ከኮሮናቫይረስ እያገገሙ ያሉ ምን ይላሉ? የ2 ወጣት ሴቶች ታሪክ

ጄሲ ክላርክ ሆስፒታል ውስጥ እያለች
የምስሉ መግለጫ, ጄሲ ክላርክ ሆስፒታል ውስጥ እያለች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ላይ ተስፋፍቶ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ ቢሆንም የዚያኑ ያህል ቁጥራቸው በርካታ የሆኑት ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል። ነገር ግን በሽታው በአብዛኛው በእድሜ የገፉ ሰዎችን እንደሚያጠቃ ቢነገርም በርካታ ወጣቶች እየተያዙ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ከእነዚህም ውስጥ በበሽታው ክፉኛ ታመው ወደ ሆስፒታል በመግባት ያገገሙ ሁለት ወጣቶች ስለበሽታውና ስላለፉበት ሁኔታ እንደሚከተለው ይተርካሉ።

"ለነፍሴም ለልጄም ተጨነቅኩ"

ካረን እባላለሁ፤ እንግሊዝ ኬንት ነው የምኖረው። የ6 ወር እርጉዝ ነ ነኝ።

በየካቲት ወር 2ኛ ሳምንት ድንገት ሳል ጀመረኝ። ቀጥሎ ደግሞ አተነፋፈሴ ተቀየረ። ቶሎ ብዬ 999 ደወልኩ። በደቂቃዎች ውስጥ አምቡላንስ ቤቴ ደጅ ደረሰ። ለመተንፈስ ስለተቸገርኩ ወደ ሆስፒታል የደረስኩት አምቡላንስ ውስጥ በኦክሲጂን ታግዤ ነበር።

ምርመራ ሲደረግልኝ ኮቪድ-19 እንደሆነ ደረሱበት። ሁለቱም ሳምባዎቼ በሳምባ ምች ተጠቅተዋል።

ለብቻዬ ተነጥዬ አልጋ ያዝኩ። ማንም አይጎበኘኝም። ማንም እንዲያየኝ አይፈቀድም። ይህ ቀላል አይደለም። እንዴት ከባድ ጊዜ እንዳሳለፍኩ!

በወቅቱ ከአልጋዬ ጋ ተጣብቄ መጸዳጃ ቤት እንኳ መሄድ አልችልም ነበር። የአልጋውን አንሶላ የሚቀይሩልኝ ራሱ እኔን ወደ ሌላ አቅጣጫ በጎኔ ገልብጠው ነው።

ትንፋሽ ደጋግሞ ያጥረኝ ነበር፤ የምሞት የምሞት ስለሚመስለኝ ልክ መተንፈስ ሲያቅተኝ ቶሎ ጤና ረዳቶቹን ድረሱልኝ እላለሁ። እነሱ ለባብሰውና በሽታው እንዳይተላለፍባቸው ጭምብላቸውን በጥንቃቄ አጥልቀው እስኪመጡ ጭንቅ ነው።

ሻል ባለኝ ቁጥር ከቤተሰቤ ጋር በስልክ ለረዥም ደቂቃዎች አወራለሁ። ያን የማደርገው ፍርሃትን ለማሸነፍ ስል ነው። ልሞት እንደምችል ስለተረዳሁ ይህንኑ እነግራቸዋለሁ፤ ቤተሰቤቦቼ ለማይቀረው ክፉ ቀን መዘጋጀታቸውን ይነግሩኛል፤ በዚያ መጠን ግን ተስፋንም ይሰጡኛል።

ለእያንዳንዷ እስትንፋሴ እታገል ነበር፤ በዚያ ላይ ሁለት ነፍስ ነበርኩ፤ ለሁለት ነፍስ ነበር የምታገለው። ልጄ እንዳይሞትብኝ አብዝቼ እጨነቅ ነበር።

በሂደት እያገገምኩ ስመጣ ከሆስፒታል መውጣትና ቤቴ ውስጥ ራሴን አግልዬ ማገገም እንደምችል ተነገረኝ።

መጀመሪያ ከሆስፒታሉ በር ወጥቼ ንፋስ ፊቴን ሲገርፈኝ የተሰማኝን ደስታ በቃላት ልገልጸው አልችልም።

አስታውሳለሁ ከባሌ ጋር ነበርኩ። የፊት ጭንብል አጥልቀናል። የመኪናው መስኮት ክፍት ነበር። ድንገት ነፋሱ ሲመታኝ አቤት እንዴት ደስ እንዳለኝ!

