ኮሮናቫይረስ : ስለቫይረሱ ከሚናፈሱት በጥቂቱ፣ የአሪቲ መድኃኒትነት፣ የአለምን ህዝብ መቆጣጠሪያ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቢቢሲ ጋዜጠኞች ቡድን ከሰሞኑ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ማህበራዊ ሚዲያውን ያጥለቀለቁትንና ሃሰተኛ ወይም መሰረት የሌላቸውን መረጃዎች ሰብስቧል።
የተዋናዩ ዘሮክ የገንዘብ ስጦታ
አሜሪካዊው ተዋናይ ድዋይን ጆንሰን ወይም ዘሮክ በኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ ምክንያት ለተቸገሩ ሰዎች ገንዘብ ይሰጣል የሚል መረጃ በሺዎች በሚቆጠሩ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተጋርቷል።
ከፍተኛ ገንዘብ እንደሆነም የተገለፀ ሲሆን በበርካታ ቋንቋዎችም ተተርጉሟል። አንዳንዶቹ ቪዲዮዎችም ሆነ ፎቶዎች እንደገና በማስመሰል ጥበብ ወይም በፎቶ ሾፕ የተሰሩ ናቸው።
ይህንንም ገንዘብ ለማሸነፍ ውድድር ተዘጋጅቷል የሚል መረጃም አብሮ የወጣ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች ከሽልማቱ ዝርዝር ውስጥ ከስማቸው የመጀመሪያ ፊደል ጋር የሚመሳሰል መምረጥ ይኖርባቸዋል።
አንዳንዶች በአስገራሚ ሁኔታ የባንክ መረጃዎቻቸውን በፌስቡክ አስተያየት መስጫ ያሰፈሩ ሲሆን፤ ለእርዳታም የተማፀኑም አልታጡም።
ሽልማቶቻችሁን ኑ ውሰዱ በሚል የቀጠለ ሲሆን አንደኛው ቪዲዮ ላይ አንድ ግለሰብ ከፍተኛ ገንዘብ ሲቀበል ያሳያል። ይህንንም ቪዲዮ አራት ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።
ነገር ግን ቢቢሲ ማረጋገጥ እንደቻለው ቪዲዮው የሮክ አይደለም፤ የገንዘብ ሽልማቱም ማጭበርበር ነው።
በፕሬዚዳንቱ ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል የተባለው መድኃኒት
የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የኮሮናቫይረስን የሚከላከል ወይም የሚያድን መድኃኒት የለም ቢልም የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ግን ኮሮናቫይረስን የሚከላከል መፈወሻ አግኝቻለሁ ብለዋል።

ከዕፅዋት ተገኘ የተባለው መድኃኒት ከአርቲሜዥያ ወይም በኢትዮጵያውያን ዘንድ አርቲ ከሚባለው ተክል ነው።
ይህ እፅ የወባ በሽታን የሚፈውሱ ንጥረ ነገሮችንም በውስጡ አካቷል። ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆሊና ታዲያ ይህንን የአርቲ ተክል ከሌሎች እፅዋት ጋር በመቀላቀል መድኃኒት እንደተሰራና፣ ሙከራም ተካሂዶ ፈዋሽነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። ሁለት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችንም ማዳኑንም ይፋ አድርገዋል።
መድኃኒቱ ስለ ፈዋሽነቱ ምንም አይነት ማስረጃ ያልቀረበ ሲሆን የምርምር ተቋማትም ማረጋገጥ አልቻሉም። ፕሬዚዳንቱ ግን አልሰማም ብለዋል፤ ሃገሪቱ ጥላው የነበረውንም አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔም በከፊል አንስተዋል።
የሃገሪቱ ሚዲያ እንደዘገበው ከአንድ ሺህ በላይ ወታደሮች በመዲናዋ አንታናናሪቮ ተሰማርተው መድኃኒቱን እያከፋፈሉ ነው።
ህዝቡም ለመቀበል የተሰለፈበት ቪዲዮም ወጥቷል። አቅማቸው ለማይፈቅደው ማህበረሰብ በነፃ የሚከፋፈል ሲሆን ለሌላው ግን በትልልቅ መደብሮች መሸመት ይችላሉ።
የጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ተቋም በአርቴሚዥያ (አርቲ) ኮሮናን ለመፈወስ ያስችላል ወይ በማለት ምርመራ የጀመረ ሲሆን ውጤቱ አልታወቀም። ኮንጎም በአትክልቱ ላይ የምርምር ስራዎችን ጀምራለች።
የብርቱካን ልጣጭ ፈዋሽነት
ከሰሞኑ ሙቅ ውሃ፣ የብርቱካን ልጣጭ፣ ቪክስ ተብሎ የሚጠራው ቅባትን በመቀላቀል መጠጣት ቫይረስንም ሆነ ባክቴሪያን ይገላል፣ ሁሉንም ፀረ ተህዋሲያንንም ከሰውነት ያስወግዳል የሚለው ቪዲዮ በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ ሆኗል። ወደ 1.6 ሚሊዮንም ሰዎች በቲክቶክ ተመልክተውታል።

