ኮሮናቫይረስ፡ በአዲስ አበባ ሁለት ወጣቶች በጥይት ተመትተውበታል በተባለው ክስተት የሆነው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Sintayehu Chekol
በአዲስ አበባ ከተማ፣ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሁለት ወጣቶች መመታታቸው እና ከሁለቱ የአንደኛው ህይወት ማለፉ በተለያዩ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የሚሽከረከር ዜና ሆኗል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ተቃዋሚው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮችም በተጎጂ ቤተሰቦች መኖሪያ በመገኘት ከቤተሰቦቹ አባላት ጋር መነጋገራቸውን እንዲሁ በማኅበራዊ የብዙሃን መገናኛዎች የተሰራጩ ፎቶዎች አመላክተዋል።
በትክክል የተከናወነው ምንድን ነው ሲል ቢቢሲ ከሁለቱ ወጣቶች የአንደኛውን አባት አቶ ደርቡሽ ተስፋዬን አነጋግሯል።
መቼ እና የት?
አቶ ድርቡሽ መጋቢት ሃያ ስድስት ቀን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ከሩሲያ ኤምባሲ ጀርባ አካባቢ በሚገኘው የመኖሪያ አካባቢያቸው አመሻሽ ለአንድ ሰዓት ሩብ ጉዳይ አካባቢ ተኩስ መሰማቱን ይገልፃሉ።
"ተኩስ የተሰማበት ቦታ ላይ ልጆች ወድቀዋል፤ የአንተ ልጅ አቤል እና ሚኪያስ [ደምስ] በጥይት ተመትተዋል አሉኝ። ወዲያው እንደሰማን ከቤት ወጣን" ይላሉ አቶ ድርቡሽ።
ከቤት ወጥተው ተኩስ ወደተሰማበት አካባቢ ሲቀርቡም በርካታ የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው እንደነበሩ ይናገራሉ።
ሁለቱ ወጣቶች ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል መወሰዳቸውን እና እርሳቸው በሆስፒታሉ ሲደርሱ የሚኪያስ ሕይወት ማለፉ፣ የእርሳቸው ልጅ አቤል ግን በሕይወት እንደሚገኝ እና የቀዶ ጥገና እየተደረገለት መሆኑ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ ተናገረዋል።
"ሐኪም እንዳለኝ [ጥይቱ] በቀኙ በኩል ከጡቱ በታች ገብቶ፣ በግራ በኩል ጉበቱን ሦስት ሳንቲ ሜትር በስቶ ከዚያ የእጁን መጋጠሚያ ላይ ነው የመታው።"
ከዓለም አቀፉ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ጋር በተገናኘ አቤል ከቀዶ ጥገናው ከሦስት ቀናት በኋላ ከሆስፒታል ወጥቶ በአሁኑ ወቅት ቤት ውስጥ "ቤተሰብ በሆነች ነርስ" ነው እየታከመ ያለው- እንደአቶ ደርቡሽ ገለፃ። "አሁንም አልጋ ላይ ነው፤ ምንም መንቀሳቀስ አይችልም። ራሱን ግን ያውቃል፤ ምግብም ፈሳሽም ይወስዳል።"
መነሻ ምክንያት
አቤል ድርቡሽ እና ሚኪያስ ደምስ የቅርብ ጓደኛሞች ነበሩ፤ ሁለቱም የሃያ አንድ ዓመት ወጣቶች ናቸው- እንደ አቶ ድርቡሽ።
እርሳቸው እንደሚሉት የክስተቱ መነሻ አቤል የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጠውን የአስር ዓመት ልጅ መጠጥ የሚሸጥበት ቤት ውስጥ በማግኘቱ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ ልጁን ይዞት ከመጣው ወጣት ጋር ንትርክ ውስጥ መግባቱ ነው።
ይሁንና በሁለቱ ወጣቶች መካከል ያለው ግጭት ረግቦ ሁለቱም በየፊናቸው መሄድ ጀምረው ነበር ይላሉ።
የፖሊስ ምላሽ
ከክስተቱ በኋላ የወረዳው ፖሊስ ድርጊቱን መመርመር መጀመሩን እና መርማሪም ወደቤታቸው መምጣቱን ነገር ግን- ምናልባትም እነርሱ ሆስፒታል ሄደው ስለነበር- ከመርማሪው ጋር ያለመገናኘታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል አቶ ድርቡሽ።
ይሁንና ማንም መጥቶ ሳያናገረኝ ቀናት ተቆጥረዋል ይላሉ።
ከቀናት በኋላ "የሟች [ሚኪያስ] አባት እና እኔ ወደ ወንጀል ምርመራ [ክፍል] ሄደን ጠየቅን። የምርመራ ክፍል ሹሙ ሥራ በዝቶብን ነው አለን [እና ] ሰው አዘዘልን። መርማሪውን ስንደውልለት ዛሬ አይመቸኝም ነገ እመጣለሁ አለ። በማግስቱ መጥቶ ቃል ተቀበለን" የሚሉት አቶ ድርቡሽ ከዚያ በኋላ ግን "ሰውዬው ይያዝ [አይያዝ]፣ ማን እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጥቃት አድራሹ ታውቆ፣ ችሎትም የሚቀርብ ከሆነ በስፍራው ለመገኘት ጥያቄ ቢያቀርቡም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ችሎት የለም መባላቸውን ገልፀዋል።
"ድፍንፍን አደርጉብን"
ቢቢሲ ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ስልክ ቢደውልም ምላሽ ማግኘት ሳይሳካለት ቀርቷል። የፌዴራል ፖሊስ የኮምኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ጀይላን አብዲ በበኩላቸው በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል።













