ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮችን እየረዳ ያለው ቢሊየነር ጃክ ማ ማነው?

ጃክ ማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና ቁጥር አንድ ባለ ሀብት ነው። ባለፈው ወር የትዊተር ገጽ ከፍቶ ከጻፋቸው መካከል “አንድ ዓለም አንድ ትግል” “በጋራ እናሸንፋለን” የሚሉት ይጠቀሳሉ።

ቢልየነሩ ጃክ ማ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ150 አገሮች የህክምና ቁሳቁስ እርዳታ አድርጓል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ ቬንትሌተርም ሰትቷል።

ሆኖም ድርጊቱ ለተቺዎቹም ለደጋፊዎቹም ግልጽ የሆነ አይመስልም። የጃክ ማ ቸርነት የኮምኒስት ቻይና ነጸብራቅ ነው? ወይስ ግላዊ ጥረቱ ለፓርቲ ፕሮፖጋንዳ እየዋለ ይሆን?

በእርግጥ እርዳታ የሚሰጣቸውን አገሮች ሲመርጥ የቻይናን ዲፕሎማሲ ተመርኩዞ ነው። ምናልባት ግን የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በድርጊቱ ሳይቀኑ አልቀሩም።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ድጋፍ እናደርጋለን ካሉ የቴክኖሎጂ ሰዎች መካከል የትዊተር መስራች ጃክ ዶርሲ ይገኝበታል፤ አንድ ቢልየን ዶላር ሰጥቷል።

ካንዲድ የተባለ ለኮቪድ-19 የተሰጡ እርዳታዎችን በደረጃ የሚያስቀምጥ ተቋም፤ የጃክ ማን አሊባባ 12ኛ ቦታ አስቀምጦታል። ይህም ቁሳቁስ ሳይቆጠር፣ ከገንዘብ እርዳታ አንጻር ብቻ ነው።

እንደ ጃክ ማ የህክምና ቁሳቁስ ለሚያስፈልጋቸው አገሮች በስፋት ማከፋፈል የቻለ የለም። ካለፈው ወር መባቻ ጀምሮ ወደ አፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ እና ላቲን አሜሪካ ቁሳቁሶቹ ተልከዋል።

ባለሀብቱ ለክትባት ምርምር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብም ሰጥቷል። በትውልድ ቀዬው ዢዣንግ የሚገኙ የህክምና ጥናቶች በ16 ቋንቋዎች እንዲተረጎሙም አድርጓል።

የጃክ ማን ግለ ታሪክ የጻፈው ደንከን ክላርክ “የቻይና እርዳታ ሰጪ አውሮፕላን ከሃንግዡ አዲስ አበባ የመላክ አቅሙም ገንዘቡም አለው” ይላል።

የብዙዎች ወዳጅ?

ጃክ ማ ከተወዳጅ የእንግሊዘኛ መምህርነት ትልቁን የቻይና የቴክኖሎጂ ድርጅት ወደማቋቋም የተሸጋገረ ሰው ነው። ‘የምሥራቁ ዓለም አማዞን’ የተባለውን አሊባባ የጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1999 ሃንግዡ ከሚገኘው አነስተኛ ቤቱ ውስጥ ነበር።

አሊባባ አሁን ላይ የዓለም ሁለተኛ ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ማዕከል በሆነችው ቻይና ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆኗል። በቻይና የድረ ገጽ ግብይት፣ በባንክና በመዝናኛ ዘርፍ ቁልፍ ቦታ አለው።

መስራቹ ጃክ ማ ደግሞ ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ አለው። ከቻይና ኃያላን አንዱም ነው።

ጃክ ማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሦስት ዓመት በፊት ከአሊባባ መሪነት ወርዶ ትኩረቱን በጎ አድራጎት ላይ ቢያደርግም፤ አሁንም ከድርጅቱ ቦርድ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ጃክ ማ ነው።

ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት የሚያደርገው ድጋፍ የቻይና ፓርቲን ደንብ የተከተለ ይመስላል። የቻይና ጎረቤት እና ተፎካካሪ ከሆነችው ታይዋን ጋር ይፋዊ ግንኙነት ላላቸው አገሮች ድጎማ አልተሰጠም።

ጃክ ማ ትዊተር ላይ ለ20 የላቲን አሜሪካ አገሮች እርዳታ እሰጣለሁ ብሏል። ታይዋንን የሚደግፉ እንደ ሄይቲ እና ሆንዱረስ ያሉ ግዛቶች የህክምና ቁሳቁስ እንደሚፈልጉ ቢያሳውቁም፤ ባለሀብቱ ከረዳቸው 150 አገሮች ዝርዝር ውስጥ የሉም።

በእርግጥ የባለሀብቱ የተራድኦ ድርጅት ድጎማ የሚደረግላቸውን አገሮች ዝርዝር ይፋ ማውጣት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

ከኩባ እና ከኤርትራ ውጪ እርዳታ የተላከላቸው አገሮች ያለ ምንም ችግር ነው የደረሳቸው።

ይህ ቸርነት ባለሀብቱን ዝነኛ አድርጎታል። የቻይና ሚዲያ የጃክ ማን ስም ከአገሪቱ መሪ ዢ ዢፒንግ ባልተናነሰ ሁኔታ ደጋግመው ሲጠሩም ይደመጣል።

