ኢትዮጵያን የቢጫ ወባ ወረርሽኝ እንደሚያሰጋት የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
ድርጅቱ እንዳለው በመጋቢት ወር በበሽታው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ቁጥር ሦስት እንደነበረ አመልክቶ ባለንበት የሚያዝያ ወር ግን የተጠርጣሪዎችቹ አሃዙ ወደ 85 ከፍ ማለቱን ገልጿል።
በሽታው አለባቸው ተብለው ከተጠረጠሩት ሰዎች መካከልም ስምንቱ በምርመራ በሽታው እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል።
የቢጫ ወባ ክትባት ተመልሶ እንዲጀመር መደረጉን ያመለከተው የዓለም ጤና ድርጅት፤ ከሚኖሩበት አካባቢ እርቀው የመሄድ የጉዞ ታሪክ በሌላቸው ሰዎች ላይ መታየቱ እንዳሳሰበው አመልክቷል።
"በአገር ደረጃ ያለው የበሽታው ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተደረሰበት" መሆኑን ድርጅቱ ጠቅሶ፤ በተለይ በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኘው የጉራጌ ዞን ገጠራማ አካባቢዎች ውስጥ የቢጫ ወባ በሽታው የመስፋፋት መጠን ፈጣን መሆኑን ተገልጿል።
አክሎም "በሕዝብ ውስጥ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ዕድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች መገኘታቸው በጣም አሳሳቢ ነው" ሲል ድርጅቱ ስጋቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ለቢጫ ወባ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በተለይ ትኩረት በማድረግ የበሽታው መከላከያ ክትባት ለሰዎች ሲሰጥ ቆይቷል።
በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ዋነኛ የጤና ችግር በሆነበትና ትኩረት ሁሉ ወደዚህ ወረርሽኝ በዞረበት በዚህ ጊዜ ተጨማሪ በሽታዎች የሚከሰቱ ከሆነ የሚያስከትሉት ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ።












