ኮሮናቫይረስ፡ የፅኑ ህሙማን ፈታኙ የማገገም ሂደት ምን ይመስላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ (ቬንትሌተር)፣ የፊት ጭምብል እንዲሁም የፅኑ ህሙማን ክፍል ማቆያ የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ መስማት የዓለማችን አዲሱ እውነታ ሆኗል።
በኮሮናቫይረስ የታመሙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እየታከሙም ይገኛሉ፤ ብዙዎችም በሞትና በህይወት መካከል ናቸው ።
በሆስፒታሎች በሚገኙ የፅኑ ህሙማን ክፍሎች ውስጥ በህይወት ለመቆየት ትግሉ ቀጥሏል። በራሳቸው መተንፈስ ያዳገታቸው ሰዎች በተራቀቁ ማሽኖች በመጠቀም በህይወት ለመቆት የሚያስችላቸው ትንፋሽ ተቀጥሎላቸዋል። የተለያዩ የሰውነት ተግባራትን በማሽኖች በመጠቀምም ነው አካላቸው እየሰራ ያለው። መድኃኒቶችም እንደአስፈላጊነቱ ይሰጣቸዋል።
ለኮሮናቫይረስ መድኃኒት አልተገኘም። በአሁኑ ሰዓት በፀና ለታመሙ ህሙማን በሳንባቸው ውስጥ በቂ ኦክስጅን እንዲያገኙ ማድረግና በሽታን የመቋቋም አቅማቸው እንዲጠናከርና ቫይረሱን አካላቸው እንዲታገል የማድረግ ሥራ ነው በጤና ባለሙያዎች እየተሰራ ያለው።
ይህ ግን የማገገማቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በፅኑ ህሙማን ማከሚያ ክፍል ማገገም የቻሉ ህሙማን የጤና ችግራቸው ማብቂያ አይደለም።
በቀጣይነት የጤና ሁኔታቸው የተወሳሰበ ይሆናል። ከሆስፒታልም ከወጡ በኋላ ሙሉ በሙሉ ለመዳን ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል። የማይሽር የሥነ ልቦና ጠባሳም ሊያስከትል ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መተንፈስን መማር
ለረዥም ጊዜያት በፅኑ ህሙማን ክፍል የቆዩ ህሙማን ከወጡ በኋላም በራሳቸው መተንፈስ ስለሚያዳግታቸው የቴራፒ ህክምና ይሰጣቸዋል፤ በራሳቸው መተንፈስን እንደገና እንዲማሩ።
ከወጡም በኋላ የነበሩበት አሰቃቂ ሁኔታ እንዲህ በቀላሉ የሚጋፈጡት አይሆንም፤ ፍራቻም ያጠላባቸዋል።
በተለይም ረዘም ያለ ጊዜ ለቆዩት እንደገና ወደነበሩበት ህይወት መመለስ ፈተና ነው፤ ወደቀድሞ ማንነታቸውም ለመመለስ ከፍተኛ ትግል ይገጥማቸዋል።
"ታመው የፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የገቡ ከሆነ ህይወትዎ እንደሚቀየር ይወቁ። ቢሻልዎት እንኳን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍልዎ መሆኑን ማወቅ አለብዎት" በማለት በዩናይትድ ኪንግደም የሮያል ግዌንት ሆስፒታል የፅኑ ህሙማን አማካሪ ዶክተር ዴቪድ ሄብበርን ይናገራሉ።
"የፅኑ ህሙማን አገግመው በሚነቁበት ወቅት በጣም ስለሚደክሙ ያለድጋፍ መቀመጥ አይችሉም። እጃቸውን እንኳን ከተኙበት አልጋ ማንሳት አይችሉም፤ ጉልበታቸው ይክዳቸዋል" ይላሉ።
በህክምናው ወቅት ምግብ በቱቦ አማካኝነት ይገባላቸው ከነበረም የመናገርም ሆነ የመዋጥ እክሎች ከተሻላቸው በኋላ የሚያጋጥሟቸው ናቸው።
"ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ፤ ራሳቸውን ማወቅም ሆነ የነበራቸውን እውቀት መመለስ ችግር ይገጥማቸዋል" ብለዋል ዶክተር ሄብበርን በትዊተር ገፃቸው።
"ከጊዜ ጋር ይሻላቸዋል። በቴራፒ የታገዘ የህክምና አገልግሎት፤ የቋንቋና የንግግር ክህሎትን የሚያሰለጥኑ ባለሙያዎች፣ የሥነ ልቦናና ሌሎች ተጨማሪ እርዳታዎች ማግኘት አለባቸው። ይህም አንድ ዓመት ወይም ከዚያ የረዘመ ጊዜ ይወስዳል" ይላሉ።
ባለሙያዎች አፅንኦት ሰጥተው የሚናገሩት በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ማገገም የመጀመሪያው ደረጃ ቢሆንም፤ አገገምኩ ተብሎ መዘናጋት የለባቸውም ለረዥም ጊዜ የተቀናጀ የባለሙያዎች ክትትል መሰረታዊ ጉዳይ ነው።

በፅኑ ህሙማን የሚያጋጥም የአዕምሮ መረበሽ
በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ካሉ ህሙማን ውስጥ ሩብ የሚሆኑት ከፍተኛ የሆነ የአዕምሮ መረበሽ ያጋጥማቸዋል።
