ኖርዌይ ፡ በአንድ ዋሻ ውስጥ ሲዝናኑ የነበሩ ሰዎች በጭስ ታፍነው ሆስፒታል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ ውስጥ በሚገኝ በአንድ ከመሬት በታች ባለ ዋሻ ውስጥ ተሰባስበው እየተዝናኑ ከነበሩ ሰዎች መካከል ከ20 የሚበልጡት በካርበን ሞኖክሳይድ ጭስ ታፍነው በመመረዛቸው ሆስፒታል መግባታቸው ተነገረ።
ግለሰቦቹ ሊገኙ የቻሉት በአካባቢው ቅኝት ሲያደርጉ የነበሩ ፖሊሶች በዋሻው ውስጥ ከነበሩት መካከል የተወሰኑት ራሳቸውን ስተው ወደ ጎዳና በመውጣት ወዲያ ወዲህ ሲሉ ካገኟቸው በኋላ ነው።
ከዚህም በኋላ ሌሎቹ ጓደኞቻቸው በጭሱ ታፍነው ከዋሻው ውስጥ በመውጣታቸው አምቡላንስ ተጠርቶ ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ተደርጓል።
ባለስልጣናቱ የፓርቲው ታዳሚዎችን ለመመረዝ ያበቁት ወደ ዋሻው ይዘው ከገቡት አነስተኛ ጄኔሬተር በሚወጣ ጭስ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ።
በጭሱ የመመረዝ ጉዳት ካጋጠማቸው 25 ሰዎች መካከል ሁለቱ በዋሻው ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ፖሊሶች ናቸው።
ግለሰቦቹ አሁን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተም "እድለኞች ናቸው፤ የሁሉም የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ ነው። በጤናቸው ላይ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም" ሲሉ በኦስሎ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ዋና ሐኪም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከ20 በላይ ሰዎች በጭስ በታፈኑበት በዚህ ዝግጅት ላይ 200 የሚደርሱ ሰዎች ታድመውበት እንደነበር የኦስሎ ፖሊስ አስታውቋል።
በተጨማሪም ታምመው ወደ ሆስፒታል ከገቡት የፓርቲው ታዳሚዎች ውጪ ያሉት ማቅለሽለሽ፣ የራስ ምታት፣ ራስን የመሳት ስሜት ካጋጠማቸው ወደ ሐኪም ቤት እንዲሄዱ ፖሊስ መክሯል።
ፖሊሶች በአደጋው ስፍራ ከመድረሳቸው በፊት ከዋሻው ወጥቶ የሄደ የዝግጅቱ ታዳሚ እንዳለው በስፍራው በነበረው የታፈነ አየር ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ ውጪ እየወጣ አየር ሲወስድ ነበር።
የኦስሎ ፖሊስ በዋሻው ውስጥ ስለተካሄደው ዝግጅት ቀድሞ ጥቆማ የደረሰው ቢሆንም በወቅቱ ለምን እርምጃ መውሰድ እንዳልቻለ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
















