ኮሮናቫይረስ፡ "ከሞትኩ መላዕክትስ ስሜን ለምን አይጠሩም እል ነበር" ከኮሮናቫይረስ ያገገመችዋ

የአርባ ዘጠኝ ዓመቷ ኤልዛቤት በህይወት መቆየትን፣ መተንፈስን እንደ ቀላል አታየውም። እድለኛ እንደሆነችም ታውቃለች። በኮሮናቫይረስ በጠና ታማ ሆስፒታል የገባችውም በዚህ ወር ነበር። ለማገገም ያያችውን ስቃይ፣ ሆስፒታል ውስጥ ስለተደረገላት ድጋፍ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ አጫውታዋለች።
የመጀመሪያዎቹ ቀናት
አስታውሳለሁ ቀኑ አርብ ነበር፣ ከሌላው ጊዜ በተለየ ድካም ተጫጫነኝ። አልጋ ላይ ስወጣ ድካሙን መቋቋም አልቻልኩም ነበር። በመጪዎቹ ቀናት ቅዳሜና እሁድም እንዲሁ በማላውቀው ምክንያት በድካም ተወጥሬ ነው ያሳለፍኳቸው።
ሰኞ ዕለትም ድካሙ ቀጠለ፣ እግሬ መዝለፍለፍ እንዲሁም መቋቋም የማልችለው ህመም ይሰማኝ ጀመር። ምናልባት የጡንቻ መኮማተር ይሆን ብዬ ህመሙንም ለማስታገስ ፓራሲታሞል ዋጥኩኝ።
ሳል ነበረኝ ግን ከባድ አልነበረም። ለሳምንት ያህልም ከአልጋዬ መውጣት አልቻልኩም። አካባቢዬ ወደሚገኝ የነዳጅ ማደያ በትግል እቃ ለመግዛት ሄድኩ።
ስመለስ ያንቀጠቅጠኝ ያንዘፈዝፈኝ ነበር፤ ሰውነቴ በረዶ የሰራ ይመስል ቀዘቀኝ። ሙቀት እንዴት ላግኝ? የሞቀ ውሃ በአራት ጠርሙሶች አድርጌ፣ ሁለት ብርድ ልብስ ብደርብም ምንም ሊሞቀኝ አልቻለም።
ከዚያም ትንሽ ቆይቶ ሙቀት አይደለም ትኩሳት ለቀቀብኝ።
ሰውነቴ እንደ እሳት ነደደ፣ የራስ ምታቱ ጭንቅላቴን ለሁለት የሚከፍል እስኪመስል ድረስ በቃላት መግለፅ የማልችለው ህመም ይሰማኝ ጀመር።
መብላት አልቻልኩም፣ ያስመልሰኛል፣ ሰውነቴ በላብ ተጠመቀ፣ ትንፋሼም መቆራረጥ ጀመረ እናም ትንሽ ቆይቶም መተንፈስ አልቻልኩም።
የአስም ህመምተኛ በመሆኔ የትንፋሼ ሁኔታ ትንሽ ቢያሰጋኝም ቤት ሆኜ ማገገም እንደምችል ተስፋ ነበረኝ። ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ ራሴን መሳት ጀመርኩ፣ ያለሁበትን መዘንጋት ጭራሽ የ15 ዓመት ልጄ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ለእርዳታ እንደደወለ ሲነግረኝ እንደ ህልም ነው ትዝ የሚለኝ።
የህክምና ባለሙያዎቹ መጥተው የአምቡላንስ ሾፌሩ "በጣም ደክማለች፤ ይዘናት ልንመጣ ነው" ሲልም ከርቀት ይሰማኛል። የኦከስጅን መተንፈሻ ማሽን ገጠሙልኝና ወደ አምቡላንሱ ውስጥ አስገቡኝ።
አንደኛው ልጄ እናቴን ጠርቷት ስለነበር ስታየኝ የወላድ አንጀቷ ተብረከረከ። ለእኔም በዚያ ሁኔታ ሆኜ ፊቷ ላይ ያለውን ተስፋ መቁረጥ ማየት ከባድ ነበር። የልብ ህመም ስላለባት ተጠግታ ልታየኝም አልቻለችም።