እንዲያውም ዢ ዢፒንግ ወረርሽኙ ከቁጥጥር ሳይወጣ በፊት ማስቆም ይችሉ ነበር ተብለው ሲተቹ፤ ጃክ ማ በአንጻሩ እየተሞገሰ ነው።

የቻይና መንግሥት በኮቪድ-19 ክፉኛ ወደተጠቁ አገሮች የህክምና ባለሙያዎች እየላከ ነው። በተለይም የአውሮፓ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

ሆኖም ግን ቻይና የላከቻቸው የህክምና መሣሪያዎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አይችሉም ተብሎ አገሪቱ ተተችታለች።

‘’የቻይና አፍሪካ ፕሮጀት’ ድረ ገጽ ዋና አርታኢ ኤሪክ ኦላንደር እንደሚለው፤ የጃክ ማ ድጎማ በመላው አፍሪካ እንዲመሰገን አድርጎታል።

ባለሀብቱ መላው አፍሪካን እጎበኛለሁ ብሎ ቃል መግባቱ ይታወሳል። ከአሊባባ ኃላፊነቱ ከወረደ በኋላ ወደ አህጉሪቱ አዘውትሮ እየመጣም ነው።

ከወራት በፊት አዲስ አበባ ተገኝቶ እንደነበርም ይታወሳል።

ጃክ ማ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጃክ ማ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር

ዢ ዢፒንግ ጃክ ማን ይቀየሙት ይሆን?

የቻይናው ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ሁሌም መሞገስ ይፈልጋሉ። የሚቀናቀናቸውን ሰው መንግሥታቸው ኢላማ ሲያደርገም ታይቷል።

ከዚህ ቀደም ታዋቂ ተዋንያን፣ ዜና አንባቢዎች፣ ቢልየነር በጎ አድራጊዎች ዘለግ ላለ ጊዜ ከሕዝብ እይታ ጠፍተው ነበር። አንዳንዶቹ ታስረዋል፤ የተቀሩት ደግሞ ፓርቲውን ለመደግፍ ቃል ከገቡ በኋላ ከእገታ ተለቀዋል።

ጃክ ማ 2018 ላይ ከአሊባባ መሪነት የተነሳው ከኮምኒስት ፓርቲው በላይ እየገነነ ይሄዳል በሚል ፍራቻ ነው የሚል ጭምጭምታ እንደተሰማ አጥኚዋ አሽሊ ፌንግ ትናገራለች።

ባለ ሀብቱ ግን በመንግሥት ግፊት ስልጣኑን እንዳልለቀቀ ተናግሯል።

2017 ላይ ጃክ ማ ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በትራምፕ ህንጻ ተገናኝተው ነበር። ዢ ዢፒንግ ግን ከትራም ጋር የተገናኙት ከወራት በኋላ ነበር።

የባለሀብቱን ግለ ታሪክ የጻፈው ደንከን እንደሚለው፤ ጃክ ማ በወቅቱ ፈጣን እርምጃ ነበር የወሰደው።

“ጃክ ማ በንግዱ ዘርፍ ለስለስ ያለ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ነው። ፓርቲው እንዲህ አይነት ሚና የሚጫወቱ ሰዎች ስለሚስያቀኑት ነገሩ አስፈሪ ነው” ይላል።

በእርግጥ ጃክ ማ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለ አንስቶ የኮምኒስት ፓርቲው አባል ነው። ነገር ግን “አሊባባ ፓርቲውን ቢወደውም ከፓርቲው ጋር በትዳር አይጣመርም” የሚል አዝማሚያ አለው።

ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ድጎማ ሲያደርግ የፓርቲውን ይሁንታ ባይጠይቅም፤ የቻይና አምባሳደሮች እርዳታው በተላከባቸው አገሮች አውሮፕላና ማረፊያ በመገኘት አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ነው።

ቻይና ታዋቂ ሰው እየፈለገች ስለሆነ፤ ከዚህ ቀደም ታዋቂነታቸው ችግር ውስጥ የከተታቸው ቻይናውያን የገጠማቸው አይነት እጣ ፈንታ ባለሀብቱ አይገጥመው ይሆናል።

ኤሪክ ኦላንደር እንደሚለው፤ ጃክ ማ ለአፍሪካ የገባውን ቃል አክብሯል። ብዙ ታዋቂ ሰዎች እናደርጋለን ያሉትን ሳይፈጽሙ መቅረታቸውን እንደ ማሳያም ይጠቅሳል።

ደንከን በበኩሉ፤ በአሊባባ ትርፋማነት ምክንያት ጃክ ማ ለቻይና ጠቃሚ ሰው ነው። ዓለም አቀፍ እውቅናውን እንዲሁም ከምድራችን ባለሀብቶች ጋር ያለውን ትስስር ተጠቅማ ቻይና ገጽታዋን ልትገነባም ትችላለች።

ካንዲድ በተባለውና ለኮቪድ-19 የተሰጡ እርዳታዎችን በደረጃ በሚያስቀምጠው የአሜሪካ ተቋም ውስጥ የሚሠራው አንድሪው ግራቦይስ እንደሚናገረው፤ የጃክ ማ ልገሳ ቻይናንም እየጠቀማት ነው።

“ቀድሞ አሜሪካ ትወስድ የነበረውን የድጋፍ መሪነት ሚና ቻይና እየወሰደች ነው” ይላል።

ኮሮና
Banner