ኮሮናቫይረስ ፡ በየደቂቃው በዓለም ዙሪያ ኮቪድ-19 የሚይዛቸውና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ተነስቶ ሰው ከማይኖርበት አንታርክቲክ ውጪ ሁሉንም የዓለማችንን አህጉራትን ያዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሁኑ ወቅት የምድራችን ዋነኛ የጤና ስጋት ሆኗል።
ኮቪድ-19 በመባል የሚታወቀው ይህ ወረርሽኝ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ ሲሆን፤ መጀመሪያ ትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል።
እስካሁን በቫይረሱ ከ186 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተያዙ ሲሆን ከ4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በበሽታው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተያዙና ከሞቱ ከአንድ ዓመት በኋላ የተለያዩ አይነት ክትባቶች ተገኝተው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ለሰዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።
ነገር ግን አሁንም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም፣ የእጅን ንጽህና በተደጋጋሚ መጠበቅና በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በሽታውን ለመከላከል ዋነኞቹ መንገዶች መሆናቸውን ባለሙያዎች አጥብቀው ይመክራሉ።
በየደቂቃው በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት ውስጥ በኮቪድ-19 የሚያዙ፣ ከበሽታው የሚያገግሙና በቫይረሱ ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎችን አሃዝ ቀጥሎ ከተቀመጠው ዝርዝር ላይ ይመልከቱ።
የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ምንድናቸው?
የኮሮናቫይረስ ሁለት ዋነኛ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ወደ ትንፋሽ ማጠር ይወስዳሉ። ደረቅ ሳል ሲባል በጣም ጠንካራ የሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ነው። ከዚህ በፊት ደረቅ ሳል ካለብዎ የኮሮናቫይረስ ሳል በጣም ለየት ያለና ከባድ መሆኑን ማስተዋል ይችላሉ።
ከፍተኛ ትኩሳት የሚባለው ደግሞ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ37.8 ዲግሪ ሴልሲየስ ሲልቅ ነው። ይህ ትኩሳት ሰውነት እንዲግል ወይም ደግሞ ከፍተኛ ብርድና መንቀጥቀጥ እንዲሰማን ያደርጋል።
ከእነዚህ ሁለቱ ዋነኛ ስሜቶች ባለፈ ራስ ምታትና ተቅማጥ አንዳንድ የበሽታው ታማሚዎች ያሳይዋቸው ምልክቶች ናቸው። የማሽተትና የመቅመስ አቅም ማጣትም ምልክቶች ሆነው ተመዝግበዋል።
ምልክቶቹ ቫይረስ ሰውነት ውስጥ በገባ በአምስት ቀናት ሊታዩ ይችላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ምልክቶቹ እስከ 14 ቀናት ድረስ ሳይታዩ ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስረዳል።
















