የትግራይ ኃይሎች "15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው" ወደ አፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ገብተዋል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, woyen
የአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ፤ የትግራይ ኃይሎች በወረዳው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "በከፈቱት ጥቃት"፤ "ወደ 15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው" መግባታቸውን እና "ስድስት መንደሮችን" መቆጣጠራቸውን በመግለጽ ከሰሱ። የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በበኩሉ "የከፈትነው ጥቃትም ሆነ የተቆጣጠርነው መሬት የለም" ሲል ወንጀላውን አጣጥሏል።
የአፋር ክልል መንግሥት "የህወሓት ቡድን" ሲል የጠራው ኃይል በክልሉ ዞን ሁለት መጋሌ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "የከባድ መሳሪያ ተኩስ መክፈቱን" በመግለጽ የከሰሰው ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው።
የመጋሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አብዱ ሼክ በራህ ኡስማን አጎራባች በሆነው የትግራይ ክልል የሚገኘው "የቲዲኤፍ ኃይል"፤ ከትናንት ረቡዕ "ጠዋት ጀምሮ ወደ ቦታ መያዝ" እንቅስቃሴ ገብቷል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሙሉ ቀን ያንን ቦታ ይዘው፣ እስከ 12 ሰዓት ሕዝቡ እየሸሸ፣ [ታጣቂው ቡድን] ቦታ እየያዘ ሄዷል። ከዚያ ሁሉንም ቦታ ከተቆጣጠረ በኋላ ከባድ መሳሪያ ወደ ሕዝቡ መወርወር የጀመረው [ምሽት] 12 ሰዓት አካባቢ ነው" ሲሉ በክልሉ መንግሥት የቀረበውን ውንጀላ አጠናክረዋል።
የአፋር ክልል መንግሥት "ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በንጹሐን የአፋር አርብቶ-አደሮች ላይ"፤ "በሞርታር እና በዙ-23" ከባድ መሳሪያዎች ተኩስ መከፈቱን በመጥቀስ በመግለጫው ወንጅሏል።
የአካባቢው ነዋሪ በተኩሱ ድምጽ "ተደናግጦ፣ መሸሹን" የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብዱ፤ ወደ ክልሉ እንቅስቃሴ ያደረገው "በጣም ብዙ ኃይል" መሆኑን አንስተዋል። የትግራይ ጦርነትን ያስቆመው "የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግጭት አዋጅ በግልጽ አፍርሷል" ሲልም ወቅሷል።
"አሁን ይሄ ነው ሊባል የሚችል አይደለም" ሲሉ የታጣቂዎችን ብዛት በቁጥር መጥቀስ እንደማይችሉ አክለዋል። መጋሌ ወረዳ ከትግራይ ክልል ጋር "በአራት ወረዳ" እንደሚዋሰን የሚናገሩት አቶ አብዱ፤ "በዚያ ግንባር ሁሉ ኃይሉ ገብቷል" ብለዋል።
ታጣቂው ኃይል "ስድስት እና በዚያ አካባቢ መደሮችን ይዟል። ሕዝብ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ማለት ነው። በቦታ ስፋት ግን ወደ 15 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል" ሲሉ ከስሰዋል። ዋና አስተዳዳሪው በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆኑ የጠቀሷቸው "ካርፋቱ"፣ "አለ ጉቢ"፣ "ሚልኪ"፣ "ጎረ አይ"፣ "ጉላ ዲዳ" እና "ዳልጊና" የተባሉ መንደሮችን ነው።
አቶ አብዱ አክለውም "የቀበሌውን ማዕከል እስካሁን አልያዙም። ግን ከማዕከል ውጪ ያሉ አንድ ኪሎ ሜትር [ርቀት ላይ ያሉ አካባቢዎች] ሙሉ በሙሉ በእነሱ ቁጥጥር ውስጥ ናቸው" ብለዋል። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ፤ በታጣቂዎች እጅ ወድቀዋል የተባሉት አካባቢዎች ነዋሪ የነበሩ ሰዎች ወደ አቶምሳ ቀበሌ "ማዕከል" እና "አሮሪ የሚባል አካባቢ" ሸሽተዋል።
