የፕሪቶሪያ ስምምነት ለምን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም? አዲስ ስምምነትስ ያስፈልጋል?

የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኡሁሩ ኬንያታ እና ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኡሁሩ ኬንያታ እና ጌታቸው ረዳ

የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ግጭቱን ከማስቆም ባሻገር የተጣለበትን ተስፋ ያህል ተግባራዊ የሆነ አይመስልም።

15 አንቀፆች ያሉት ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የህወሓት ወኪሎችን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ፊርማ ያረፈበት ነው።

የስምምነቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ በቋሚ የተኩስ አቁም ዘላቂ ሰላም ማምጣት ነው።

የኢፌዴሪን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ሕገ መንግሥትን ማክበር፣ እንደ ስልክ እና ባንክ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች መመለስ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ ትጥቅ መፍታት እና ውህደት፣ ስደተኞችን እና ተፈናቃዮችን መመለስ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ የስምምነቱ ቁልፍ ክፍሎች ናቸው።

ስምምነቱ በሁለቱ ተስማሚዎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር ሁለቱም ወገኖች መፈፀም አለባቸው ብሎ የሚዘረዝራቸው ኃላፊነቶችንም የያዘ ነው።

መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ፣ ከፊል የተፈናቃዮች መመለስ እንዲሁም ህወሓትን ከሽብርተኝነት መዝገብ መፋቅን የመሰሉ እርምጃዎች ወዲያው ተወስደዋል።

ስምምነቱ ቀን በመቁረጥ ቀላል መሳሪያዎችን ጨምሮ ህወሓት የታጠቃቸውን የጦር መሳሪያዎች ስምምነቱን በፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ በሙሉ እንደሚያስረክብ በአንቀፅ ስድስት ላይ ሰፍሯል።

ስምምነቱን ተከትሎ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት እና ወደ ማኅበረሰቡ መልሶ ለማዋሃድ የተመሠረተው ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን ከትግራይ ክልል 275 ሺህ ገደማ ታጣቂዎች ትጥቅ እንደሚያስፈታ የተናገረ ቢሆንም በዕቅዱ ልክ ግን መራመድ አልቻለም።

በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ዓለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረው ስምምነቱ አልተፈፀመም የሚሉ ክሶች መሰማት የጀመሩት ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በወራት ውስጥ ነው።

በተለይም የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው ደቡባዊ እና ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች እንዲሁም የተፈናቃዮች መመለስ ጉዳይ ጠንካታ ጥያቄዎች የተነሱባቸው ናቸው።

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከሦስት ዓመታት በኋላም መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሲሆኑ፤ ተፈናቃዮቹ የከፋ የሰብዓዊ እርዳታ ችግር እንደገጠማቸውም በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከሦስት ዓመታት በኋላም ትጥቅ ፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ ያልተዋሃዱት የክልሉ ተዋጊዎቹ ጉዳይም እንዲሁ።

ስምምነቱ ምን ገጠመው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዓለም አቀፍ ሕግ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር አደም ካሴ የፕሪቶሪያውን ስምምነት "ለመነጋገር አስቻይ ሁኔታ" የመፍጠሪያ መሠረት ብቻ አድርገው ይመለከቱታል።

"...ትግራይ ክልልን መልሶ ወደ ፌደራል፣ ወደ ተቋም፣ ወደ ፖለቲካው፣ ወደ አስተዳደሩ፣ ወደ ኢኮኖሚው መመለስ፤ ከዚያም አልፎ ደግሞ የተለያዩ ነጥቦቹ ላይ ስምምነት ለመድረግ፤ ለመነጋገር አስቻይ ሁኔታ የመፍጠር ነው አንጂ ስምምነቱ በራሱ የሚፈታው ነገር አልነበረውም" ይላሉ።

ሆኖም ክልሉ "ወደ ፌደራል አልተመለሰም" ሲሉ የፌደራል ውክልናን እና የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ማጣት ለአብነት በማንሳት ስምምነቱ ላለመፈፀሙ መሠረታዊ ችግር አድርገው ያዩታል።

የሰላም እና ግጭት ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሸትል ትሮንቮል በሁለቱም የፌደራል መንግሥቱ ምክር ቤቶች ውስጥ ትግራይ የፌደራል ውክልና "ማጣት" ስምምነቱ ላለመጸፈሙ ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው።

የፕሪቶሪያ ስምምነት ላለመፀሙ በተለይም የይገባኛል ውዝግብ ካለባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ከሦስት ዓመታት በኋላ አለመመለስ እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ይቀርባል።

ለተፈናቃዮች አለመመለስ የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት እርስ በእርስ የሚካሰሱ ሲሆን፤ ተፈናቃዮች በሁለቱ ኃይሎች ፍትጊያ በህወሓት እንደ "መያዣ" መሆናቸውን በመንግሥት እና በህወሓት ተቃዋሚዎች በኩል በተደጋጋሚ ይነሳል።

