ኮሮናቫይረስ ሁለቴ ሊይዘን ይችላል?

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለ ኮሮናቫይረስ በርካታ ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ነው። ቫይረሱ አንዴ ከያዘን በኋላ በድጋሚ ሊይዘን ይችላል? በበሽታው አንዳንዶች ለምን ከሌሎች በባሰ ይጠቃሉ? ወረርሽኙ ሁሌም ክረምት ላይ ይከሰት ይሆን? ክትባት ቫይረሱን ለመከላከል ውጤታማ ይሆናል? በሽታውን እንዴት በቁጥጥር ስር አውለን ወደፊት እንቀጥላለን? በሽታውን የመከላከል አቅም አዳብረዋል የሚል ማረጋገጫ ያገኙ ሰዎች ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ ይችሉ ይሆን? ወዘተ. . .

ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል በሽታውን የመከላከል አቅም የማዳበር (ኢሚዩኒቲ) ጉዳይ ዋነኛው ቢሆንም አጥጋቢ ምላሽ የለውም።

ሰውነታችን ኮሮናቫይረስን የመከላከል አቅም እንዴት ያዳብራል?

በሽታን የመከላከል አቅም ሁለት ደረጃ አለው። የመጀመሪያው ሰውነት ወራሪ ነገር ሲገጥመው በመዋጋት የሚሰጠው ምላሽ ሲሆን፤ ‘ኢኔት ኢሚዩን ሪስፖንስ’ ይባላል።

በዚህ ወቅት ሰውነት ኬሚካል ያመነጫል። ነጭ የደም ሕዋሳትም ጉዳት የደረሰበትን ሕዋስ ያጠፋሉ።

ይህ ለኮሮናቫይረስ ብቻ ሳይሆን ለማንኛውን በሽታ ሰውነት የሚሰጠው ምላሽ ነው። ኮሮናቫይረስ እንዳይዘን የማድረግ አቅምም የለውም።

ሰውነታችን እንደ ኮሮናቫይረስ አይነት በሽታ ሲገጥመው የሚሰጠው የመከላከያ ምላሽ ‘አዳፕቲቭ ኢምዩን ሪስፖንስ’ ይባላል።

ቫይረሱ ላይ ያነጣጠሩ ፀረ እንግዳ አካላት (አንቲቦዲስ) የሚፈጠሩበት ሂደት ሲሆን፤ በቫይረሱ የተጠቁ ሕዋሳትን ለይቶ የሚያጠቃ ‘ቲ ሴል’ ያመነጫል።

ሰውነት ኮሮናቫይረስ ላይ ያነጣጠሩ ፀረ እንግዳ አካላት ለማመንጨት እስከ አስር ቀን እንደሚወስድበት ጥናቶች ያሳያሉ። በሽታው ክፉኛ ያጠቃቸው ሰዎች ጠንካራ የመከላከል አቅም ያዳብራሉ።

ይሄኛው በሽታን የመከላከል ምላሽ (አዳፕቲቭ ኢምዩን ሪስፖንስ) በጣም ጠንካራ ከሆነ በቀጣይ በበሽታው ላለመያዝ ይረዳል።

የኮቪድ-19 መጠነኛ ምልክት የታየባቸው ወይም ከነጭራሹ ምልክት ያላሳዩ ሰዎች፤ በሽታውን በበቂ ሁኔታ መከላከል የሚያስችል አቅም ስለማዳበራቸው የታወቀ ነገር የለም።

በሽታን የመከላከል አቅም ምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

ሰውነታችን አንዳንድ በሽታዎችን ያስታውሳል አንዳንዶቹን ደግሞ ይረሳል።

ለምሳሴ ሰውነታችን ኩፍኝን ፈጽሞ አይረሳም፤ ስለዚህ በሕይወት ዘመናችን ከአንድ ጊዜ በላይ ኩፍኝ አይዘንም።

አንዳንድ በሽታዎችን ግን ሰውነታችን ይዘነጋቸዋል። እንደ ምሳሌ የሕጻናት መተንፈሻ አካል በሽታዎችን ማየት እንችላለን። ልጆች በተደጋጋሚ በእነዚህ በሽታዎች ይያዛሉ።

አዲሱ ኮሮናቫይረስ (Sars-CoV-2) መሰራጨት የጀመረው በቅርቡ ስለሆነ የሰው ልጅ ለምን ያህል ጊዜ በሽታውን የመከላክለ አቅም እንደሚያዳብር ገና አልታወቀም።

ግን የሌሎች ስድስት አይነት ኮሮናቫይረሶችን ባህሪ በማየት መገመት ይቻላል።

ከቫይረሱ አይነቶች አራቱ፤ እንደ ጉንፋን አይነት ምልክት ያላቸው ሲሆን፤ በሽታን የመከላከል አቅም የሚገኘውም ለአጭር ጊዜ ነው። ስለዚህም አንዳንዶች በዓመት ሁለቴ ሊያዙ ይችላሉ።

