ሩዋንዳ፡ የ'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ጀግናው በሽብር ክስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

Paul Rusesabagina

የፎቶው ባለመብት, RIB

የምስሉ መግለጫ, የ'ሆቴል ሩዋንዳ' ፊልም ጀግናው በሽብር ክስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በፈረነንጆቹ 1994 ላይ በፈጸሙት ጀብድ ''ሆቴል ሩዋንዳ'' የተሰኘው ፊልም ሆሊውድ እንዲሰራው ምክንያት የሆኑት ግለሰብ በሽብር ክስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሩዋንዳ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የሁቱ ተወላጅ የሆኑት ፖል ሩሰሳባጊና በሩዋንዳ ተከስቶ በነበረው የዘር ጭፍጨፋ ወቅት ሆቴል ሩዋንዳ በሚሰኘው ሆቴላቸው ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎችን ከጥቃት በማስመለጣቸው ይወደሳሉ።

በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ከ800ሺህ በላይ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ተጨፍጭፈው ተገድለዋል።

ፖል ሩሰሳባጊና ከሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በኋላ የጦር ክንፍ ያለው እና መቀመጫውን ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ያደረገ ተቃዋሚ ፓርቲ መስርተው ነበር።

ዓለም አቀፍ የእስር ትዕዛዝ ከወጣባቸው በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ66 ዓመቱ ፖል በፖሊስ ታጅበው እና እጃቸው በካቴና ታስሮ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ላይ ታስረው ታይተዋል።

ፖል ሩስሳባጊና ከአገር ውጪ ሲኖሩ የቆዩ ሲሆን የአገሪቱ ባለስልጣናት ፖል ስለተያዙበት ሁኔታ እንዲሁም ስለቀረበባቸው ክስ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

በፈረንጆቹ 2011 ላይ በሩዋንዳ የሚገኝን ኃይል በገንዘብ ይደግፋሉ ተብለው ይተቹ ነበር።

2004 ላይ ለዕይታ በበቃው ሆቴል ሩዋንዳ ፊልም ላይ የቱትሲ ተወላጅ ያገቡት ፖል ሩሰሳባጊና የዘር ጭፍጨፋ የሚያካሂዱ የቱሁ ሚሊሻዎችን ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው በመጠቀም እና በገንዘብ በመደለል እስከ 1200 የሚሆኑ ቱትሲዎችን ሲያተርፉ ይታያል።