የብሪታኒያው ጋዜጠኛ ዴቪድ አሮኖቪች ለቢቢሲ እንደተናገረው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በሳንባ ምች ህመም ምክንያት ራሱን የፅኑ ህሙማን ክፍል ሲያገኘው የተሰማውን እንዲህ ይናገራል።
"እንዲህ ግልፅ ባለ ቋንቋ ለመናገር፤ ስነቃ ከቀን ወደ ቀን እያበድኩ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። የሌለ ድምፅ እንዲሁም ሰዎች ሲያወሩ ይሰማኛል" ብሏል።
"ብዙ ነገሮች እየተፈፀሙብኝ እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር። ይባስ ብሎ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ወደ ሙት መንፈስ ቀይረውኛል ብዬ አመንኩኝ። ከዚያም በሚያሳዝን ሁኔታ ሊበሉኝ እያዘጋጁኝም ነው ብዬ መፍራት ጀመርኩ" በማለት የነበረውን ስሜት አጋርቷል።
ጋዜጠኛው በማከልም በህይወቱ ውስጥ አሰቃቂ የሚላቸውን ሦስትና አራት ቀናትም ያሳለፈበት ሁኔታ እንደሆነ ይናገራል።
እሱ ብቻ ሳይሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ህሙማንም በዚሁ መንገድ አልፈዋል። ክስተቱም በስልሳዎቹ ውስጥ በፅኑ ህሙማን ላይ ያለውን የአእምሮ መረበሽ ይፋ ያደረገ ነው።
በዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎች ይህ የሚፈጠረው በአእምሮ ውስጥ ያለ የኦክስጅን እጥረት፣ ለማደንዘዣ የሚጠቀሙት መድኃኒቶች፣ የእንቅልፍ እጥረት ሲያጋጥም እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሆኖም ዴቪድ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚያጋጥመው የአዕምሮ መረበሽ ብዙ የሚወራለት አይደለም። ህሙማን የአእምሮ ህመምተኛ የሚል ስያሜ እንዳይሰጣቸውም በመፍራት በሚስጥር ይይዙታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደቤት መመለስ
ምንም እንኳን የጤና ባለሙያዎች የሰለጠኑና የተረጋጉ ቢሆንም፤ የፅኑ ህሙማን ክፍል የሚረብሽ ቦታ ነው።
"የሰውን ልጅ ለማሰቃየት የሚደረጉ ዘዴዎችን በምናስብበት ወቅት የሚመጡልን ሃሳቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የምታልፉባቸው ሁኔታዎች ናቸው" የሚሉት በለንደን ኮሌጅና በዊቲንግተን ሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ህክምና ፕሮፌሰር ሂውግ ሞንቶጎሞሪ ናቸው።
ህሙማን ራቁታቸቸውን ይሆናሉ፣ በተለያየ ሰዓትም የሚሰሙ የጥሪ ድምፆች አሉ፣ እንቅልፋቸው በጤና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይቋረጣል፣ ሙሉ ሌሊቱንም መድኃኒት ይሰጣቸዋል በማለት ፕሮፌሰር ሂውግ ለጋርዲያን ጋዜጣ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ምቾት የማጣት ሁኔታ፣ ግራ መጋባት፣ ፍራቻና ጥቃት የሚያደርስባቸው አካል እንዳለ የማሰብ ሁኔታ የፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የገቡ ሰዎች የሚያልፉባቸው አሰቃቂ እውነታዎች ናቸው።
ለዚያም ነው ግለሰቦቹ ከፅኑ ህሙማን ክፍል ወጥተው ወደ የቤታቸው በሚሄዱበት ወቅት የነበረው ስቃይን በቀላሉ መላቀቅ ስለማይችሉ ለቤተሰባቸውም ይተርፋል።
እንቅልፍ አይወስዳቸውም፣ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ መቆየታቸውን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ሊረሱት ይችላሉ።
ይህንንም ለመከላከል ሲል የእንግሊዝ የጤና አገልግሎት በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የቆዩ ቤተሰቦች ማስታወስ ይረዳቸው ዘንድ ማስታወሻ ቢያስቀምጡላቸው ጥሩ ነው ይላሉ።
