው አይደለም የሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ". . . ልዩነቱ ምንድን ነው ሲባል አንደኛው የትግራይ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ያለ ልዩነት ነው። ይሄ ቋሚ ነው ብዬ ነው የማስበው" ይላሉ የባይቶናው ም/ሊቀመንበር።

"ትግራይ ራሷን የቻለች አገር መሆን አለባት ብለው የሚያምኑ ፓርቲዎች አሉ። የኢትዮጵያ አካል ሆና መቀጠል አለባት የሚሉ አሉ። ሦስተኛ አማራጭ ይመጣል ብዬ የማስበው ትግራይ በኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር መተሳሳር አለባት የሚል ኃይልም ሊኖር ይችላል" ሲሉ ያብራራሉ።

አቶ ተክሊት እነዚህ አስተሳሰቦች በህወሓት የበላይነት ተጨፍልቀው ተይዘው የነበሩ መሆናቸውን እና አሁን ያ ኃይል ሲዳከም እነዚህ ሃሳቦች መድረክ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

"ለዚህም በትግራይ የተፈጠረው የአስተሳሰብ ልዩነት፣ የህወሓት መዳከም እና የፖለቲካ አስተሳሰቡ ተፈትሾ ወድቋል ብለው ስላመኑ እና ከውጭ የሚመጣ ግፊት ነው" ብለው እንደሚሰስቡ ሦስት ምክንያቶችን አቶ ተክሊት አስቀምጠዋል።

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በምን መልክ ወደ አንድ ይመጣሉ የሚለውን "ራሳቸው ፓርቲዎቹ ይመልሱ" የሚሉት የስምረቱ አቶ ሃፍቱ፣ ወደ ሁለት እና ሦስት ትልልቅ ፓርቲ መሰባሰባቸው እንደማይቀር ያላቸውን እምነት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የውድብ ወለዶ ፓርቲ አባል አቶ ግዑሽ ግደይ

የፎቶው ባለመብት, sm

የምስሉ መግለጫ, ውድብ ወለዶ ፓርቲ በትግራይ በቅርቡ የፖለቲካ ምህዳሩን ከተቀላቀሉ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው

የፓርቲዎች የመብዛት ጥቅም እና ተግዳሮት

የስምረት ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አስተሳሰቦች መብዛት "ለትግራይ ጥሩ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በቅድሚያ "የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር የሚችል ከባቢ እየተፈጠረ ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይህም ሕዝቡ አማራጮችን መስማት እና መወሰን እንዲችል ያደርገዋል።

አሁን ከ15 በላይ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አስተሳሰቦች ላይ መወያየት እና መነጋገር ሲጀምሩ ወደ አንድ በመምጣት "ሁለት እና ሦስት ትልቅ ለትግራይም ለኢትዮጵያም የሚጠቅም አስተሳሰብ ወደ መሆን መምጣታቸው አይቀርም" ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ።

የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በክልሉ የፓርቲዎች ቁጥር እየበዛ የመጣው ክልሉን ለበርካታ ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረው አካል "በመሳሪያ ወይንም በሠራዊት ተጠቅሞ ማፈን በመጀመሩነው።"

አሁን ግን በሁሉም አካባቢ ሰዎች ፓርቲ እያደራጁ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ ፓርቲዎችን እየመሠረቱ ነው ይላሉ።

ይህ በክልሉ በአንድ ኃይል የተያዘውን ሥልጣን "ለመገርሰስ የራሱ ሚና ይኖረዋል" የሚሉት አቶ ዮሴፍ፣ በክልሉ "ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት በጣም ጠቃሚ ይሆናል" ብለዋል።

ፓርቲዎች መብዛታቸው ሕዝቡ ለመታገል የፈጠራቸው የተለያዩ መድረኮች ስለሆኑ ችግር አለመሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተውም ያስረዳሉ።

የውድብ ወለዶ ትግራይ ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው "በአንድ አካባቢ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ብዙ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የሚኖሩት ካለው የፀረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ እና አገዛዝ የተነሳ ነው" በማለት "ፓርቲ መብዛቱ ሳይሆን ችግሩ፣ አሁን ሕብረተሰቡ የሚያነሳውን ጥያቄ ይመልሳሉ ወይ የሚለው ነው።"

የፓርቲዎች መብዛት "አፈና የሞላበትን አገዛዝ ከሕበረተሰቡ ጋር በመሆን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሻገር ለማድርግ" እንደሚያግዙ ጨምረው አስረድተዋል።

ለአቶ ዮሴፍ የፓርቲዎቹ በቁጥር መብዛት ችግር የሚሆነው "የውጭ ኃይሎች የፓርቲዎቹን ብዛት ትግራይን፣ የሕዝቡን አንድነት ለመከፋፈል" ለመጠቀም የሚሞክሩ ከሆነ ነው።

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለጻ የውጪ ኃይሎች ያሏቸው አካላት በፓርቲዎቹ መብዛት በኩል ገብተው "ክፍፍሉን ለማስፋት ወይንም ችግር ለመፍጠር የመጠቀም ፍላጎት ይታያል" ሲሉ ስጋታቸውን አስቀመወጠዋል።

የስምረቱ አቶ ሃፍቱ ተግዳሮቱን ሲያስረዱም እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ከባቢን "አልተለማመድነውም፤ ስለዚህ ሕዝቡ ግራ ሊጋባ ይችላል" በማለት ነው።

