ኮሮናቫይረስ፡ ቤት ጥቃት የበዛበት ሲሆን ወደየት ይሸሻል?

የፎቶው ባለመብት, Lorena Quaranta
በስፔኗ ግዛት አልማሶራ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብና የሶስት ቀናት ሐዘን ታውጇል። ምናልባት ስፔን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በኮሮና ቫይረስ ከመሞቱ ጋር ሊያያዝ ይችላል። ሁኔታው እንደሱ አይደለም የብዙዎችን ልብ የሰበረው የካሪናን አሟሟት ለማሰብ ነው።
ካሪና ከሁለት ልጆቿ ፊት ለፊት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችው በባለቤቷ አማካኝነት ነው። ከገደላትም በኋላ እጁን ለፖሊስ የሰጠ ሲሆን ወንጀሉንም ተናዟል።
ከኮሮና በፊት ቢሆን ሰው ተሰባስቦ የ35 አመት እድሜ ያላትን ጎረቤታቸውን ይዘክሯት ነበር። አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ቤታቸው የዋሉ ግለሰቦች ግን በርቀት በሃዘን አስበዋታል።
ደወልም ተደወለ፣ ልብ የሚሰረስር ሙዚቃም በኦርኬስትራ ታጅቦ ቀረበ፤ የአካባቢው ህዝብ መውጣት ባይችልም በመስኮታቸው እንዲሁም የቻሉት ደግሞ ወደ በረንዳቸው ወጣ ብለው በፀሎት አስበዋታል።
አገራት የኮሮና መዛመትን ለመቆጣጠር ቤት የመቀመጥ ውሳኔ ማሳለፈቸውን ተከትሎ ሴቶች ከጥቃት አድራሾቻቸው ጋር በአንድ ቤት እንዲቆለፉ፣ እርዳታ ከሚለግሷቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አለመኖር እንዲሁም ማምለጥ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ልጆችም ትምህርት ቤት ስለማይሄዱና ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ስለሚያሳልፉ የነዚህ ጥቃቶች ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤ ለማይሽር ስነልቦናዊ ጉዳቶችም እየተጋለጡ ነው።
ካሪና በስፔን ውስጥ በዚህ አመት ብቻ በትዳር አጋሮቻቸው ወይም በቀድሞ አጋሮቻቸው ከተገደሉ ሴቶች መካከል 17ኛዋ ናት። ኮሮናን ለመከላከል ውሳኔዎች ከተላለፉ በኋላ በትዳር አጋሯ የተገደለችው የመጀመሪያ ሴት ሆናለች።

ከቤት ጥቃት አድራሽ ፍራቻ፤ ከውጭ ቫይረሱን ፍራቻ- የሁለት አለም እሳት
አውሮፓ የኮሮና ቫይረስ ማእከል መሆኗን ተከትሎ ቤት የመቀመጥ እወጃን አስተላልፋለች። ምንም እንኳን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ የደረሱ ጥቃቶችን በተጠናቀረ መልኩ ማግኘት ባይቻልም ባለሙያዎች ከሚደርሳቸው የተበታተኑ መረጃዎች ማየት እንደሚቻለው ቤት ውስጥ የሚደርሱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን ነው።
ጭንቀት ጥቃት አድራሾችን የበለጠ ጠብ ጫሪ ያደርጋቸዋል፤ ለሴቶቹ ደግሞ ማንም እንደማይደርስላቸው ሲያውቁ ደግሞ የበለጠ ጨካኝነት ያጠቃቸዋል።
ከወር በፊት የቤት መቀመጥ ውሳኔው በስፔን ሲተላለፍ እንደ ኪካ ፉሜሩ ላሉ ባለሙያዎች ምን ያህል ሁኔታው አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ጠቋሚ ነበር። በካናሪ አይላንድስ ተቋም እኩልነት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ኪካ "ምንም እንኳን ኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለማስቆም ጥሩ መፍትሄ ቢሆንም ጥቃት በሚደርስበት ቤት ውስጥ ላሉ ሴቶችና ልጆች የከፋ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል አመላካች ነው" ይላሉ