የፎቶው ባለመብት, TikTok
ቲክቶክ ቪዲዮውን ከገፁ ላይ ካወረደው በኋላም ቪዲዮው በኢንስታግራም ላይ ወጥቶ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል። ኢንስታግራምም ቪዲዮውን ከገፁ አጥፍቶታል።
ሙቅ ውሃም ሆነ ሲትሪክ አሲድ ያለባቸውን ፍራፍሬዎች መመገብ የኮሮናቫይረስን ለማዳናቸው ምንም መረጃ የለም።
በቪዲዮ ተጠቃሚዎች ዘንድ ዝነኛ በሆነው ቲክቶክ የተለያዩ ውዝግብን የሚያጭሩ ቪዲዮዎችም ወጥተዋል።
ለምሳሌም ያህል የኮሮናቫይረስን እያዛመተ ያለው 5ጊጋ ባይት ኢንተርኔት ነው በሚል ከሴራ ጋር የተገናኙ መረጃዎች ተለቀዋል።
በወጡትም ቪዲዮዎች ላይ በቴሌኮም ዘርፉ የሚሰሩ ሰራተኞችን ጥቃት እንዲደርስባቸው የሚያበራቱ መልእክቶችም ተላልፈዋል። ቪዲዮዎቹ ከቲክቶክ ገፅ ላይ የጠፉ ሲሆን ካሁን በኋላ በሴራ ላይ የሚያጠነጥኑ ቪዲዮዎችን እንደማይቀበሉም ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የኤድስ ምርምር ለቫይረሱ መንስኤ አይደለም
ከሰሞኑ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሳይንቲስት ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅ የኮሮናቫይረስ በላብራቶሪ ነው የተፈጠረው የሚለው አስተያየት ከፍተኛ ውዝግብን ፈጥሯል።
ሉክ ሞንታግኒየር የኤች አይቪ ቫይረስን ካገኙት ሳይንቲስቶች አንዱ ሲሆኑ በፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበውም ቫይረሱ በድንገት ከውሃን ላብራቶሪ እንዳመለጠ ገልፀዋል። ሳይንቲስቱ እንደሚሉት የኤድስ በሽታ ላይ የሚደረግ ክትባትም ምርምር ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
ሳይንቲስቱ ይህንን ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ መላምቶች ቢሰሙም ኮሮናቫይረስ ድንገት ከላብራቶሪ ለመውጣቱ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለ የቢቢሲው የሳይንስ አዘጋጅ ፖውል ሪንከን ይናገራል።
እስካሁን በቫይረሱ ላይ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት ቫይረሱ ከእንስሳት እንደመጣ ነው።
የሳይንቲስቱ አስተያየት የሰፈረበት ቪዲዮ ከፍተኛ ተመልካች አይቶታል፣ ለበርካታ መላምቶችም በር ከፍቷል።

የአለምን ህዝብ የመቆጣጠሪያ መንገድ
ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዘው የሚሰጡ አስተያየቶች ማብቂያ የላቸውም። ኮሮናቫይረስን የፈጠሩት በአለም ታላላቅ የሚባሉ ኃይሎች ሲሆኑ ይህም የአለምን ህዝብ ለመቀነስ የወጠኑት ሴራ እንደሆነ የቀድሞው የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት ኃላፊ ቭላድሚር ካቭችኮቭ በዩቲዩብ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
የቀድሞ የደህንነት ኃላፊ እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ በሰው ወይም በላብራቶሪ ስለመሰራቱ ሳይንሳዊ መረጃዎች ቢኖሩም በርካታ ሳይንቲስቶች ግን ከእንስሳት ነው የመጣው በማለት አጣጥለውታል ብለዋል።
በባለፈው ወር የወጣው ይህንን ቃለ መጠይቅ ዘጠኝ ሚሊዮን ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን በርካቶችም በፌስቡክ እያጋሩት ነው፤ በተለያዩ ቋንቋዎችም ተተርጉሟል።













