በኢትዮጵያ ክረምቱ የኮቪድ-19 ስርጭትን ሊያባብስ ይችላል?

ዝናብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክረምት የተለያዩ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች የሚቀሰቀሱበት ወቅት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ወቅት ጠብቆ የሚመጣ ጉንፋንን ጨምሮ ሌሎችም ህመሞች የሚበረቱበት ጊዜ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኮቪድ-19 ስርጭት ሊጨምር ይችል ይሆን? ስንል በጎንደር ዩኒቨርስቲ የሚሠሩትን የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ቴዎድሮስ ጸጋዬን ጠይቀናል።

ባለሙያው እንደሚሉት፤ በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰቱ የመተንፈሻ አካል ህመሞች በተቀረው ዓለም ቀዝቃዛ በሆነ ወቅት ይከሰታሉ። ይህም በእንግሊዝኛው ዊንተር በሚባለው (ከኅዳር እስከ መጋቢት) ባለው ጊዜ የሚታይ ህመም ነው።

ወደ ኢትዮጵያ አውድ ስንመጣ በቂ ጥናት ባይኖርም፤ ዝናባማ በሆኑ የክረምት ወራት (ከግንቦት እስከ መስከረም) የመተንፈሻ አካል ህመም በብዛት ይስተዋላል።

አብዛኞቹ የመተንፈሻ አካል ህመሞች የሚከሰቱት በቫይረስ ቢሆንም እንደ አለርጂና አስም ያሉ ያለ ቫይረስ የሚመጡ ህመሞችም አሉ። እነዚህ ህመሞች በቅዝቃዜ ወቅት የሚቀሰቀሱት በሦስት ምክንያቶች እንደሆነ ዶክተሩ ያስረዳሉ።

አንደኛው በበሽታው ከሚያዙ ሰዎች ጋር የተያያዘ ምክንያት ነው። “ሰዎች ቀዝቃዛ ወቅት ላይ የመሰባሰብ ባህሪ አላቸው። ይሄ ደግሞ የበሽታዎችን [ኮቪድ-19ኝን ጨምሮ] የመተላለፍ እድል ይጨምረዋል። ቀዝቃዛ አየር ሲኖር የአየር ቧንቧችንም ስሱ ይሆናል” ይላሉ።

የሁሉም ሰው በሽታ የመከላከል አቅም እኩል ስላልሆነ በቀላሉ በቀዝቃዛ አየር ሳቢያ አለርጂ የሚነሳባቸው ሰዎች አሉ። ሰውነት ከውጪ የሚመጣውን ወራሪ ለመከላከል የሙቀት መጠኑን ከፍ ስለሚያደርግ ትኩሳት ይፈጠራል።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ለቫይረሶቹ የሚፈጠረው ምቹ ሁኔታ ነው። ቅዝቃዜ የመተንፈሻ አካልን ሊጎዳ ይችላል። የመተንፈሻ አካል ሲጎዳ ደግሞ ለቫይረስ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

ሦስተኛው የከባቢ አየር ለውጥ ለበሽታ ማጋለጡ ነው። “ይህ ወቅት ቀዝቃዛና ደረቅ ነው፤ ቀዝቃዛና ደረቅ አየር በአየር ቧንቧ ሲያልፍ ጉዳት ይፈጥራል” ሲሉ ዶክተሩ ያብራራሉ።

ክረምት የኮቪድ-19 ስርጭትን ያባብሳል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥናት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ከዚህ ቀደም የታዩ ተመሳሳይ በሽታዎችን በመመርኮዝ ግን ለበሽታው ተጋላጭ የመሆን እድል እንዳለ ይናገራሉ።

“ኮሮናቫይረስ እንደ ሌሎቹ አይነት በሽታዎች ያለ ባህሪ የሚያሳይ ከሆነ ይህ ዝናባማ ወቅት ለበሽታው በጣም አጋላጭ ነው።”

ሌሎች አገሮች ላይ የታውን የቫይረሱን የስርጭት መጠን ብንመለት፤ በቀዝቃዛ ወራት (በሽታው በተከሰተበት ዊንተር ወቅት) ላይ የህሙማን ቁጥር ጨምሯል። ይህ በኢትዮጵያም ሊከሰት እንደሚችል ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

የበሽታዎች ምልክት መመሳሰል

ሌሎች የመተንፈሻ አካል በሽታዎችና ኮቪድ-19 መካከል የምልክት መመሳሰል አለ? ካለስ አንድ ሰው በምን ህመም እንደተያዘ ለማወቅ ምን ማድረግ ነው የሚጠበቅበት? ስንል ዶ/ር ቴዎድሮስን ጠይቀን ነበር።

ባለሙያው እንደሚያስረዱት፤ ቅዝቃዜን ተከትሎ አንዳች የመተንፈሻ አካል ህመም ሲከሰት፤ ሰውነት ከውጪ የሚመጣውን ወራሪ ለመከላከል የሙቀት መጠኑን ከፍ ስለሚያደርግ ትኩሳት ይፈጠራል። ይህም ከኮሮናቫይረስ ምልክቶች አንዱ ነው።