"ሕዝቡ ገና ስላልተረጋጋ" ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ መጥቀስ እንደማይችሉ የሚገልጹት አቶ አብዱ፤ "ተቆርጦ የቀረም ሕዝብ አለ" በማለት ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ በአሁኑ ሰዓት የተኩስ ድምጽ እንደሌለ ቢገልጹም፤ ታጣቂው ቡድን "ወደፊት እየገፋ" በመሆኑ "በድጋሚ ተኩስ ይነሳል" የሚል ስጋት መኖሩን አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, magalle woreda communication
አፋር ክልል መንግሥት በትናንት መግለጫው፤ የህወሓት ቡድን "ከድርጊቱ በአስቸኳይ ካልተቆጠበ"፤ "የዜጎች ደኅንነት እና የወሰኑን ክብር የማስጠበቅ፣ እንዲሁም ራስን ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ" አስጠንቅቋል።
ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብዱ፤ "የአካባቢ ሚሊሻ እና ሕዝብ ካልሆነ በቀር" እስካሁን ድረስ ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸዋል ወደተባሉ ቦታዎች እንዲገባ የተደረገ "የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት ኃይል አለመኖሩን" ተናግረዋል። "በክልሉ መንግሥት [በኩል] 'ጦርነቱ እንዳይከሰት' ተብሎ ይመስለኛል እስካሁን ወደዚያ የመጣ ኃይል የለም" ብለዋል።
ጥቃት ተከፍቶባቸዋል በተባሉት አካባቢዎች ላይ "ሓራ መሬት" ወይም "የትግራይ ሠላም ኃይል" በመባል የሚታወቁት ከትግራይ ኃይሎች የተገነጠሉ ታጣቂዎች ስለመኖራቸው ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አብዱ፤ "የተያዘው ቦታ፣ ተኩስ የተከፈተበት አካባቢም ላይ እንደዚያ የሚባሉ ሰዎች የሉም" ብለዋል።
ቢቢሲ በአፋር ክልል መንግሥት የቀረበውን ክስ በተመለከተ ለትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ለሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ተክላይ ኪዳነ ጥያቄ አቅርቧል። የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው "አፋር ገብተን የተቆጣጠርነው አንድም ቦታ የለም" ሲሉ በትግራይ ኃይሎች ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።
"እኛ የከፈትነው ግጭት የለም፤ እንደዚህ ዓይነት ዝግጁነትም የለም" የሚሉት ብርጋዴር ጄነራል ተክላይ፤ በምላሹ "የአፋር ኃይል" እና "የሓራ መሬት ኃይሎች"፤ "ተደጋጋሚ ትንሳዎችን" ፈጽመዋል ሲሉ ከስሰዋል።
"በአፋር ራሳቸውን ሓራ መሬት ብለው የሚጠሩት በተደጋጋሚ ከአፋር ኃይል ጋር ሆነው የተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ነበር። የሰውም ጉዳት ደርሶብናል፤ እናውቃለን። የደረሰውን ጉዳት ግን በሚዲያ መግለጽ አንፈልግም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, sm
ብርጋዴር ጄነራል ተክላይ፤ "ተደጋጋሚ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል" በሚል የጠቀሷቸው "ምላዛት"፣ "አኻዛ"፣ "ደስአ"፣ "ወጀራት" እና "ገረብ አገው" የተባሉ አካባቢዎችን ነው።
ባለፈው ሳምንት እሁድ ጥቅምት 23/2018 ዓ.ም. "ገረብ አገው እና ደደርባ በሚባል አካባቢ ትንኮሳዎችን ፈጽመዋል፤ ጉዳትም ደርሷል" በማለት ወንጅለዋል።
"እንደውም እንጠያየቅ ከተባለ፤ 'ብዙ አያስፈልግም' ብለን ስላሰብን እንጂ የአፋር ልዩ ኃይል የትግራይ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ እናውቃለን። ይህንን በይፋ ለሕዝባችን ግልጽ እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እነዚህ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ የወሰደው "ራስን የመከላከል" እርምጃም ሆነ የተሰጠ "ግብረ መልስ እንደሌለ" የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው ይናገራሉ።
