ኮሮናቫይረስ ፡ በአውሮፓ ከተሞች "ኮቪድ-19 ውሸት ነው" የሚሉ ተቃውሞዎች እየተካሄዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከአርብ ጀምሮ እየተካሄዱ ያሉ ሰልፎች መልከ ብዙ ቢሆኑም 'ጭራሽ ኮሮና የሚባል ቫይረስ ብሎ ነገር የለም፣ እየተጭበረበርን ነው' ብለው የሚያምኑ ሰልፈኞችም የተገኙበት ሆኗል፡፡
የብዙዎቹ ሰልፈኞች ጥያቄ ግን በኮሮና ምክንያት የተጣሉ ገደቦች ይነሱ የሚሉ ናቸው፡፡
በጀርመን በርሊን ሰፊ ተቃውሞ የተካሄደ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ 300 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
የጀርመን ሰልፈኞች ያነሱት ተቃውሞ በዋናነት 'በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጥብቅ የተደረጉ መመሪያዎች ይነሱልን መረረን' የሚል ነው፡፡
በጀርመን ለተቃውሞው 40ሺ የሚጠጉ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በአመዛኙ ሰላማዊ ሆኖ የቆየው ተቃውሞ በነጭ አክራሪዎች ነውጥ ምክንያት መልኩን እየቀየረ መጥቷል፡፡ ድንጋይና ጠርሙስ መወራወርም ተጀምሯል፡፡
በበርሊን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአውሮፓ ከተሞች ተመሳሳይ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡
በለንደን በዝነኛው ትራፋልጋር አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ብዙዎቹ "ኮሮናቫይረስ ብሎ ነገር የለም፤ እየተጭበረበርን ነው" የሚል ይዘት ያላቸው መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡
በፓሪስ፣ በቪየና እንዲሁም በዙሪክ ይኸው ተቃውሞ በተመሳሳይ መንፈስ ቀጥሏል፡፡
በጀርመን የተካሄደው ተቃውሞ ፍትጊያ የበዛበትና ማኅበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ አስቸጋሪ እንደነበር ፖሊስ አምኗል፡፡
"ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ የሚቻለውን ለማድረግ ሙክረናል፡፡ በሰልፈኞች መሀል የኮሮናቫይረስ ደንቦችን ማስጠበቅ ግን አልቻልንም" ብሏል ፖሊስ በትዊተር ገጹ፡፡
ፖሊስ በቁጥጥር ካዋላቸው ሰዎች መሀል አንዱ "ኮሮናቫይረስ ብሎ ነገር የለም፣ ዉሸት ነው የሚለውን መላምት በማራገብ የሚታወቀው አቲላ ሂልድማን" ይገኝበታል፡፡
ሂልድማን ለሰልፈኞች ድምጽ ማጉያ ይዞ ተከታታይ ንግግር ሲያደርግ ነበር፡፡
ሂልድማን በጀርመን እውቅ የምግብ አብሳይ ባለሙያ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የነጭ አክራሪዎችን አስተሳሰብ በመጋራት ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኗል፡፡
"ኮሮናቫይረስ የሚባል ነገር የለም፤ ጀርመን ከቢልጌትስ መወገኗን ታቁም" የሚሉ አስተሳሰቦችን ማራመድ በመጀመሩ ብዙ ተከታዮችን አፍርቷል፡፡
ብዙዎቹ ሰልፈኞቹ ጭምብል ማጥለቅና ሌሎች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚወሰዱ መመርያዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ስለሆኑ እንዳሻን እንሁን የሚል ጥያቄ ነው ያነሱት፡፡
ከሰልፈኞቹ መሀል እውቅ ሰዎችም ተገኝተውበታል፡፡
ለምሳሌ ሮበርት የጆን ኤፍ ኬኔዲ ልጅ ለሰልፉ ድጋፍ ከሰጡት መሀል ይገኝበታል፡፡
ሮበርት ኬኔዲ ጁንየር በሰው እጅ የተገደሉት የዝነኛው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የወንድም ልጅ ሲሆን ክትባትን በመቃወም ከፍተኛ ተከታይ ያፈራ ሰው ነው፡፡
ሮበርት ኬኔዲ በርሊን ድረስ በመምጣት ሰልፉን ተቀላቅሏል፡፡
ጀርመን እስካሁን 242,000 ሰዎች በኮቪድ-19 እንደተጠቁባት እና ከ10ሺ ሰዎች በታች እንደሞቱባት ይታወቃል፡፡

