ከዚህ ቀደምም በነበሩ እንደ ጎርፍ ባሉ ሁኔታዎች ሰዎች ቤት ውስጥ መቀመጥ አስገዳጅ በሚሆንበት ወቅት የሚደርሱ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምሩም አስተውለዋል።
ጣልያን፡ እንደ ስፔን ጣልያንም በኮሮና ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ ናት። ከመቶ በላይ ዶክተሮች ኮሮናን ሲያክሙ ህይወታቸውን አጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Lorena Quaranta
የ27 አመቷ ሎሬና ኳራንታ ዶክተር ለመሆን የቀራት ጥቂት ጊዜ ነበር፤ ህይወቷ በአጭር ባይቀጭ። እንደ ሌሎች ዶክተሮች በኮሮና አይደለም የሞተችው የፍቅር ጓደኛዋ መግደሉንም ለፖሊስ ተናዟል።
አስከሬኗም ወደተወለደችበት ሲሲሊ ፋቫራ ከተማ ሲመለስም ብዙዎች በበረንዳቸው ላይ ነጭ አንሶላ ሰቅለው በኃዘን ተቀብለዋታል።
የነጩ አንሶላ ምልክትም ከንቲባ አና አልባ ይገልፁታል " የመንፈሷን ፅዳት እንዲሁም ለዘመናት ህልሟ የነበረው ዶክተር ስትሆን የምትለብሰውን ነጭ መለዮ ልብስ የሚያመላክት ነው።"
የቤት ውስጥ ጥቃት ማሻቀብ
ፈረንሳይ፦ በፈረንሳይ ከጥቃት ጋር ተያይዞ ለእርዳታ የሚደረጉ ጥሪዎች ብዙም አልነበሩም። ነገር ግን የቤት ውስጥ መቀመጥ አዋጁን ተከትሎ የድረሱልኝ ጥሪ በአጠቃላይ በአገሪቷ በሶስት እጥፍ መጨመሩን መንግሥት አስታውቋል። በተለይም በዋና መዲናዋ ፓሪስ ቁጥሩ ከፍተኛ ሆኗል።
መስማት ለተሳናቸው መልእክት መላክ የሚችሉ ሲሆን በቀንም 170 መልእክቶች ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች ይመጣሉ።
በስፔንም ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች አስፈላጊና መሰረታዊ ተብለው ከተፈረጁት ውስጥ ሲሆን በመንግሥትም ከፍተኛ ድጋፍ ይቸረዋል።
ጥቃት ለሚደርስባቸው ሴቶች የእርዳታ የስልክ መስመሮች የተዘረጉ ሲሆን፤ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት 18 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በፈረንሳይ ከስልክና ከመልእክቶች በተጨማሪ በኢሜይል የሚደርሱ መልእክቶች 286 በመቶ፣ እንዲሁም በዋትስአፕ በዘጠኝ ቀናት ብቻ 168 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተዘግቧል።
ህይወትን የሚታደገው 'ማስክ-19'
በስፔን ካናሪ አይላንድስ የሚገኘው የእኩልነት ተቋም 'ማስክ 19' የሚል ዘመቻን ጀምረዋል። ይህም ዘመቻ ጥቃት የደረሰባት ሴት ከቤት የመውጣት መብቷ እንዲከበርላት ያለመ ነው።
በአሁኑ ሰአት የመድኃኒት መደብሮች (ፋርማሲዎች) ሰዎች በነፃነት ከሚሄዱባቸው ቦታዎች አንዱ ነው።
" አንዲት ሴት በቅርብ ወደሚገኝ ፋርማሲ በመሄድ ማስክ 19 የሚለውን የሚስጥር ቃል ብትናገር- ህይወቷ ይድናል" በማለት የዘመቻው ጠንሳሽ ኪካ ፉሜሮ ያስረዳሉ።
እንዲህ አይነት ሴቶች በሚመጡበት ወቅት የፋርማሲው ሰራተኞች ስማቸውን፣ አድራሻና የስልክ ቁጥራቸውን በመመዝገብ ለአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ያሳውቃሉ። ሴቶቹ ቤታቸው በመሄድ መጠበቅ ይችላሉ ወይም ፖሊስና እርዳታ አድራሾች እስኪመጡ ድረስ ባሉበት ቦታ ሆነው መጠበቅ ይችላሉ።

