ኮሮናቫይረስ፡ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ የግድ አስፈላጊ ሊሆን ነው?

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
የኮሮናቫይረስ ሥርጭትን ለመቀነስ ብዙዎቻችን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ይኖርብን ይሆን?
የዓለም ጤና ድርጅት የከፍተኛ ባለሙያዎች ስብስብ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመምከር ዕቅድ ይዟል። አባላቱ በአፍና በአፍንጫ ጭምብል አጠቃቀም ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶችንም ይመርምራሉ።
አሜሪካ ውስጥ የተሠራ አንድ ጥናት፤ አንድ ሰው ሲያስል ከአፍና አፍነጫው የሚወጡ ፍንጥቃጣቂዎች እስከ 6 ሜትር ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል፤ ማስነጠስ ደግሞ 8 ሜትር እንደሚጓዝ ደርሼበታለሁ ብሎ ነበር።
የስብስቡ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሄይማን አዲስ የተሠራ ጥናት በጭምብል አጠቃቀም ዙሪያ የተለየ ሐሳብ ይዞ መጥቷል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
'የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉንም አማራጮች እያየ ነው። ከዚያ በኋላ በአፍና በአፍንጫ ጭምብል አጠቃቀም ዙሪያ አዲስ መመሪያ ልናወጣ እንችላለን፤ አሊያም ባለበት ሊቀጥል ይችላል።'
ምን ይመከራል?
የዓለም ጤና ድርጅት፤ በሽታ ከሰው ሰው እንዳይተላለፍ በሚል ከሚያስነጥስ ወይም ከሚያስል ሰው ቢያንስ የአንድ ሜትር ርቀት እንዲኖረን ይመክራል።
ድርጅቱ፤ የበሽታ ምልክት ያለባቸው ብቻ የአፍና አፍንጫ ጭምብል እንዲያደርጉ ይመክራል። ጤናማ ሰዎች ጭምብል ማድረግ ያለባቸው ሌሎችን የሚንከባከቡ ከሆነ አሊያም ደግሞ የሚያስነጥሱና የሚያስሉ ከሆነ ነው ይላል።
ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የበርካታ አገራት የጤና ባለሙያዎችና ባለስልጣናት ማንኛውም ሰው ከቤት ውጪ በሚንቀሳቀስበት ወቅት አፍን አፍናጫውን እንዲሸፍን እየመከሩ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ይህንን በማይፈጽሙት ላይ ቅጣት እየጣሉ በማስገደድ ላይ ናቸው።
ጭምብሎች ጥቅም የሚኖራቸው ሰዎች እጃቸውን በአግባቡ የሚታጠቡ ከሆነና ጭምብሉን ከተጠቀሙ በኋላ ካስወገዱ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ያሳስባል።
ዩናይትድ ኪንግደምም ሆነች አሜሪካ ዜጎቻቸው ከቤታቸው ውጪ በሚሆኑበት ጊዜ የሚመክሩት ቢያንስ የሁለት ሜትር ርቀት እንዲጠብቁ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ቫይረሱ በቅንጣት ጠብታዎች ነው የሚተላለፈው የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።
ለምሳሌ አንድ ሰው ሲያስነጥስ ወይም ሲያስል የሚወጣው ጠብታ ወይ ይተናል አሊያም መሬት ላይ ወድቆ ይጠፋል ተብሎ ይታሰባል። ስለዚህም አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ ባሻገር አፍና አፍንጫን መሸፈን አስፈላጊ እንደሆነ እተመከረ ነው።
አዲሱ ጥናት ምን ይላል?
የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ተመራማሪዎች ዘመን አፈራሽ የካሜራ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አንድ ሰው ሲያስነጥስ ወይም ሲያስለው ምን እንደሚፈጠር ማወቅ ችለዋል።
በጥናታቸው መሠረትም ከማሳል የሚወጣው ፍንጥቅጣቂ ፈሳሽ አስከ 6 ሜትር ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል ደርሰውበታል። ማስነጠስ ደግሞ በጣም በፍጥነት ስለሚጓዝ እስከ 8 ሜትር ድረስ ሊሄድ ይችላል ብለዋል።
አንዳንድ አጥኚዎች አሁን እየተመከረ ያለው የሁለት ሜትር ርቀት አይበቃም ይላሉ።
የጤና ድርጅቱ ሰዎች ምን ይመክራሉ?
ፕሮፌሰር ሄይማን አዲስ የተሠራው ጥናት በሰው ልጆች መካከል ይመከር የነበረውን ርቀት ስሊያሰፋው በደንብ እናየዋለን ይላሉ። አልፎም ጥናቱ በማስረጃ መቶ በመቶ ሲረጋገጥ ጭምብል ማድረግ ርቀትን ከመጠበቅ እኩል አስፈላጊ እንዲሆን እንመክር ይሆናል ባይ ናቸው።
ቢሆንም የጭምብል አጠቃቀም ጉዳይ ብዙ እንደሚቀረን ይናገራሉ። ቡድኑ በሚቀጥሉ ጊዜያት ተጨማሪ ምክክሮች እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
በርካታ አገራት ጭምብል መጠቀም ግዴታ እያደረጉ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት በጥናቱ መሠረት ጭምብል ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ካወጀ ምናልባትም ያለ ጭምብል መንቀሳቀስ አዳጋች ይሆናለ።