መንግሥት ተፈናቃዮችን ለመመለስ "ፅኑ አቋም" እንዳለው እና ህወሓት መሰናክል እንደሆነበት ደጋግሞ ሲናገር፤ ህወሓት ደግሞ ፌደራል መንግሥቱ ተፈናቃዮችን የመመለስ ፍላጎት የለውም የሚል ክስ ያቀርባል።

ሌላው የታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት፣ መበተን እና መዋኸድ (ዲዲአር) ሙሉ ለሙሉ አለመካሄድ ስምምነቱ በእንጥልጥል ላይ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

ምንም እንኳ በስምምነቱ ጥቂት ወራት ውስጥ ህወሓት ትጥቅ እየፈታ ነው ቢባለም፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ባለፈው ሐምሌ 2017 ዓ.ም. በአንድ የወታደራዊ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ያሰሙት ንግግር የፍጥጫውን ከፍታ የሚያሳይ ነው።

"ታንክ እና መድፉን አስረክቡ። አየር መቃወሚያውን አስረክቡ። ባለፈው ያስረከባችሁት አለ፤ ይህን ግን ደብቃችሁ ነው የቆያችሁት። አሁን ብቅ ብቅ እያደረጋችሁት ነው። በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት አስረክቡ" ሲሉ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው "ትግራይ የምንልከው በጀት ሙሉ በሙሉ የሚውለው ለወታደሮች ነው። ይህ ትግራይን እየጎዳ ነው ያለው" ብለዋል።

በእነዚህ እና በሌሎችም ምክንያቶች የስምምነቱ ዋነኛ ቁልፍ ጉዳዮች ወደ ተግባር ባለመሸጋገራቸው በሁለቱም ወገን ስጋት እና ጥርጣሬን ፈጥሯል።

የሞተባቸውን ሰው ፎቶ ይዘው የሚያለቅሱ ነጠላ እና ጥቁር ሻርፕ የለበሱ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የፕሪቶሪያው ስምምነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚነገረውን ጦርነት ያስቆመ ነው

ዶ/ር አደም ካሴም የፕሪቶሪያ ስምምነት ላለመፈፀሙ እምነት ማጣትን ትልቅ ስፍራ ይሰጡታል።

"ሰላምን ለማምጣት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ሁለቱም ያንን ነገር ለመውሰድ የተዘጋጁ አይመስለኝም።...ሁለቱም ጥንካሬያቸውን፤ ጉልበታቸውን አጎልብተው በንግግሩ ውስጥ የተሻለ [ውጤት] ለማግኘት ያሰቡ ይመስላል። ይሄ ደግሞ ጥርጣሬውን ይበልጥ እያሰፋው እና ምንአልባትም ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ያባባሰ፤ ወደ ግጭት እየገፋን ይመስለኛል።"

የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀፅ ሰባት በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመንን ለመፍጠር መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች በዝርዝር ቢያስቀምጥም፤ ጣት ከመቀሳሰር ግን የገታ አይደለም።

ከዚህም አልፎ ወደ ግጭት ዳግም ለመመለስ አዝማሚያዎች እና "ዝግጅቶች" እንዳሉ ተደጋግሞ የተነሳ ሲሆን፣ ባለፉት ሳምንታትም ሁለቱም ወገኖች ለሌላ ዙር ጦርነት በመሰናዳት አንዳቸው ሌላኛቸውን እየከሰሱ ነው።

ዶ/ር አደም ከህወሓት ሕጋዊ እውቅና ማጣት እስከ መከፋፈል ድረስ የተፈጠሩ ሁነቶች አለመተማመኑን እንደጨመሩ ጠቅሰው፤ "በንግግር ለመፍታት ሳይሆን በጉልበት ላለመጠቃት ራስን ማዘጋጀት በአብዛኛው ቅድሚያ የተሰጠው" ይመስላል ይላሉ።

"እምነት በሌለበት ሁኔታ ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ማሰብ ከባድ ነው። የድንበር ጉዳይ ሥርዓት ሳይበጅለት ፍላጎት ቢኖርም የተፈናቀሉ ሰዎችን መመለስ ከባድ ነው የሚሆነው። መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ላይ መፍትሔ ሳይበጅ እነዚህን ነገሮች መመለስ ከባድ ነው።

"መጀመሪያም ወደ ጦርነት ያስገባው አለመተማመን አልቀነሰም፤ እንዲያውም ጨምሯል። አንፃራዊ መተማመን ካልተፈጠረ ደግሞ ነገሮች ይፈታሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው" ይላሉ።

የሰላም እና ግጭት ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሸትል ትሮቮኖል፤ "የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመጀመሪያው ቀኑ ጀምሮ የተዳከመ ነው። ላለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ቁልፍ ስምምነቶችን ማስፈፀም አልተቻለም።"

አክለውም በፕሪቶሪያ ስምምነት በዋናነት የተጠበቀው ነገር መቀለ ባለው ጊዜያዊ አስተዳደር እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ግልፅ ግጭት እና ጦርነት እንዳይኖር ማድረግ መሆኑን በመጥቀስ፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት "ከሞላ ጎደል ፈርሷል" የሚል አመለካከት አላቸው።

