አይሾውስፒድ፡ "ገና ኢትዮጵያ 2018 ላይ ናት? 13 ዓመቴ ነው ማለት ነው?"

የፎቶው ባለመብት, FANABC
በዓለማችን ታዋቂ ከሆኑ ይዘት ፈጣሪዎች አንዱ የሆነው ወጣት በአፍሪካ 20 ሀገራት ለመጎብኘት ቆርጦ ከተነሳ ቀናት ተቆጥረዋል።
"በምስራች የተሞላች" በሚላት አህጉር እየተዟዟረ በቀጥታ የሚያስተላልፋቸው ቪድዮዎችን ሚሊዮኖች ተመልክተውለታል።
በኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ታዳጊዎች እሱን ሲያዩ በደስታ ፈንጥዘዋል። በኢንተርኔት የሚያውቁትን ወጣት በአካል በማግኘታቸው ደስታቸው ወደር አልነበረውም።
አይሾውስፒድ አሊያም ስፒድ በዩቲዩብ ከ48 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት። አንዳንድ ጊዜ 3 ሰዓታት ሌላ ጊዜ ደግሞ 11 ሰዓታት ቀጥታ እያስተላለፈ ይቆያል። ተፅፈው ባልተዘጋጁ ሞቅ ባሉ ይዘቶቹ ነው የሚታወቀው።
ጥቁር አሜሪካዊው ስፒድ በቅርቡ 21 ዓመት ይሞላዋል።
በኢስዋቲኒ 'ሊጂማኮ' የተሰኘ ቅፅል ስም ተሰጥቶታል፤ ሯጩ እንደማለት ነው። በንጉሣዊው ቤተ-መንግሥት ተገኝቶ ንጉሡንና ቤተሰቦቹን እንዲጠብቅ ሲመረጥ በቀጥታ ስርጭቱ አሳይቷል።
ሌሎች አፍሪካዊያን ደግሞ 'ስፒዳኒ' ሲሉ ይጠሩታል።
የመዝገብ ስሙ ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር የሆነው ስፒድ በመጀመሪያ የጎበኛት የአፍሪካ ሀገር አንጎላ ናት። ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሀገራትን ጎብኝቷል። ናይጄሪያ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ላይቤሪያ እና ጋናንም እንደሚያዳርስ ይጠበቃል።
ከካሜራ ባለሙያዎች፣ የጥበቃ ሰዎች እና ሎጂስቲክ ከሚያንቀሳቅሱ ባልደረቦቹ ጋር አብሮ ነው የሚንቀሳቀሰው።
የአፍሪካን ታሪክ፣ የቀን ተቀን ሕይወት፣ ባሕል እና ምግብ እንዲሁም ስፖርት ለማጣጣም ነው ዕቅዱ። በመንገዱ አድናቂዎቹን እና እሱን የሚመስሉ ወጣቶችን አግኝቷል። በኢትዮጵያም የገጠመው ይህ ነው።
የአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የቱሪዝም ሚኒስትሮችንም አናግሯል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ስፒድ በቀጥታ ስርጭቱ የሚያገኛቸውን ሰዎች ሲያናግር ይስተዋላል።
"አፍሪካ ምን እንደምትመስል ለዓለም ማሳየት እፈልጋለሁ" ሲል በደቡብ አፍሪካ ቆይታው ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Eswatini Tourism
አንዳንዶች የአፍሪካ ጉዞው የረባ ነገር የለውም ሲሉ ትችታቸውን ያሰማሉ። እራሱን ብቻ ነው የጠቀመው ይላሉ።
ስፒድ 'ጌመር' ሆኖ ነው ወደ እውቅና የመጣው። ቁጭ ብለው የኮምፒውተር ጌም እየተጫወቱ ቀጥታ ከሚያስተላልፉ ወጣቶች መካከል ነበር።
በ2022 እውቅናው እየጨመረ ሲመጣ ከመቀመጫው ተነስቶ ሌሎች ይዘቶችን መፍጠር ጀመረ። ቀጥሎ ወደ እግር ኳስ ዓለም ገባ።
ወደ እውቅና የመጣበት መንገድ አከራካሪነት የተለየው አይደለም።