ሆስፒታል ስንደርስም የእኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አምቡላንሶችም ህመምተኞችን ለማውረድ ተራቸውን እየጠበቁ ነበር። ተራዬም እስኪደርስ ለሦስት ሰዓታት ያህል ጠበቅኩ። ተራዬ ሲደርስም በተሽከርካሪ ወንበር እየገፉ ለብቻ የተለየ ክፍልም ሆነ ቦታ እንደሌለና ሆስፒታሉም ከአፍ እስከ ገደፉ መሙላቱን ሰማሁ።
አይኖቼን ጨፍኜ የሚሉኝን እሰማለሁ፣ ሰዎች ይጣደፋሉ፣ ስልኮች ይጮሃሉ፤ ሆስፒታሉ በረሻ የተሞላ ነበር።
ትንሽ ቆይቶም አንድ ነርስ "አፍሺን ክፈቺና ከጉሮሮሽ ናሙና እንወስዳለን" አለኝ ህመም ነበረው፤ ከዚያም ከአፍንጫየም እንዲሁ በተመሳሳይ ናሙና ተወሰደ። የደም ምርመራ፣ የደረት ራጅ ያልተደረገልኝ ምርመራ የለም።
ምን እየተከናወነ እንደሆነ አልገባኝም፤ ከአሁን አሁን ራሴንም የምስት መስሎኝ ነበር። በመቀጠልም አንዲት ነርስ መጥታ ኮሮናቫይረስ እንደሆነና 24 ሰዓትም በኦክስከጅን በመታገዝ መተንፈስ እንዳለብኝ አስረዳችኝ።
ደረቴ ላይ ያለው ህመም ይህ ነው የሚባል አይደለም፤ የድንጋይ ክምር የተጫነኝ ይመስለኛል። ማስታገሻ መርፌም ቢወጉኝ፤ ህመሙ አልቀነሰልኝም። ሆዴን የመውጋት ስሜት ተሰማኝ፤ ከባድ የሚባለውን የምጥ አይነት ስሜትም ይሰማኝ ቀጠለ። ጮክ ብዬም ማልቀስ ቀጠልኩ አልቻልኩም፤ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻለኝም እያልኩ ነበር።
በሞት ጥላ ስር
ከእኔ ጋር አራት አልጋዎች ነበሩ፤ ሁሉም ህመምተኞች ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሲሆን በተጨማሪም ተደራራቢ የጤና እክል ነበረባቸው። ሁለት ተለቅ ያሉ ሴቶች የስኳር ህመምተኞች ነበሩ። ሌላኛዋ ሴትዮ እኔ ከገባሁ ከቀናት በኋላ ስለመጣች ብዙ አላስታውስም።
የመጀመሪያዎቹ ቀናቶች እንደ ሰመመን ነው የሚታወሱኝ፤ ነርሶች ይገባሉ ይወጣሉ። ፅዳት ሠራተኞች በየጊዜው እየመጡ ያፀዳሉ። የውሃ ጥም ያነደዳቸው ህሙማን ደወሉን በተደጋጋሚ ይደውሉታል። ነርሶቹ ያለመታከት ቢያንስ ከአስራ ሁለት ሰዓት በላይ ያለማቋረጥ ይሰራሉ። ድካማቸው በፊታቸው ላይ ይነበባል፤ በከፍተኛ ሁኔታ ዝለዋል።
አንድ ምሽት ላይ አንድ ወንድ በክፍላችን ውስጥ አየሁ። የሴቶች ብቻ በሆነው የህሙማን ክፍል ወንድ ምን ይሰራል? ብዬ ነርሷን ጠራሁ።
ነርሷም ከእኔ በተቃራኒ ያለችው ሴትዮ ልጅ እንደሆነና ልትሞት እያጣጣረች መሆኑን ነገረችኝ።
ልቤ ተሰበረ፤ አዘንኩላቸው ግን ለራሴም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተሰማኝ "እንደእኔ አይነት ሙሉ ሰው በአይኔ እያየሁ እንዴት ትሞታለች?" እያልኩ በተደጋጋሚ እጠይቃለሁ። ግራም ተጋብቻለሁ።
መጋረጃውን ከለል ቢያደርጉትም ድምፅ ይሰማኝ ነበር።
"ሞቻለሁ ወይስ አለሁ?"