ለዚህም ተመራማሪው እንደ አስረጂ የሚያቀርቡት ሁለቱም ወገኖች በጠላትነት እየተያዩ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ነው።

በእርግጥም ባለፉት ወራት በህወሓት በኩል ትጥቅ መፍታት እንደማይኖር እና የተጨማሪ የኃይል ሥልጠና እየተካሄዱ መሆናቸውን ወታደራዊ መሪዎቹ ከመናገራቸውም በላይ በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ነው።

በመንግሥት በኩልም ከየትኛውም ወገን ለሚመጣ ስጋት ምላሽ ለመስጠት የመከላከያ ሠራዊቱ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሲናገሩ ቆይተዋል።

በተጨማሪም ህወሓት በቀደመው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ከወጋው የኤርትራ መንግሥት ጋር "ፅምዶ" የሚባል ጥምረት በመፍጠር ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው በማለት መንግሥት ይከስሳል።

ህወሓት በበኩሉ የስምምነቱን ሦስተኛ ዓመት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መንግሥት "ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልፅ እንቅስቃሴ" እያደረገ ነው ሲል ከስሶ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አቤቱታውን አቅርቧል።

ስምምነቱ አለመፈፀሙ ምን አንደምታ አለው?

ትግራይ ክልልን አልፎ ተዛምቶ የነበረው ጦርነት በስምምነት እንዲቋጭ ዓለም አቀፍ ጫናዎች በርትተው ነበር።

ሁለቱ ወገኖች በተለያየ ጊዜ ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ ሲቀመጡም ሆነ መስማማታቸውን ሲያበስሩ ድጋፍ ዘንቦላቸዋል።

በሰነዱ ላይ ይህን ስምምነት ለማስፈፀም እና ለመከታተል በአፍሪካ ኅብረት የባለሙያዎች ቡድን የሚታገዝ እና በአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበርነት የሚመራ ከሁለቱም ወገኖች እና ከኢጋድ ወኪል የያዘ የጋራ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ይደነግጋል።

ኮሚቴው የስምምነቱን አፈፃፀሙን በይፋ ሐምሌ 2/2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ መገምገሙን ያሳወቀ ሲሆን፤ ዝርዝር መረጃም ሆነ ከዚህን ጊዜ በኋላ በይፋ ያለው ነገር የለም።

ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ አለመሆኑ እረፍት የሚነሳ መሆኑን የሚናገሩት የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር አደም ካሴ፤ ከማገገም ይልቅ እንደ አገር እና እንደ ማኅበረሰብ "ሀሳባችን፣ አቅማችን፣ ጉልበታችን፣ ሀብታችንም ለጦርነት ነው የሚሆነው።"

አንደምታውን ሲገልፁም "ችግራችንን ተነጋግረን ተስማምተን እንፈታዋለን የሚለውን የይቻላል ሀሳብ ያፈረሰው ይመስለኛል" በማለትም ሌሎች ግጭቶች በድርድር እንዳይፈቱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ይጠቁማሉ።

ስምምነቱ በአዲስ?

ዶ/ር አደም ከዚህ በኋላ የፕሪቶሪያ ስምምነት ይሠራል ብለው አያምኑም። በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸውን አማራ ክልል እና ኤርትራን ያካተተ አዲስ ስምምት ያስፈልጋልም ይላሉ።

"ሰፋ ያለ ፖለቲካዊ እምነትን፤ ሰፋ ያለ ሰላምን ለማምጣት አዲስ ነገር ነው የሚያስፈልገው። አዲሱ ነገር ደግሞ ሁለቱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትንም የሚያካትት መሆን አለበት ብዬ ነው የማስበው።

"አሁን ባለንበት ሁኔታ የትግራይን ጉዳይ ለብቻ መፍታት የማንችልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። አሁን የፕሪቶሪያን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መፈፀም አይቻልም" ሲሉ ከስምምነቱ በኋላ የተፈጠሩ አዳዲስ ሁነቶች አስቻይ አለመሆናቸውን ያሰምራሉ።

ፕሮፌሰር ሸትል ትሮቮኖልም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። የፕሪቶሪያ ስምምነት በአዲስ ስምምነት መተካት አለበት ይላሉ።

"በእውነተኛ ፖለቲካዊ መንገድ በተለይ በድርድር በአዲስ ስምምነት መተካት አለበት" የሚሉት ተመራማሪው፤ ለዚህ ግን ዝቅተኛ ፍላጎት እንዳለ እና "በሚያሳዝን ሁኔታ በኃይል ለውጥ ለማምጣት [ፍላጎት] ያለ ይመስላል።"

"ሁኔታውን ለማርገብ ከውጭ ያን ያህል እርምጃ መውሰድ የሚቻል አይመስለኝም። ዋነኛ ተቀናቃኞቹ ዓለም አቀፍ ምክር እንደማይሰሙ በተደጋጋሚ አሳይተዋል። እናም ለዓለም አቀፍ ጫና እጅ አይሰጡም። ለሰፊ የሰላም ስምምነት በአገር ውስጥ መፍትሔ መፈለግ አለባቸው።"