የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ስላገኘችው ሴት ያውቃሉ?

የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ስላገኘችው ሴት ያውቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ያገኘችው የስኮትላንዳዊ አውቶብስ ሾፌር ልጅ ናት።

ጁን አልሜዳ ትባላለች። ትምህርት ያቋረጠችው በ16 ዓመቷ ነበር።

ዶ/ር ጁን በቫይረስ ምርምር ፈር ቀዳጅ ከሚባሉት አንዷ ናት። የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ተከትሎም ከዓመታት በፊት የሠራቸው ሥራ ዳግም መነጋገሪያ ሆኗል።

ኮቪድ-19 አዲስ ቫይረስ ቢሆንም ከኮሮናቫይረስ አይነቶች አንዱ ነው። የመጀመሪያውን ኮሮናቫይረስ ዶ/ር ጁን ያገኘችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1964፣ በለንደኑ ሴንት ቶማስ ሆስፒታል ውስጥ በሚገኝ ቤተ ሙከራዋ ነበር።

በ1930 የተወለደችው ጁን፤ መደበኛ ትምህርት እምብዛም ሳታገኝ ነበር ከትምህርት ቤት የወጣችው። ነገር ግን ግላስጎው ውስጥ የቤተ ሙከራ ቴክኒሻንነት ሥራ አገኘች።

1954 ላይ ወደ ለንደን አቅንታ ኤንሪኬ አልሜዳ ከሚባል ቬንዝዊላዊ አርቲስት ጋር ትዳር መሰረተች።

የጉንፋን ምርምር

ጥንዶቹ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቶሮንቶ ካናዳ ሄዱ።

ዶ/ር ጁን ማይክሮስኮፕ የመጠቀም ችሎታዋን ያዳበረችው በኦንትርዮ ካንሰር ተቋም እንደሆነ የህክምና ጉዳዮች ጸሐፊው ጆርጅ ዊንተር ይናገራል።

ቫይረሶችን በተሻለ ሁኔታ ማየት የሚቻልበትን መንገድ በመቀየስ ፈር ቀዳጅ የሆነችው፤ ዶክተሯ በ1964 ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተመልሳ በሴንት ቶማስ ሆስፒታል ትሠራ ጀመር። (ይህ ሆስፒታል የዩኬው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ የታከሙበት ነው።)

ዶ/ር ጁን በወቅቱ በጉንፋን ላይ ይመራመር ከነበረው ዶ/ር ዴቪድ ታይሮል ጋር ተጣመረች።

ዶ/ር ዴቪድ ከፍቃደኛ ሰዎች የአፍንጫ ፈሳሽ ናሙና በመውሰድ ከጉንፋን ጋር የተያያዙ ጥቂት ቫይረሶችን ለማግኘት ችሎ ነበር። ሁሉንም የቫይረስ አይነቶች ግን አላገኘም ነበር።

ከናሙናዎቹ አንዱ በ1960 ከነበረ አዳሪ ትምህርት ቤት የተወሰደ፤ B814 የሚል መጠሪያ የተሰጠው ነበር።

ዶ/ር ዴቪድ ይህ ናሙና በኤሌክትሮን ማይክሮስኮፕ ይታይ እንደሆነ ዶ/ር ጁንን ጠየቀ። ዶክተሯም የቫይረሱን ቅንጣቶች አይታ እንደ ኢንፍሉዌንዛን ቢመስልም ኢንፍሉዌንዛ ያልሆነ ቫይረስ መሆኑን ገለጸች።

ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው የሰው ኮሮናቫይረስ ነው።

ኮሮናቫይረስ

የህክምና ጉዳዮች ጸሐፊው ጆርጅ እንደሚለው፤ ዶ/ር ጁን የአይጦች ሄፒታይተስ እና ዶሮዎችን የሚያጠቃ ብሮንካይትስ ላይ ስትመራመር ተመሳሳይ የቫይረስ ቅንጣቶች አግኝታለች።

ሆኖም ጥናቷ በሙያ አጋሮቿ መጽሔት ላይ ለመውጣት ተቀባይነት አላገኘም ነበር። የመፍሔቱ ዳኞች፤ ተመራማሪዋ የተጠቀመቻቸው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ቅንጣቾች ምስሎች መጥፎ ናቸው ብለው ነበር ጥናቱን ውድቅ ያደረጉት።

በ1965 ግን ጥናቱ በ ‘ብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል’ ታተመ። ዶ/ር ጁን የተጠቀመችው ምስል ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ‘ጆርናል ኦፍ ጄነራል ቫይሮሎጂ’ በተባለ መጽሔት ታትሟል።

ኮሮናቫይረስ የሚለውን ስያሜ ያወጡት ዶ/ር ጁን፣ ዶ/ር ዴቪድ እና የወቅቱ የሴንት ቶማስ ኃላፊ ፕሮፌሰር ቶኒ ዋተርሰን ናቸው።

የቫይረሱን ምስል ሲመለከቱ፤ እንደ ጨረር ያለ ነገር እንደከበበው ስላዩ ኮሮናቫይረስ ብለውታል።

ጁን፤ ዶክትሬቷን ያገኘችው ለንደን ውስጥ ነበር።

በመጨረሻም ‘ዌልካም ኢንስቲትዩት’ ውስጥ ስትሠራ የተለያዩ ቫይረሶችን በመለየት አስመዝግባለች።

ከዚህ ተቋም ከለቀቀች በኋላ፤ ዩጋ መምህርት ሆና ነበር። በ1980ዎቹ ግን ወደ ህክምናው ዘርፍ ተመልሳ፤ የኤችአይቪ ቫይረስ ምስሎችን በማንሳት አማካሪ ሆናለች።

ዶክተሯ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው በ2007፣ በ77 ዓመቷ ነው።

ሕይወቷ ባለፈ በ13 ዓመቱ ለሥራዋ ተገቢውን እውቅና እያገኘች ነው። ዛሬ ላይ የመላው ዓለም ራስ ምታት የሆነውን ቫይረስ ለመገንዘብ የዶ/ር ጁን ምርምር አስፈላጊ ነበር።

ኮሮና
Banner