ከዚያ በኋላ መቃዠት ጀመርኩ። በህይወቴ የማውቃቸው ሰዎች ጋር እያወራሁ ይመስለኛ፤ የት እንደሆነ አላውቅም። "ሞቻለሁ ወይስ አለሁ?" ራሴንም እጠይቅ ነበር።
እነዚህን ሰዎች የማናግረው ወደ ሞት እየተሻገርኩ ስለሆነ ነው? ሰዎች ወደሞት ሲቃረቡ ሙሉ ህይወት በጨረፍታ ትመጣለች ሲሉ ይህንን ማለታቸው ነው። ከዚያም ደግሞ ከእራሴ ጋር ያለኝ ሙግት ይቀጥላል "አይ አልሞትኩም! ከሞትኩ ነጩ ብርሃን የታለ? መላዕክትስ ስሜን ለምን አይጠሩም?"
ሲነጋጋ አንድ ነርስ ሴትየዋ መሞቷን አረዳን። አስከሬኗን በፍጥነት ያነሱታል ብለን ብንጠብቅ ምንም የለም። ለሰዓታት ያህልም ሬሳዋ እንደተንጋለለ ማየት አሰቃቂ ነበር። ከዚያም አስከሬኑን አፀዳድተው በፕላስቲክ ጠቀለሉት፤ እቃ የሚያሽጉ ነው የሚመስሉት። አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብለውም ለአስከሬን ወደተዘጋጀው ትልቅ ሻንጣ መሰል ነገር ውስጥ አስገቡት።
አስከሬኑ ከሻንጣው ብረት ጋር ሲጋጭ ያወጣው ድምፅ እስካሁን ይዘገንነኛል፤ እስከ ህይወቴ መጨረሻ አልረሳውም።
የሞተችበት አካባቢ ተፀዳ፣ የሎሚ መአዛ ባለው ሽታ ተረጨ። አልጋው ባዶ ሆነ። የሰው ልጅ ታይቶ ጥላ ይሉ እንዲህ ነው፤ ባንዴ መሞት አለ። ሰው ነበረች አሁን አፈር። ይህ ሁኔታ ህይወቴን ነው የቀየረው።
ከእኔ ትይዩ የተኛችውም ሴትዮ ድንገት እራሷን ሳተች ልጇም "እማማ፣ እማማ፤ እኔ ነኝ" እያለች ስትጣራ ይሰማኛል። ልጇ አላወቀችም ግን ሞታለች። ለሁለት ቀናትም ያህል ስትሰቃይ ነበር። ከእኔ አጠገብ ያለችው ሴት እየተሻላት ነበር እኛ አካባቢ ያሉ የህመምተኛ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ህሙማን ግማሹ ተርፎ ግማሹ በመሞቱ እድለኛ ነን ትለኛለች።
በሞትና በመኖር መካከል የሚደረግ ትግል
በህይወት ለመቆየትም ታገልኩ። ተስፋ ልቆርጥ ስል እንደገና ራሴን አይዞሽ ግፊ፣ ገና አርባ ዘጠኝ ዓመትሽ ነው። ለመሞት ዝግጁ አይደለሽም። ቀንሽ ገና ነው እላለሁ። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለልጆቼ፣ ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼ ስል መኖር እንዳለብኝ ተሰማኝ።
እህቴ ሎሬን፣ ወንድሜ ሪቻርድ በተደጋጋሚ ፍቅርና ድጋፍ የተሞላበት መልዕእክቶች ልከውልኛል፤ መንፈሴንም ጠግነውታል። የመኖር ተስፋዬንም አንሰራርተውታል።
መጋቢት 30/2012 ዓ.ም ሙሉ ጨረቃ ወጣች። በጨረቃ ለሚቆጥሩ አዲስ ወቅትም ነው። ወቅቱንም የማገገሚያየ ምልክት እንደሆነ አድርጌ ወሰድኩት።