ራዮት ጌምስ ከሚባለው ውድድር የታገደው አንዲት ተጫዋች ላይ ባደረሰው ዘለፋ ምክንያት ነበር። ያደረገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ አምኖ ይቅርታ ጠይቋል።
ጌም እየተጫወተ ሳሉ ወሲባዊ የሆነ እንቅስቃሴ አሳይቷል ተብሎ ለአንድ ሳምንት ከዩቲዩብ ታግዶም ያውቃል።
እንደ ውሻ በመጮህ፣ ወደኋላ በመገልበጥ እና የአትሌቲክስ እንቅስቃሴዎችን በማሳየት ይታወቃል። እየበረረ የሚመጣ መኪና ዘሎ ተሻግሯል። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የእግር ኳስ ጀግናው ነው። "ሱ. . . " እያሉ ደስታውን ይገልፃል።
በእንግሊዝኛ ጄን ዚ እና ጄን አልፋ የሚባሉት ትውልዶች ገደብ የሌለው፤ ተፅፎ ያልተዘጋጀ ይዘቱን ይወዱለታል። በቀጥታ ስርጭቱ ምንም ነገር ሊፈጠር ይችላል።
"ያለውን ጉልበት እና የሚያደርገውን ነገር በጣም ነው የምወድለት" ሲል የ16 ዓመቱ ዛምቢያዊ አድናቂው ቺናያማ ዮንጋ ለቢቢሲ ይናገራል።
"እንደ ውሻ ሲጮህ እንኳ ያስቀኛል" ይላል ስፒድ ላይ ለማየት ከተገኙ በርካታ ዛምቢያዊያን መካከል የሆነው ቺናያማ።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ተገኝቶ 4 ሰዓታት ለሚሆን ጊዜ የቀጥታ ስርጭት በርካታ ነገሮችን አሳይቷል።
ቁምጣ እና 7 ቁጥር ያለበት ቢጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ማሊያ ለብሶ ከተማዋን ተዘዋውሯል።
ከመርካቶ ባሕላዊውን ሸማ ሸምቶ ወደ ሳይንስ ሙዚየም ገብቶ ጎብኝቷል፤ ወደ አድዋ መታሰቢያ አቅንቶ በባዶ እግሩ የአድዋ አርበኞችን ዘክሯል።
ኢትዮጵያ የራሷን የዘመን አቆጣጠር እንደምትከትል በሰማ ጊዜ "እንዴ! ገና አሁን 2018 ናችሁ? 13 ዓመቴ ነው ማለት ነው? ሮናልዶ አሁንም ለሪያል ማድሪድ ነው የሚጫወተው?" ሲል የተሰማውን ገልጿል።
ስፒድ እስክስታም ሲጨፍር ነበር። የ33 ዓመቱ ዮናኤል ታዲዮስ በመገረም ሲመለከተው ነበር።
"ከባሕላዊ ጨፋሪዎች ጋር የነበረው ቁርኝት በጣም የሚገርም ነው" ሲል ዮናኤል ለቢቢሲ ይናገራል። "ስፒድ ጥሬ ስጋ ለመብላት መሞከሩ በራሱ የሚደነቅ ነው" ይላል።
የዐፄ ኃይለ ሥላሤን ኃውልት እያሳያ ሳለ የኢንተርኔት አገልግሎቱ በመንቀራፈፉ ምክንያት ተቋርጦበታል።
ያም ሆነ ይህ ስፒድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ዮናኤል ደስተኛ ነው። "በርካታ ይዘት ፈጣሪዎች ስለኢትዮጵያ ባላቸው የተሳሳተ አመለካከት ምክንያት ወደዚህ አይመጡም" ይላል።
አንዳንድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የስፒድ የአፍሪካ ጉዞ "ካለው ስልታዊ እንግልት ትኩረት ለማዞር የሚደረግ ሙከራ" ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
ነገር ግን ዮናኤል በዚህ አይስማማም። "በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ስለሀገራችን አዎንታዊ እይታ እንዲኖራቸው አድርጓል" ይላል።