ቴኔሪፍ በሚባል ግዛት ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ከጥቃት አድራሽ ጓደኛዋ ጋር ለሁለት ሳምንታት የቆየች ሲሆን ፋርማሲው በመሄድ ኮዱን (የሚስጥር ቃሉን) ተናግራ ወደ ቤቷ ሄደች። በወቅቱ ጥቃት አድራሽ ጓደኛዋ ሁኔታውን ሳያውቅ ከፋርማሲው ውጭ ሆኖ እየጠበቃት ነበር። የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም ቤቷ በመሄድ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ወስደዋታል።
በስፔኗ ግዛት ግራን ካናሪያ የ78 አመት የዕድሜ ባለፀጋ በባለቤታቸው ተገድለዋል። አሮጊቷ በአገሪቷ ውስጥ በትዳር አጋር የተገደሉ ሁለተኛዋ ሴት ሆነዋል።
"በእድሜ ተለቅ ያሉ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት ሪፖርት ለማድረግ እስከ አስራ አምስት አመታት እንደሚወስዱ" በሴቶች ጥቃት ዙሪያ የመንግሥት ተወካይ የሆኑት ቪኪ ሮዜል ገልፀው " እናውግዘው። ለነሱ ድምፅ እንሁናቸው። ይህም ሕይወትን ይታደጋል" በማለት መልእክታቸን አስተላልፈዋል።
የማስክ 19 ዘመቻ ከመላው ስፔን አልፎ፣ በፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ኖርዌይና አርጀንቲና ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው።
በማድሪድ የሚገኘው የአስፓሺያ ፋውንዴሽን መስራች ቨርጂኒያ ጊል ሴቶች ከጥቃት በተጨማሪ፣ በቫይረሱ የመያዝ ሰቀቀን እንዲሁም ከቤት ወጥተው ሪፖርት ቢያደርጉ ጥቃት አድራሾች የበለጠ ሊጎዱዋቸው እንደሚችሉ ማሰብና የትኞቹ ተቋማት እርዳታ እንደሚሰጡ ለይቶ አለማወቅ ተደራራቢ ችግሮች ብለው ከሚጠቅሷቸው መካከል ናቸው።
አንዳንድ ጊዜም ጥቃት አድራሾች በፖሊስ ቁጥጥር ስር አለመዋላቸውና ኢፍትሃዊ በሆኑ ፍርድ አሰጣጥ ሂደቶች በነፃ መለቀቃቸው ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶችን መከራ ከፍ አድርጎታል።
የአንዳንድ አገራት አመርቂ ስራዎች
በሩሲያ፦ ነዋሪነቷን ያደረገችው ማሪያ (ስሟ ተቀይሯል) ጥቃት በደረሰባት ወቅት ከቤት ልውጣ አልውጣ በሚል መንታ ሃሳብ ልቧ ቆመ።
ከዚህ በፊት ባለቤቷ ምንም አይነት ጥቃት አድርሶባት ባያውቅም የቤት መቀመጥ ውሳኔ መታወጁን ተከትሎ በአንደኛው ቀን ለአስራ ስምንት ሰአታት የቆየ ጥቃት ፈፀመባት።
"በመጀመሪያ ስድብ ነበር። ከዚያም እቃ መሰባበር፣ በኋላም እቃ እያነሳ በኔ ላይ እንዲሁም ልጆቼ ላይ መወርወር ጀመረ" በማለት ለቢቢሲ የተናገረችው ማርያ " ቤት ውስጥ አለ የሚባል እቃ ሁሉ ነው ያደቀቀው። የአሳ ማስቀመጫ እንዲሁም ፍሪጅ አልቀረውም። ልጆቼ ደንግጠው እየተንዘፈዘፉ ነበር"
ለዚህ ሁሉ መቀጣጠሉ ምክንያት የሆነው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስራ መስራት አይቻልም የሚለውን ውሳኔ ተከትሎ ገቢው በመቀነሱ ነው ትላለች።
እንዲሁ በንዴት ግሎ ቢራ ሊገዛ በወጣበት ወቅት ወደ ፖሊስ ደወለች። "ፖሊሶች ቤቱ የሱ ስለሆነ እንደማያስወጡት ነገሩኝ። ለራሴም ሆነ ለልጆቼ ሌላ መጠለያ ፈልጊ አሉኝ" ብላለች።
በዴንማርክም የቤት መቀመጥ አዋጁን ተከትሎ የእርዳታ ጥሪዎች በእጥፍ ጨምረዋል። ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ጥቃት ለሚፈሩ ሴቶች መጠለያ የሚሆን 55 ስፍራዎችን ለአራት ወራት ያህል ያዘጋጀ ሲሆን ትምህርት ቤቶችም ለሴቶች መጠለያ በራቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