ከኮሮናቫይረስ አይነቶች ሁለቱ እጅግ አደገኛ ናቸው። ሳርስ ወይም ‘አክዩት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም’ እና መርስ ወይም ‘ሚድል ኢስት ሪስፓይራቶሪ ሲንድረም’ የሚያስከትሉት እኒህ ናቸው።

ለነዚህ በሽታዎች የሰው ልጆች ፀረ እንግዳ አካላት (አንቲቦዲስ) የሚያመርቱትም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው።

የህክምና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ፖል ሀንተር እንደሚሉት፤ ጥያቄው መሆን ያለበት በሽታውን የመከላከል አቅም እናዳብራለን? የሚለው ሳይሆን በሽታውን የመከላከል አቅም ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? የሚለው ነው ይላሉ።

“ለእድሜ ልክ የሚሆን በሽታ የመከላከል አቅም እንደማናዳብር እርግጥ ነው። የሳርስ ፀረ እንግዳ አካላት ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው እስከ ሁለት ዓመት የሚቆይ በሽታ የመከላከል አቅም ሊገነባ ይችላል።”

አንድ ሰው በበሽታው በድጋሚ ቢያዝም እንደ መጀመሪያው ጊዜ አይጠናበትም።

በሽታው ሁለቴ ይዞን ይሆን?

በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለቴ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ተዘግቧል።

አንዳንዶቹ ዳግመኛ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ቫይረሱ በሰውነታቸው ውስጥ ተደብቆ ከጊዜ በኋላ ዳግመኛ በሽታው የተገኘባቸው ናቸው።

ከበሽታው እንዳገገሙ ከተነገራቸው ሰዎች መካከል ትክክለኛ ምርመራ ሳይደረግ ‘አገግማችኋል’ የተባሉ እንዳሉም ተመራማሪዎች ይስማማሉ።

የሰው ልጆች በሽታውን የመከላከል አቅም አዳብረው እንደሆነ ለማወቅ ሆነ ተብሎ በቫይረሱ ሁለቴ እንዲያዙ ባይደረግም፤ ዝንጀሮዎችን በሽታውን በማስያዝ ጥናት እየተካሄደ ነው።

ዝንጀሮዎቹ በሦስት ሳምንት ልዩነት ሁለቴ በበሽታው እንዲያዙ ተደርጎ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበሽታው ምልክት አልታየባቸውም።

‘አንቲቦዲስ’ ካለን በሽታውን መከላከል እንችላለን?

ስለዚህ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። አንዳንድ አገሮች በሽታውን የመከላከል አቅም አዳብረዋል ላሏቸው ሰዎች ማረጋገጫ ‘ፓስፖርት’ መስጠታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት የማይደግፈውም ለዚህ ነው።

ፀረ እንግዳ አካላት እንዳላቸው የተረጋገጠ ሰዎች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያደረጉ አገሮች አሉ። በተለይም ለአረጋውያን እንክብካቤ ለሚሰጡና ለህክምና ባለሙያዎች ይህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ሆኖም ግን በሁሉም ህሙማን ላይ ፀረ እንግዳ አካላት ቢገኝም ሁሉም አኩል አይደሉም። ኮሮናቫይረስን መግታት የሚችሉት ‘ኒውትራላይዚንግ አንቲቦዲስ’ የሚባሉት ናቸው።

ቻይና ውስጥ ከቫይረሱ ባገገሙ 175 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ የ30 በመቶው ‘ኒውትራላይዚንግ አንቲቦዲስ’ ዝቅተኛ መሆኑን አሳይቷል።

በተጨማሪም በ ‘አንቲቦዲስ’ ሰውነታችን ቢጠበቅም እንኳን፤ ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው ልናስተላልፍ እንችላለን።

በሽታን የመከላከል አቅም ጠቃሚ ነው?

በሽታን የመከላከል አቅም ጉዳይ በኮቪድ-19 በተደጋጋሚ እንያዛለን? ከተያዝንስ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም በሽታውን የመከላከል አቅም ካዳበሩ የበሽታውን አደገኛነት ይቀንሰዋል።

ስለ ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅም ግንዛቤ ካዳበርን ማን ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆነ፣ በሽታውን ሊያስተላልፍ የሚችለው ማን እንደሚሆን ለማወቅ ይረዳል። እንቅስቃሴ ላይ የተጣለውን ገደብ ለማላላትም ያግዛል።

በእርግጥ ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ በሽታን የመከላከል አቅም ማዳበር ከባድ ነው። ይህም ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ሊያከብደው ወይም ክትባቱ በምን ያህል ጊዜ ልዩነት መወሰድ አለበት የሚለውን ሊለውጠው ይችላል።

አንድ ሰው በበሽው ተይዞ አልያም ክትባት ካገኘ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ የሚቆይ በሽታን የመከላከል አቅም ማዳበር ይችላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲገኝ የቫይረሱን ስርጭት መግታት የሚቻልበትንም መንገድ ያመላክታል።

ከላይ የተነሱት ጥያቄዎች ገና መልስ ያልተገኘላቸው ናቸው።

ኮሮና