ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መንግሥታት ከተሜውን ከኮሮናቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዲታደጉ ጥሪ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, EYERUSALEM JIREGNA
የኮሮናቫይረስ መዛመትን ተከትሎ የአፍሪካ አገራት በከተሞች ላይ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የምጣኔ ሃብታቸውን ስሱ ጎን ከግምት ውስጥ ያስገባና ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የብዙ አፍሪካ አገራት የምጣኔ ሃብት እድገት አንቀሳቃሽ ኃይሎች ከተሞች እንደመሆናቸው መጠን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ሁኔታዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ የኮሚሽኑ የሥዓተ ፆታ፣ ድህነትና ማኅበራዊ ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ቶኮዚ ሌሩዝቪድዚ ገልፀዋል።
የአፍሪካ ከተሞች 600 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖሩባበቸውና የአህጉሪቱንም 50 በመቶ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት (ጂዲፒን) አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ናቸው።
በቦትስዋና፣ ኡጋንዳ፣ ቱኒዝያና፣ ኬንያ ባሉ አገራት ደግሞ ሰባ በመቶውን አጠቃላይ ብሔራዊ ምርን ይሸፍናሉ። የምጣኔ ሃብት አስተፅኦዋቸውም ካላቸው የሕዝብ ቁጥር ይበልጣል።
ከኮሮናቫይረስ መዛመት ጋር ተያይዞም በሚወሰዱ እርምጃዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከተሜዎች ለሥራ አጥነት ይጋለጣሉ። በተለይም የአገራቱ የምጣኑ ሃብት መሰረት የሆኑት ማኑፋክቸሪንግና የአገልግሉት ዘርፎች መሽመድመድ ያጋጥማቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ከተሞችን መሰረት ያደረጉት እነዚህ ዘርፎች 64 በመቶ የሚሆነውን አጠቃላይ ብሔራዊ ምር የሚሸፍኑና ከፍተኛ የሰው ኃይልም ቀጣሪ ናቸው።
በተለይም ከሰሜን አፍሪካ ውጭ ያሉ 250 ሚሊዮን የሚሆኑ በኢመደበኛ የተቀጠሩ አፍሪካውያን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ መግለጫው አመልክቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ከተሞች ውስጥ መቀመጫቸውን ያደረጉ የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ጫና ውስጥ መግባታቸው አይቀርም ተብሏል።
በተለይም ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች የአህጉሪቷ 80 በመቶ ቀጣሪ እንደመሆናቸው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱትም እነሱ እንደሚሆኑ መግለጫው አሳይቷል።
ይህም ሁኔታ መሰረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲጨምር በር ይከፍታል፤ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞችም ላይ እንደተስተዋለው በመቶ እጅ ምግብ ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።
አገራቱ የካፒታል ወጪያቸው በዓለም አሉ ከሚባሉት አገራት በጣም ዝቅተኛ መሆን፣ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ያላቸው አቅም እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ተደራራቢ ችግር ሊያስከትል ይችላል ብሏል።
የተለያዩ የከተማ አስተዳደሮች የነበራቸውን በጀትም ለድንገተኛ የኮሮናቫይረስ ምላሽ እንዲሁም ለጤና ሽፋን ስለሚያውሉትም የገንዘብ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም።
እናም በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ የከተማ አስተዳደሮች የችግሩ ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው፣ የሚያስተዳድሩትን ሕዝብም ሆነ አካባቢ የመረዳት አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ፣ ማኅበረሰቡን በቀጥታ ማስተባበርም ስለሚችሉ ግልፅነትና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ብሏል።
መግለጫው አክሎም ከድንገተኛ የጤና ሽፋንና ሰብአዊ ድጋፎች በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን መጋፈጥ ያስችላቸው ዘንድ በተለያየ ደረጃ መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥቷል።
ከእነዚህም ውስጥ ኮሚሽኑ የከተሞች ኢኮኖሚያ እንዲያገግም መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች መካከል በተለያየ ደረጃ ያሉ የከተማና የአካባቢ አስተዳደሮችን ማጠናከር፣ ለጥቃቅን፣ አነስተኛ፣ መካከለኛ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ሥራ አጥ እንዳይሆኑ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የገንዘብ እፎይታ፣ በኢመደበኛ ተቀጥረው ለሚሰሩ የማኅበራዊ ጥበቃ ድጋፎች ያስፈልጋል ተብሏል።
ረዘም ባለ ጊዜ ደግሞ የከተሞች ምጣኔ ሃብት ሙሉ በሙሉ እንዲያገግም ኢንቨስትመንቶችን መጨመር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
ምንም እንኳን መግለጫው ከተሞች ላይ ያለውን ተግባር ቅድሚያ ይሰጥ ቢልም በአጠቃላይ አገራዊና ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ከግምት ውስጥ ሊገቡ እንደሚገባ አስምሯል።














