በሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ የሚፈለጉት ተጠርጣሪ ፈረንሳይው ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, US STATE DEPARTMENT
ፌሊሲዬን ካቡጋ፤ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል እጅጉን ተፈላጊ ሰው ናቸው። ሰውዬው ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፈረንሳይ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ካቡጋ ፈረንሳይ ውስጥ አዝኒዬር ሱር ሴን በተሰኘ ሥፍራ ማንታቸውን ቀይረው እየኖሩ ነበር ተብሏል።
ዓለም አቀፉ የሩዋንዳ ወንጀል ችሎት የ84 ዓመቱን ግለሰብ በዘር ማጥፋት ወንጀል እና የሰው ልጅ ላይ ሰቆቃን በመፈፀም ወንጀል ይፈልጋቸዋል።
በፈረንጆቹ 1994 የሁቱ አክራሪዎች 800 ሺህ ያክል ሰዎችን ሲጨፍጭፉ ሰውዬው አክራሪዎቹን በገንዘብ ደግፈዋል ይባላል።
የሁቱ አማፅያን በወቅቱ የአናሳዎቹን ቱትሲዎችና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ዒላማ አድርገው ነበር ጥፋት የፈፀሙት።
ዩናይትድ ስቴትስ፤ ካቡጋ ያለበትን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ማለቷ አይዘነጋም።
በሄግ የሩዋንዳን ጉዳይ የሚከታተሉት ዋና አቃቤ ሕግ ፈረንሳይ ሰውዬውን ልታገኝ የቻለችው ከብዙ ፍለጋና ድብቅ ኦፕሬሽን በኋላ ነው ብለዋል።
"የፌሊሲዬን ካቡጋ መታሠር የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀም የተጠረጠሩ ሰዎች ከ26 ዓመታት በኋላ ሊያዙ እንደሚችሉ ማሳያ ነው" ብለዋል ዋና አቃቤ ሕግ ሰርጌይ ብራሜርትዝ።
አቃቤ ሕጉ አክለውም የሰውዬው በቁጥጥር ሥር መዋል አገራት የሚተባበሩ ከሆነ የወንጀል ተጠርጣሪዎች የትም መደበቅ እንደማይችሉ ያሳየ ነው ብዋል።
አቃቤ ሕጉ ለፈረንሳይ መንግሥት ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ፤ ሩዋንዳ፣ ብሪታኒያ፣ ጀርመንና አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች አገራትና ድርጅቶች ትብብር ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
ሰውዬው በፈረንሳይ ሕግ መሠረት አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ዓለም አቀፉ የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ወንጀልን ወደሚመለከተው ችሎት እንደሚተላለፉ ተነግሯል። በዚያም ፍርዳቸውን መከታተል የሚጀምሩ ይሆናል።
ካቡጋ በፈረንጆቹ 1997 ነው በሰባት ወንጀሎች እንደሚፈለጉ የተነገረው። ዘር ማጥፋትና የዘር ጥፋት ማነሳሳት ከሚጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል ናቸው።
ካቡጋ የፎ ደ ዴፎንስ ናሲዮናል [ኤፍዲኤን] ተባባሪ መሥራች ናቸው። ይህ ድርጅት ደግሞ ለወቅቱ የሩዋንዳ ጊዜያዊ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የዘር ማጥፋቱ እንዲፋፋም አግዟል ስትል አሜሪካ ሰውዬውን ትከሳለች።
ሰውዬው ከዚህም አልፎ ለታጣቂዎች የሎጂስቲክ መረጃ በመስጠት እንዲሁም የወታደር መለያና መሣሪያ በማስታጠቅ የዘር ጥፋቱን አፋፍመዋል ተብለው ሲፈለጉ ቆይተዋል።