ገና ዲሞክራሲውን በሚገባ ስላልተለማመድነው በፓርቲዎች መካከል "የጠላትነት" ስሜት ሊዳብር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ይናገራሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ ተክሊት በበኩላቸው ህወሓት እንደ ፓርቲ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውጭ ቢደረግም አሁንም ግን "ቀላል የሚባል ፓርቲ አይደለም" ይላሉ።

ህወሓት በአስተሳሰብ ከሕዝቡ ጋር የተያያዘ ነው የሚሉት አቶ ተክሊት፣ ይህም በአደረጃጀት ካሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንጻር ግዙፍ ነው ብለዋል።

"በትግራይ ታሪክ እና ሥነልቦና ውስጥ ያለው ስፍራ ጉልህ ነው" የሚሉት አቶ ተክሊት "አሁኑ የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛት ህወሓት የያዘውን ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር ሊያፍታታው ይችላል" የሚል ተስፋ አላቸው።

ሌላኛው በትግራይ ምሑራን ዘንድ የሚንሸራሸሩ ሃሳቦች በመኖራቸው "እነዚህ ሃሳቦች ይብዛም ይነስ የተለያዩ ደጋፊዎች እና አቀንቃኞች አሏቸው። ፓርቲዎቹ ሲበዙ እነዚህ አስተሳሰቦች ሊወከሉ ይችላሉ" ሲሉ የሚኖራቸውን በጎ አስተዋጽኦ ይዘረዝራሉ።

አቶ ተክሊት ግን የፓርቲ መብዛት "ለትግራይ ፖለቲካ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳት አለው" በማለት "የፓርቲዎች መብዛት አመሠራረታቸው ላይ አካባቢያዊነት እየታየበት መሆኑ አንዱ አደጋ ነው" ብለዋል።

ይህም "የትግራይን ጥያቄ አደጋ ውስጥ ሊጥለው ይችላል" በማለት ስጋታቸወን ገልጸዋል።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ክልሉ ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ያግዛል?

የባይቶና ምክትል ፕሬዚዳንት የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ያለው ፍላጎት እና ሃሳብ ግልጽ አይደለም ይላሉ።

የፌደራል መንግሥቱ "አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ተመችቶታል ብዬ ነው የማስበው። አሁን ህወሓት እኮ መሬት ላይ አልቆለታል" በማለት ሕዝቡን እያስተዳደሩ ያሉት "ኮር እና ከኮር በላይ የሚባሉ አዛዦች ተሰብስበው በመሳሪያ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።

ህወሓት "የሕዝብ ድጋፍ የለውም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍም የለውም። ሕጋዊነት የለውም" የሚሉት አቶ ዮሴፍ "የፌደራል መንግሥት እየመላለሰ ሥልጣን ይሰጠዋል" ሲሉ ይህም ግራ እንደሚያጋባቸው ይናገራሉ።

ትግራይ ላይ ህወሓት ምን ነገር መፍጠር የሚችልበት አቅም የለውም። የሚሉት አቶ ዮሴፍ የፌደራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ያገባኛል ከሚሉ ወገኖች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለበት ያነሳሉ።

አቶ ሃፍቱ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚኖሩ ፍጥጫዎችን በማስቀረት ረገድ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ባይ ናቸው።

"የሕግ የበላይነትን በማክበር ጠንካራ ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ወደ ሕዝብ በማምጣት ሕዝብ እንዲመርጥ ለማድረግ፣ ሰላም፣ ልማት እና ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ።"

የውድብ ወለዶ ትግራይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሠለሞን በበኩላቸው "የፌደራል መንግሥቱ በአሁኑ ወቅት እየተወያየ ያለው ከአንድ ወገን ጋር [ከጊዜያዊ አስተዳደሩ] ብቻ ነው" በማለት ይህ ስህተት መሆኑን ያስረዳሉ።

"እኛ የምናምነው የትግራይ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ኃይሎች ጋር በሙሉ ከሲቪክ ማኅበረሰብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር መወያየት አለበት ብለን ነው የምናምነው" በማለት በትግራይ ያለውን ውጥረት ለመፍታት ከእነዚህ አካላት ጋር በቅርበት መሥራት አንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

እንደ አቶ ተክሊት ደግሞ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማለዘብ በሁለቱም ወገን የሚኖር "ቅን ልቦና" ያስፍለጋል፣ በተለይ ደግሞ ከፌደራል መንግሥቱ የበለጠ የሚጠበቅ ነው ይላሉ።

"አሁን ያለውን የትግራይ ፖለቲካ በተለያዩ አስተሳሰቦች በመከፋፈል ህወሓትን ቅርቃር ውስጥ ለማስገባት የሚጠቀምበት ከሆነ ግን የበለጠ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል" ሲሉ ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል።

ህወሓት ቅርቃር ውስጥ ሲገባ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚኖረው የክልሉ ግንኙነት ውስጥ ችግር መፍጠሩ አይቀርም የሚል ስጋት አቶ ተክሊት አላቸው።

"ፌደራል መንግሥቱ የፓርቲዎቹን ጉዳይ በቅን ልቡና የማይመለከተው ከሆነ ህወሓት ለፕሮፓጋንዳው እና ራሱን ለመከላከል ሊጠቀምበት ይችላል" በማለት ከህወሓት በመነጋገር መፍትሄ ማምጣት ወሳኝ ነጥብ ነው ይላሉ።