መላው የሰውነታቸው ተግባር ይከናወን የነበረው በማሽን ታግዞ ስለነበር ካገገሙም በኋላ የሰውነት አካላት ወደ ቀድሞ ተግባራቸው በፍጥነት አይመለሱም። የጡንቻ መዛል እንዲሁም የማያቋርጥ ድካም ለረዥም ጊዜ አብረውት ለመኖር የሚታገሉት እውነታ ይሆናል።
ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የተገኘ ጥናት እንደሚያሳየው በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ፅኑ ህሙማን ከ3-11 በመቶ የሚሆን የጡንቻ ጥንካሬን እያጡ ይሄዳሉ ይላል።
ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ማገገም
ለብዙ የኮቪድ-19 ህመምተኞች በራሳቸው መተንፈስ አለመቻልና ሳንባቸው ከጥቅም ውጭ መሆን ለመሻል ረዥም ጊዜን እንደሚወስድ ማሳያ ነው።
የትንፋሽ መሳሪያ (ቬንትሌተር) ለህሙማኑ ኦከስጅን ወደ ሳንባ ለመውሰድና ካርቦንዳይኦክሳይድ ወደ ውጭ ለማስወጣት ይጠቅማል።
ቬንትሌተሩም እንዲሰራ በአፍ ወይንም በአፍንጫ የሚገባ ቱቦ ይገጠማል፤ በከፍተኛም ሁኔታ ማደንዘዣ ይሰጣቸዋል። አንዳንዶቹም ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው ቱቦው በመተንፈሻ አካላቸው ውስጥ ይገጠማል። ይህም የህሙማኑን የመዳን ጉዞ የበለጠ ያወሳስበዋል።
በእንግሊዝ፣ ዌልስና ሰሜናዊ አየርላንድ በተደረገ ጥናት ፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የገቡ ህሙማን በአማካኝ ከአራት እስከ አምስት ቀናት ያሳልፋሉ።
የህሙማኑ ቁጥር 2 ሺህ 249 ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት እንዲወጡ ተደርገዋል፤ ሌሎች 15 በመቶውን ደግሞ ሞት ነጥቋቸዋል። 1 ሺህ 600 የሚሆኑት ደግሞ አሁንም በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ናቸው። ይህ ግን አጠቃላይ አገሪቷ ውስጥ ያለውን መረጃ አያሳይም።
ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘ ሌላ መረጃ እንደሚያሳየው ተጨማሪ የላቀ የመተንፈሻ ድጋፍ ከተደረገላቸው የኮሮናቫይረስ ህመምተኞች መካከል 67 በመቶ ሞተዋል። በቻይና ደግሞ ቬንትሌተር የተገጠመላቸው ህሙማን ውስጥ መትረፍ የቻሉት 14 በመቶ ብቻ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, PA
'ቀስ በቀስ የመዳን ተስፋ'
የ61 ዓመቱ ሂልተን መሪይ ፊሊፕሰን በኮሮናቫይረስ ከተያዙ በኋላ በቬንትሌተር በመታገዝ ነበር ሲተነፍሱ የነበሩት።
ይመገቡ የነበሩትም በቱቦ አማካኝነት ስለነበር 15 በመቶ የሚሆነውን የሰውነት ክብደታቸው ቀንሷል። አገግመው ከሆስፒታል ከወጡም በኋላ እንዴት መራመድ እንዳለባቸው መማር ነበረባቸው።
የማገገማቸውንም ሁኔታ "ደረጃ በደረጃ ነው፤ ቀስ በቀስ ነው" ብለዋል።
"ለሦስት ሰዓት ያህል በጀርባዬ ሳልንጋለል በወንበር ላይ መቀመጤን እንደ ትልቅ ድል ነው ያየሁት። በጣም ነው ደስ ያለኝ" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሌሲስተር ፅኑ ህሙማን መታከሚያም ክፍል ሲወጡ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በጭብጨባና በደስታ ሸኝተዋቸዋል።
ይህንኑ የሚያሳየውን ቪዲዮ ብዙዎች ያጋሩት ሲሆን፤ በሕይወትም "ሁለተኛ እድል በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ" ብለው ብዙ ነገር እንደተማሩና ህይወትንም እንደገና እንዲያጤኑ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።
"የወፎች ጫጫታ፣ ሰማዩ፣ አበቦች፣ በሆስፒታል ውስጥ ሆኜ እያስታወስኳቸው ነበር። ሁሉ ነገር ይታወሰኛል፤ ቀላሉ ነገር ለምሳሌ ዳቦና ማርማላታ ፊቴ ላይ ድቅን እያሉ ነበር" ብለዋል።
"ያው ፈሳሽ ምግብ ነበር ሲሰጠኝ የነበረው፤ እግዚኦ ነው የሚያስብለው የሆስፒታል ምግብ፤ በተለይም የድንቹ ሾርባ ለመቅመስም ይከብዳል። የህይወቴ መጨረሻ ይሄ መስሎኝ ነበር" በማለት አስረድተዋል።














