ኮሮናቫይረስንና የፀሐይ ብርሃንን ምን አገናኛቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች ሃገራት በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የእንቅሳቃሴ ገደብ ተከትሎ ዜጎቻቸው ቫይታሚን ዲ እንዲወስዱ እየመከሩ ነው።
ለወትሮው ብዙዎቻችን የማይከፈልበት ቫይታሚን ዲ ከፀሐይ እናገኛለን። ከፀሐይ የሚገኝው ቫይታሚን ዲ ከሌሎች የቫይታሚን ዓይነቶች ጋር ተዳምሮ ሰውነታችን እንዲነቃቃና በሽታን ወግድ እንዲል ይረዳል። የቫይታሚን ዲ ጥቅም የሚገባን ወረርሽኝ ሲመጣ ነው ይላሉ የዘርፉ ሰዎች።
ዩናይት ኪንግደም ውስጥ ያሉ ሰዎች ቢያንስ በቀን 10 ማይክሮግራም ቫይታሚን ያለበት ኃይል ሰጭ እንዲወስዱ ይመከራሉ። በተለይ ደግሞ እያደገደገ ያለውን የክረምት ወቅት ተከትሎ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ካልቻሉ በሚል ነው ይህ ምክር የተለገሳቸው።
ለመሆኑ እነማን ናቸው ቫይታሚን ዲ እንዲወስዱ በፅኑ የሚመከሩት?
- በቀን ውስጥ ተገቢውን ያክል ፀሐይ የማያገኙ ከሆነ
- በአረጋውያን መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ከሆነ
- የሚለብሱት ልብስ ሙሉ የሰውነት ክፍልዎን የሚሸፍን ከሆነ
ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች በቂ የሆነ የፀሐይ መጠን ካላገኙ ቫይታሚን ዲ ላያመርት ይችላል። ምክንያቱም ቆዳቸው በባሕሪው ከፀሐይ የሚገኝ ቫይታሚንን በቀላሉ መቀበል ስለማይችል።
ብሪቲሽ ኒውቲሪሽን ፋውንዴሽን ለተሰኘ ድርጅት የምትሠራው ሳራ ስታነር 'አለመታደል ሆኖ የኮሮናቫይረስ አሉታዊ ተፅዕኖ ከእኛ ጋር ይቆያል። ይህ ማለት ደግሞ ውጭ የምንወጣበት ጊዜ ትንሽ ነው። ቤታችን መቀመጣችን ለእኛው ጥቅም ነው። ስለዚህ ከፀሐይ የምናገኝ የነበረውን ቫይታሚን በሌላ መተካት ይኖርብናል' ይላሉ።
ቫይታሚን ዲ ወሰድኩ አልወሰድኩ. . . ?
ቫይታሚን ዲ ለጤናማ አጥንት ወሳኝ ነው፤ ለጥርስና ጡንቻም እንዲህ። የቫይታሚን ዲ እጥረት በተለይ ሕፃናት ላይ የአጥንት መጣመም ሊያስከትል ይችላል፤ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ በአዋቂነት ዘመንም ጉዳት ይኖረዋል።
አንዳንድ ጥናቶች ቫይታሚን ዲ ለጉንፋን በሽታዎች ያለንን ተጋላጭነት ይቀንሳል ይላሉ። ቢሆንም ቫይታሚን ዲ የመከላከል አቅምን ይጨምር አይጨምር ማስረገጫ አልተገኘም።
በብዛት ብወስድስ?
አይመከርም። ኃኪም ካዘዘው በላይ መውሰድ በጊዜ ሂደት ጉዳት ሊያመጣ ይችላል።
ለሕፃናት በቀን ከ50 ማይክሮግራም በላይ አይመከርም። ከ12 ወራት በታች ያሉ ጨቅላዎች ከ25 ማይክሮግራም በላይ መውሰድ የለባቸውም። አዋቂዎች ደግሞ ከ100 ማይክሮግራም በላይ እንዳይወስዱ ይመከራል። ከተጠቀሱት በላይ መውሰድ የሚቻለው በኃኪም ትዕዛዝ ብቻ ነው።
ኮሮናቫይረስን ይከላከላል?
አይከላከልም። ቫይታሚን ዲ መውሰድ ከኮሮና ይታደግ አይታደግ የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ ጥናት የለም። ነገር ግን የጤና ባለሙያዎች ቫይታሚን ዲ እንዲህ ያለ ወረርሽኝ ሲከሰት ጠቀሜታው የጎላ ነው ይላሉ።
ቫይታሚን ዲ አቅማቸው የደከመ ሰዎችን በእጅጉ ያግዛል።
የስፔንና ፈረንሳይ ተመራማሪዎች ቫይታሚን ለኮሮናቫይረስ በሽተኞች ጥቅም ይኖረው እንደሆን ለማጣራት ምርምር ላይ ናቸው።
ከየት መግዛት እችላለሁ?
ቫይታሚን ዲ ገበያዎች ውስጥ እንዲሁም የፋርማሲ ሸልፍ ላይ በቀላሉ ሊገኝ ይችላል። እንዲሁ ቫይታሚን ዲ ተብለው ሊሸጡ ይችላሉ። ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ተቀይጠው ጥቅም ላይ ሊውሉም ይችላሉ። ለሕፃናት ደግሞ በጠብታ መልክ ይቀርባሉ።
በምግብ ውስጥ ሊገኝ አይችልም?
ከምግብ ብቻ ቫይታሚን ዲ ማግኘት ከባድ ነው። ምንም እንኳ የተመጣጠነ መግብ መብላት ቢመከርም ከምግብ ከተወሰነው በላይ ንጥረ-ነገር ማግኘት አይቻልም።
ቫይታሚን ዲ ከዓሣ ዓይነቶች ከእንቁላል ሊገኝ ይችላል። አንዳንድ የቁርስ ሲሪያሎች፣ ማርገሪን እና እርጎ ቫይታሚን ዲ ይገኝባቸዋል።