በተስፋ ባለሁበት ሁኔታ የተረፈችው ሦስተኛዋም ሴት ዓለምን ተሰናብታ ሄደች። ተመሳሳይ ሂደቶች ተስተናገዱ።
ምናልባት ለህይወቴ መትረፍ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው አንድ ነርስ ነው፤ በተደጋጋሚም "ዶክተሮች ደህና ነሽ ወደቤት መሄድ ትችያለች ካሉሽ ያለምንም ማወላወል ወደቤት መሄድ ነው። ብዙዎች ህሙማን የሰሩትን ስህተት አንቺም እንዳትደግሚ። አብዛኛዎቹ ተሽሏችኋል ሲባሉ ሙሉ በሙሉ አላገገምንም ብለው ሆስፒታል ይቆያሉ እናም ሁሉም ህሙማን እንደገና በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል። ሁሉም ሞተዋል" ይለኝ ነበር።
አንድ ቀንም ዶክተሩ በደሜ ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን በማየት "ደህና ነሽ፣ ልትሄጂ ትችያለሽ" አለኝ። በጣም ተደሰትኩ፣ የማይታመን ነው ቤቴ ልሄድ ነው።
ውጭ ስወጣ የብርዱ ውሽንፍር ተቀበለኝ። የሆስፒታል ጋወንና ሸበጥ አድርጌያለሁ። ብርዱ ፊቴን ለበለበው፤ ምንም ግን አልነበረም።
አሁን የአምቡላንሷን ሹፌር ስሟን አላስታውሰውም ግን መልአክ ናት። ጠዋት አስራ ሁለት ሰዓት የጀመረች እኔን ከሆስፒታል ስትወስደኝ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ከሃያ ነበር።
አስራ ስምንት ሰዓታት ሰርታለች። እንዲህ ነው ሰዎች እያገለገሉ ያሉት። ነርሶችና ዶክተሮች ብቻ አይደሉም። አምቡላንስ የሚነዱት፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ የአስተደዳር ሠራተኞች፣ አስከሬን የሚያፀዱት፣ ወደ መካነ መቃብር የሚወስዱት ስንቱ ተቆጥሮ፤ ሁሉም መስዋዕትነት ከፍሎ እየሰራ ነው።
የአምቡላንስ አገልግሎት ለሚሰጡት እንዲሁም ለሆስፒታሉ ሠራተኞች ለፅናታቸው፣ ለእንክብካቤያቸው አመስግኜ ደብዳቤ ፅፌያለሁ።
አሁንም ቢሆን በማገገም ላይ ስለሆንኩ ለሳምንታት ያህል አልጋ ላይ ነኝ። የሳንባ ምቹ እስኪሻለኝ ከሦስት እስከ ስድስት ወር እንደሚወስድ ዶክተሩ ነግሮኛል።
ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋለ እናቴ ምግብ እየሰራች ደጃፌ ላይ ታስቀምጣለች፤ ምስጋናው ይድረሳትና፤ ህይወቴን ቀጥላዋለች።
ሞትን ነክቻታለሁ እናም በህይወት በመቆየቴ ደስተኛ ነኝ። ለወደፊቱ ህይወትን እንዲህ እንደ ቀልድ አልወስድም። ቁሳቁስ፣ ሃብት፣ ንብረት ምንም ጥቅም የለውም። አሁን የሚናፍቀኝ ውጭ ወጥቼ መተንፈስ፣ ወፎችን መመልከት፣ ተፈጥሮን ማድነቅ ነው። በህይወት ለመኖር ሁለተኛ እድል ተሰጥቶኛል።