"በማንኛውም መንገድ መጠለያ እንዲኖራቸው እናደርጋለን" ያሉት ሱዛን ላማሃውጌ ሲሆኑ በሴቶች መብት አቀንቃኞች የሚመራ አንድ የድንገተኛ ማእከልም መሪ ናቸው።
በቤልጂየም በሴቶችና ቤተሰብ ጥቃት ዙሪያ የሚሰሩት ጂን ሉዊስ ሲሞንስ ሶስት እጥፍ እንደጨመረ ተናግረዋል።
"በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ደውላ ባለቤቷ ሲጋራ ሊገዛ እንደወጣና ለማውራት አስራ አምስት ደቂቃ ብቻ እንዳላት ነገረችኝ። ድምጿ በፍራቻ የተሞላ ነው፤ እየተንቀጠቀጠችም እንደሆነ ያስታውቃል። በፍጥነት አወራን። ስናመጣት በከፍተኛ ሁኔታ ደብድቧታል። ፊቷ አብጧል። አይኗንም መግለጥ አልቻለችም"
ቤት የመቀመጥ ሁኔታ ጥቃት አድራሹን የበለጠ ተዳባዳቢ ያደረገው ሲሆን፤ ጂን ሉዊስም ህይወቷ ሌላ አደጋ ውስጥ ከመግባቱ በፊት እንድታመልጥ ረዷት።
ቤት መቀመጥ ደህንንት ያልሆነበት ሁኔታ
በኮሮና ቫይረስ እያዛለሁ የሚለው ስጋት ጥቃት የሚደርስባቸውን ሴቶች ለመርዳት ከፍተኛ እክል እንደፈጠረ በአውሮፓ የስርአተ ፆታና የሴቶች ጥቃት ጉባኤ ኃላፊ ማርሴሊን ናውዲ ይናገራሉ።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በቫይረሱ እያዛለሁ በሚል ስጋት የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ ቀርተዋል፤ ህክምና የሚሰጡ ቦታዎችም የተወሰኑ ሆነዋል።
"ጥቃት የደረሰባቸው መጠለያ ቦታዎችም ቫይረሱ ይዛመታል በሚል ስጋት ሴቶችን መቀበል አቁመዋል" ይላሉ
ከዚህም በተጨማሪ ለወደፊቱም በቫይረሱ ስራ ያጡ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው ላይ ጥገኛ መሆናቸው ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችልና፤ ከጥቃትም ለማምለጥ አዳጋች እንደሚያደርገው አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በአስር ሺዎችን ቫይረሱ በገደለበት የአውሮፓ ምድር በህይወት ለመቆየት ቤት መቀመጥ ትልቅ አማራጭ ነው። ነገር ግን ከጥቃት አድራሾቻቸው ጋር በእስርና በስቃይ ላይ ላሉ ሴቶች ግን ቤት መቆየት አደጋ ነው፤ መውጣትም የራሱ አደጋ አለው። በዚህም ምክንያት አማራጭ የሌለው አማራጭ ውስጥ ገብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Olesya Volkova
በአውሮፓ የምትገኙ ሴቶች ድንገት ጥቃት ቢደርስባቸው እነዚህን ስልኮች በመጠቀም እርዳታ ልታገኙ ትችላላችሁ።
ስፔን፡ 016፣ ኢሜይል [email protected]፣ የስነ ልቦና አገልግሎት በዋትስ አፕ፣ +34 682 916 136/+34 682 508 507፣ ፋርማሲ ስትገቡም ማስክ- 19 (ማስካሪላ 19) በማለት እርዳታ ልታገኙ ትችላላችሁ
ዩኬ፦ 0808 2000 247
ጣልያን፦1522
ቤልጂየም፦ 0800 30 030፣ በፈረንሳይኛ ወይም በደች ቋንቋ ከሆነ 1712
ፈረንሳይ፦3919፣ ድንገተኛና አስቸኳይ ከሆነ 114 መልዕክት መላክ ትችላላች ወይም 17 ደውሉ
ሩሲያ፦8 800 700 06 00
በመላው አውሮፓ ዉሜን ኤጌንስት ቫዮለንስ ዩሮፕ ኔትወርክን (Women Against Violence Europe (WAVE) Network) ልትፅፉ ትችላላችሁ














