ከሰሀራ በታች አፍሪካ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ተባለ

አንዲት የጤና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት ከሰሀራ በታች ባሉ አገራት ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መያዛቸውን አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ያለው የጤና ባለሙያዎች የደኅንት መጠበቂያ መገልገያዎችና አልባሳት (ፒፒኢ) በበቂ ሁኔታ ስላልተሟላላቸው ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ጨምሮም አፍሪካ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በጣም እንዳሳሰበው ገልጿል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል የህክምና ባለሙያዎች አስር በመቶውን ይይዛሉ።

በዚህም ሳቢያ የጤና ባለሙያዎች ለአካላዊ እንዲሁም ለሥነ ልቦናዊ ጉዳትም መጋለጣቸው ተነግሯል።

በከፍተኛ ሁኔታ የጤና ባለሙያዎች ለበሽታው የተጋለጡባቸው የአፍሪካ አገራት ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ካሜሩን፣ ዛምቢያ እና ኬንያ መሆናቸውን ድርጅቱ አመልክቷል።

ለወረርሽኙ በዋነኛነት እየተጋለጡ የሚገኙት ነርሶች መሆናቸው የተቀሰው ድርጅቱ፤ እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ለሰዓታት ለህሙማን የህክምና ድጋፍ ይሰጣሉ ብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፤ ከደኅንት መጠበቂያ መገልገያዎች አልባሳት (ፒፒኢ) እጥረት በተጨማሪ ሆስፒታሎች በተገቢው ሁኔታ የጥንቃቄ እርምጃ አለመውሰዳቸው የጤና ባለሙያዎችን ለቫይረሱ ተጋላጭ አድርጓል።

ባለሙያዎቹ ተገቢውን ስልጠና ሳያገኙ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን እንዲያክሙ እንደሚደረጉም ድርጅቱ ተናግሯል።

በአህጉሪቱ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 700 ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን ከ16 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።