ለእያንዳንዷ ጥቃቅን ስጦታ ማመስገን እንደጀመርኩ ያወቅኩት ያኔ ነበር።

ካረን ከባለቤቷ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ካረን ከባለቤቷ ጋር

እየፈራሁት ነው የያዘኝ…

ጄሴ ክላርክ እባላለሁ። 26 ዓመቴ ነው። አገሬ እንግሊዝ፤ ሼፍልድ ነው። ኮሮናቫይረስ ቢይዘኝ ችግር ላይ እንደምወድቅ ገና ከመጀመርያው ታውቆኝ ነበር። ምክንያቱም ከአምስት ዓመት በፊት ኩላሊቴን ታምሜ አስወጥቻለሁ።

ኮሮናቫይረስ ደግሞ ተጨማሪ ህመም ባለበት ሰው እንደሚበረታ ስለማውቅ…

ምን ዋጋ አለው ታዲያ! ድንገት ያስለኝ ጀመር። ቀጠለና ለመተንፈስ ያዳግተኝ ጀመር።

ሆዴ አካባቢና ጎንና ጎኔ ሕመም ተሰማኝ። እውነት ለመናገር የሆነ ሰው በዱላ የደበደበኝ ያህል ነበር የሚሰማኝ።

ጠቅላይ ሚኒስራችን ቦሪስ ጆንሰን 'ቤት አርፋችሁ ተቀመጡ' ያለ ቀን እጮኛዬ ወደ ድንገተኛ ክፍል ወሰደኝ። እዚያ እንደደረስን ቶሎ ተለያየን፤ ምክንያቱም ተራራቁ ስለተባለ። አብሮኝ ሊገባም አይችልም።

በእውነቱ ብቻዬን መሆን በጣም ነበር ያስፈራኝ፡፡ የሆነ ሰው አብሮኝ እንዲሆን፤ አለሁልሽ እንዲለኝ ነበር ፍላጎቴ።

በድንገተኛ ክፍል አረንጓዴ የፊት ጭንብል ተሰጠኝ። ከዚያ ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ወደተዘጋጀ ስፍራ ወሰዱኝ። እዚያ ለደህንነታችን ሲባል አልጋችን ተራርቆ ነበር የተዘረጋው።

እስከዚያ ሰዓት ድረስ ኮቪድ-19 እንዳለብኝ አልታወቀም። ምክንያቱም አልተመረመርኩማ። ሐኪሜ እንደነገረኝ ሁሉንም ድንገተኛ ክፍል የመጣን ሰው ለመመርመር በቂ መሣሪያ የለም።

በዚያ ሰዓት ሳምባዬ አካባቢ የማቃጠል ስሜት ነበር የሚሰማኝ። የህመም ማስታገሻ ተሰጠኝ። ለ6 ሰዓት ድንገተኛ ክፍል ቆየሁ። እጮኛዬ ያን ሁሉ ሰዓት መኪና ውስጥ ደጅ እየጠበቀኝ ነበር።

በመጨረሻ ኮሮናቫይረስ ተገኘብኝ። እጮኛዬ ሥራው ከህመምተኞች ጋር ስለሚገናኝ ምናልባት እሱ አስተላልፎብኝ እንደሆነ እገምታለሁ። ምክንያቱም እሱ ምልክት የማያሳይ የኮሮናቫይረስ ተጠቂ (asymptomatic) እንደሆነ ተደርሶበታል።

ከቀናት ህክምና በኋላ ከሆስፒታል ብወጣም አሁንም ራሴን ለይቼ በማገገም ላይ ነው ያለሁት።

የተረዳሁት ነገር ቢኖር እኛ ወጣቶችም ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንደሆንን ነው። ኮሮናቫይረስ የአዛውንቶች በሽታ ነው የሚለው አመለካከት ፉርሽ ነው።

ኮሮና
Banner