“አለርጂም ቢሆን፣ ኮቪድ-19ኝም ቢሆን፣ ሌላም አይነት ኢንፌክሽን ቢሆን፤ ሰውነት ራሱን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት እንደ ማፈን፣ ማሳል፣ ትኩሳትን የመሳሰሉ ምልክቶች ይፈጠራሉ።”

የመተንፈሻ አካል ህመሞች ምልክት መመሳሰል ካለ፤ ሰዎች በሌላ የመተንፈሻ አካል ወይም በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን እንዴት መለየት ይችላሉ? ወደ ህክምና ተቋምስ መቼ ነው መሄድ ያለባቸው? ሌላው ጥያቄ ነው።

“በሽታዎችን በምልክት ለመለየት መሞከር እንዲሁም ለበሽታዎች ምልክት የተጋነነ ግምት መስጠት ጥሩ አይደለም” ይላሉ ባለሙያው።

የመተንፈሻ አካል ማንኛውም ከውጪ የገባ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ነገር ሲገጥመው በአፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል። የሰዎች የበሽታ መከላከል አቅም የተለያየ ስለሆነ አንዳንዱ በአፋጣኝ ሰውነቱ ላይ የህመም ምልክት ሲታይ ሌላው ሰው ግን ምልክት ላያሳይ ይችላል።

አብዛኞቹ የመተንፈሻ አካል በሽታዎች መካከል መመሳሰል ቢኖርም ጉዳት ከሚያደርሱበት አካል አንጻር የተለያየ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ።

የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪሙ እንደሚያስረዱት፤ አንዳንድ ቫይረሶች የላይኛውን የመተንፈሻ አካል ብቻ ያጠቃሉ። ለምሳሌ ጉንፋን ከአፍንጫ አካባቢ የዘለለ ጉዳት የለውም።

ኮቪድ-19 ደግሞ የታችኛውን የመተንፈሻ አካል ማለትም የሳንባ ክፍል እንደሚያጠቃ ታይቷል። ሳምባ ሲጎዳ ሳል፣ ትንፋሽ ማጠር የመሳሰሉት ምልክቶች ይከሰታሉ።

ከዚያ ውጪ አንዳንዴ ኮሮናቫይረስ ከላይ ያለውን የመተንፈሻ አካል ጎድቶ የጉንፋን አይነት (ጉልህ ያልሆነ) ምልክት ብቻ የሚያሳዩ ሰዎችም አሉ።

አንዳንዴ በሽታውን በምልክት ለመለየት አስቸጋሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው።

በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት በክረምት ለውጥ ያስፈልገዋል?

በዚህ የክረምት ወቅት የወረርሽኙ መስፋፋት የሚጨምርበት እድል ሰፊ ከሆነ፤ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ ማሻሻያ ወይም ለውጥ ማድረግ በተመለከተ ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደሚሉት፤ የተወሰነ ለውጥ ማድረግ ቢያስፈልግም ጉዳዩ ከተለያየ አቅጣጫ መታየት አለበት።

የመጀመሪያው ከግምት መግባት ያለበት ነጥብ ወቅቱ እንደ አለርጂ ያሉ የመተንፈሻ አካል ህመሞች የሚጨምሩበት እንደመሆኑ፤ የበሽታዎች ምልክት ተመሳሳይ ስለሚሆን የምርመራ መጠን ይጨመር ቢባል መመርመሪያ መሣሪያ እጥረት ማስከተሉ ነው።

“በብዛት ምርመራ ተደርጎ ሰዎች የሚገኝባቸው ኮቪድ-19 ሳይሆን ሌላ የመተንፈሻ አካል ህመም ከሆነ የምርመራ አቅምን ማባከን ነው። ምልክት ያሳየውን ሁሉ እንመርምር ብንል አቅማችን ይፈቅዳል?”

ሌላው ነጥብ እምብዛም ጉልህ ምልክት ለማያሳዩ ሰዎች ለኮቪድ-19 ብቻ ተብሎ የተለየ ህክምና ካልተሰጠ፤ መጠኑን መጨመር ያለውን የመመርመር አቅም ማባከን ይሆናል።

በሌላ በኩል ግን ምርመራ ሳይደረግ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሚጎዱ፣ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችም አሉ።

ዶክተሩ ከላይ የተቀመጡትን ነጥቦች በማጣቀስ፤ “በሽታው የሚያስከትለው ጉዳት በአንድ ወገን በሌላ ጎን ደግሞ ያለን አቅም ከግምት ገብተው አማካዩን መንገድ መከተል ያስፈልጋል” ሲሉ ሐሳባቸውን ይገልጻሉ።

ወረርሽኙን በተመለከተ የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይመክራሉ።

በተለይ በክረምት ወቅት ያለው መጠጋጋት የበሽታውን የመተላለፍ እድል ስለሚጨምር ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ቀዝቃዛ አየር የሚጎዳው የመተንፈሻ አካል በወረርሽኙ በቀላሉ የመያዝ እድልን ስለሚጨምርም ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ኮሮና
Banner