ኮሮናቫይረስ፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ20 በላይ ተለማማጅ ሐኪሞች በኮሮናቫይረስ ተያዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እና የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሁለት ሐኪሞችና 20 ተለማማጅ ሐኪሞች [ኢንተርኖች] በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተገለፀ።
ቢቢሲ ከዩኒቨርስቲው ምንጮች ባገኘው መረጃ መሰረት እስከ ማክሰኞ 17፣ ረቡዕ አራት እና ሐሙስ ደግሞ አንድ፤ በአጠቃላይ 22 ሐኪሞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ መካከል ሰባቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።
ይህንንም ተከትሎ ሁሉም ተለማማጅ ሐኪሞች ሥራ እንዳይገቡ እንደተነገራቸውና ሐሙስ ጀምሮ ሥራ አለመግባታቸውን ያነጋገርነው ስሙ አዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ተለማማጅ ሐኪም ለቢበሲ ገልጿል።
በሽታው እንደተገኘባቸው ካወቁ ሐኪሞች መካከል ቢቢሲ ያናገራቸው ባለሙያዎች ለቫይረሱ ሊጋለጡ የቻሉት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ታካሚዎች በቅድሚያ ከእነርሱ ጋር እንደሚገናኝና በእነርሱ ከታዩ በኋላ ወደ ሌሎች ምርመራዎች እንደሚላኩ ገልጸው፤ ይህ የሥራቸው ሁኔታ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገምታሉ።
ነገር ግን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ አስፈላጊ የመከላከያ አልባሳትና ሌሎች አቅርቦት በበቂ ሁኔታ አለመቅረባቸው ተጋላጭነታቸውን ከፍ አድርጎታል ሲሉ ይጠቅሳሉ።
"ሰርጂካል ማስክ' እና አልኮል ተሰጥቶናል። በ15 ቀናት አስር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ነው የሚሰጠን። አንድ ጭምብልን በአማካይ ከ24 ሰዓታት በላይ ነው የምንጠቀምበት" ሲል የመከላከያ ቁሶች በበቂ ሁኔታ እንደሌሉ ከተለማማጅ ሐኪሞቹ መካከል አንዱ ተናግሯል።
ለቫይረሱ ከተጋለጡት ሰባት ሴት ተለማማጅ ሐኪሞች መካከል አንዷ የሆነችው ለቢቢሲ እንዳረጋገጠችው እርሷን ጨምሮ 22 ተለማማጅ ሐኪሞች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልፃ፤ በበሽታው የተያዘችበትን ምክንያት ወይም አጋጣሚ ግን በውል እንደማታውቀው ተናግራለች።
በሆስፒታሉ ውስጥ በኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ሳይሆን በመደበኛ የሕክምና አገልግሎት ክፍል ውስጥ እንደምትሰራ የገለፀችው ሐኪም እንዳለችው "በሽታው እንዳለባቸው ሳይታወቅ የሚመጡ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ለበሽታው የተጋለጥነው ምናልባት ከዚያም ሊሆን ይችላል" ስትል ግምቷን አስቀምጣለች።
ይህችው ተለማማጅ ሐኪም እንዳለቸው በሆስፒታሉ ውስጥ የእጅ ጓንትና ሌሎች ከቫይረሱ የመከላከያ ግብዓቶች እጥረት መኖሩንም ግምቷን ገልፃለች።
"ብዙ ጊዜ በባዶ እጄ ነው የምንሰራው። በአብዛኛው ታማሚዎች የእጅ ጓንት እንዲገዙ እናደርጋለን። መግዛት የማይችሉትን ግን ካለጓንት በባዶ እጃችን እናክማለን፤ የግድ ጓንት የሚያስፈልገው ሕክምና ካለም ከሌላ ክፍል እንበደራለን" ስትል ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።
እስካሁን በበሽታው ከተያዙ ተለማማጅ ሐኪሞች ውስጥ በፅኑ የታመሙ እንደሌሉና አብዛኞቹም የበሽታው ምልክት እንዳልታየባቸው ተናግራለች።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ቢቢሲ ያናገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እና የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው፤ ሁለት ሲኒየር ሐኪሞች እና 20 ተለማማጅ ሐኪሞች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጠዋል።
በቫይረሱ የተያዙት ተለማማጅ ሐኪሞች በኮሮናቫይረስ ሕክምና ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ እንዳልሆኑ ገልፀው፤ በቫይረሱ ሊያዙ የቻሉት በሥራ ቦታ አሊያም በግል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወቅት ሊሆን እንደሚችል፤ ነገር ግን በሐኪሞቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የጥንቃቄ ጉድለት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ለባለሙያዎች የሚያስፈልጉ የበሽታው መከላከያ አቅርቦቶች እጥረት መኖሩን በተመለከተ ከቢቢሲ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ፤ ተለማማጅ ሐኪሞች በቀን ስምንት ሰዓት እንደሚሰሩ ጠቅሰው፤ በወር 22 ቀን ይሰራሉ ተብሎ ታስቦ በቀን አንድ ማስክ እንደሚሰጣቸው፤ ነገር ግን በሳምንት ሁለት እና ሦስት ቀን ብቻ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ር አሸናፊ አስፈላጊ የሚባሉት የበሽታው መከላከያ አልባሳት (ፒፒኢ) በአገር አቀፍ ደረጃ እጥረት መኖሩን ግን ገልፀዋል።
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን በተመለከተ ግን ሆስፒታሉ በተለማማጅ ሐኪሞቹ ተወካዮች አማካይነት ኤን -95 የተሰኘው ጭምብል ሳይቀር እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው 'አይሰጠንም' የሚሉ ካሉ ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል።
የተለማማጅ ሐኪሞቹ በበሽታው መያዝ ግራ ያጋባቸው ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር አሸናፊ ከሆስፒታሉ ውጪ ጭምብል ሳያደርጉ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን በመናገር "በሆስፒታሉ በርካታ ሐኪሞችና ተለማማጅ ሐኪሞች አሉ። እነዚህ ያውም ደግሞ የኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል ውስጥ የማይሰሩት እንዴት ተያዙ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
ዶክተር አሸናፊ አክለውም የሕክምና ባለሙያዎችም ሆኑ ማንኛውም ሰው ከቤት ውጪ በሚሆንበት ጊዜ የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግ እራሱንም ሆነ ሌሎችንን ለወረርሽኙ ከመጋለጥ ሊታደግ ይችላል ብለዋል።
ዶ/ር አሸናፊ ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ አንድ ሐኪምና አንድ የፅዳት ሠራተኛ በቫይረሱ መያዛቸውን አስታውሰው፤ ሌላ ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ባለሙያዎች እንዳልነበሩ ገልፀዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ ከሆኑት መካከል የሕክምና ባለሙያዎች ከፊት መስመር ላይ ይገኛሉ እንደሚገኙ አመልክቶ፤ በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ከተያዙት ሰዎች መካከል 10 በመቶዎቹ የጤና ሠራተኞች ናቸው ብሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥም ወረርሽኙ መኖሩ ከታወቀ በኋላ ባሉት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ተነግሯል።

