"ራስን ለመከላከል ካለንበት ተነስተን እርምጃ መውሰድ እንችላለን፤ ግን አላደረግነውም። ባለንበት ሆነን ራሳችንን ከመከላከል ውጪ የተቆጣጠርነው፣ የሄድንበት ቦታም የለም" ሲሉ የትግራይ ኃይሎችን ተከላክለዋል።
"የፕሪቶሪያው ስምምነት 'ፈርሷል' እስካልተባለ ድረስ እሱን አክብረን መቀጠል ነው የምንፈልገው" የሚሉት ብርጋዴር ጄነራል ተክላይ፤ "ለሌላ ጣልቃ ገብነት የሚሆን 'ቀዳዳ ማግኘት እንችል ይሆን?' በሚል ተስፋ ካልሆነ በቀር አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአፋር ክልል መንግሥት በህወሓት ይህንን ክስ ያቀረበው የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል አመረሮች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጠንካራ ውንጀላዎችን እያቀረቡ ባሉበት ወቅት ነው።
ህወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት የተፈረመበትን ሦስተኛ ዓመት በማስመልከት እሑድ ጥቅምት 23/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግሥት "ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ" እያደረገ ነው ሲል ከስሷል።
የፌደራል መንግሥት "ታጣቂዎች በመመልመል፣ በማሠልጠን እና በማደራጀት የትግራይ ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲዋጋ እየሠራ" እንደሆነ በመጥቀስም ወንጅሏል።

የፎቶው ባለመብት, EBC/SCREENSHOT
በማግሥቱ በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ደግሞ "የክህደት ኃይል" ሲሉ የጠሩትን የህወሓት ቡድን "እስካልተነቀለ ድረስ ኢትዮጵያ ሠላም አታገኝም" ሲሉ ተደምጠዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ በህወሓት የተፈጸሙ "ትንኮሳዎች፣ ሥራዎች እና ሴራዎች ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ናቸው" ሲሉም በህወሓት ውስጥ አሉ ያሏቸውን "የተወሰኑ ቡድኖች" ወንጅለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ትናንት ረቡዕ ምሽት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት አጭር ጽሁፍ፤ የፌደራል መንግሥትን "ጎትቶ ወደ ግጭት ለማስገባት" እየሞከረ ነው ያሉትን "ኃላ ቀር ቡድን" ከስሰዋል።
ይህ ቡድን "የፕሪቶሪያውን ውል ለመቅደድ ሁሉንም ዓይነት ትንኮሳ" ሞክሯል ያሉት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት፤ አሁን ደግሞ "በአፋር በኩል ነገር እየቆሰቆሰ" ነው ብለዋል።
ቡድኑ ይህንን እያደረገ ያለው ከዚህ ቀደም ለነበሩ ትንኮሳዎች "ግብረ መልስ ሳይሰጥ" የቀረውን የፌደራል መንግሥትን "ጎትቶ ወደ ግጭት ለማስገባት" እንደሆነ በጽሑፋቸው አስፍረዋል።
ይህ እንቅስቃሴ "በአለቃቸው ትዕዛዝ እየተፈጸመ ያለ የሻዕቢያ አጀንዳ ነው" ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ለዚህ ተግባር "ቀንደኞቹ ፈጻሚዎች እና ተጠያቂዎች" በሚል የጠቀሷቸው የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ሜጀር ጄነራል ፍሰሃ ኪዳኑ (ማንጁስ) እና ሜጀር ጄነራል ዮሃንስ ወልደጊዮርጊስን (መዲድ) ነው።
አቶ ጌታቸው እየተደረገ ነው ያሉትን እንቅስቃሴም "ማስቆም የሚችሉትም" እነኚሁ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እንደሆኑ ገልጸዋል።















