የኮሮናቫይረስ ወርረሽኝ የሴቶችን ሰቆቃ እያባባሰ ይሆን ?

ስዕል

የፎቶው ባለመብት, JAMES MOBBS/BBC

ብዙ አገራት በራቸውን ቆልፈዋል፤ መሪዎች ዜጎቻቸው ላይ በር ከርችመዋል። እንደ ፊሊፒንሱ መሪ ያሉት ደግሞ ደጅ የወጡ ዜጎችን ተኩሱባቸው እስከ ማለት ደፍረዋል።

እያንዳንዱ ቤት የያዘው አመል ብዙ ነው። አንዳንድ ሰዎች ቤት ሲውሉ የሚያሳዩት ባህሪ ግራ ነው። በተለይም በትዳር ውስጥ በሴቶች ላይ ጥቃት የማድረስ አመል የጸናባቸው ወንዶች ቤት ሲውሉ ለሴቶች ሰቀቀን ይሆናሉ።

ቢቢሲ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከባሎቻቸው ጋር ቤት እንዲውሉ በመገደዳቸው መከራቸውን እየበሉ ያሉ ሁለት ሴቶችን አነጋግሯል። ለደኅንነታቸው ሲል ስማቸውን ተቀይሯል።

1. ታ፤ ሕንድ

ባሌ ፀጉሬን ይዞ ከግድግዳ ጋር ያጋጨኛል…

ጠዋት 11፡00 ሰዓት እነሳለሁ። ባሌ ከጎኔ ቁጭ ብሎ ያንቋርራል። ሲያንኮራፋ ጎረቤት ይቀሰቅሳል።

ትናንትና ማታ ሰክሮ ነው የገባው።

ባጃጅ ነው የሚነዳው። በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሰው ውጭ ስለማይኖር ገቢያችን ቀንሷል። 1500 ሩፒ [የህንድ ገንዘብ] ያገኝ ነበር። አሁን ያ የለም። ስለዚህ ይበሳጫል።

"እስከመቼ ነው እንዲህ ቤት ቆልፈው የሚቀልዱብን" እያለ ግድግዳውን በቡጢ ይነርተዋል። አጠገቡ ያለ ብርጭቆ ይሰብራል። እሱ ይህን ባደረገ ቁጥር ልጆቼ ይበረግጋሉ፤ ጉያዬ ውስጥ ይደበቃሉ።

ቁጣው ሲበርድለት ሁላችንም ወደምንተኛባት ፍራሽ ሄዶ ይጋደማል። በድጋሚ እንቅልፍ ይጥለዋል። ለጊዜውም ቢሆን እፎይ እንላለን።

እሱ ቦግ ባለ ቁጥር ልጆቼን ማረጋጋት ለእኔ ፈተና ነው። በእርግጥ እንዲህ ሲቆጣና ቤቱን በአንድ እግሩ ሲያቆመው ሁልጊዜም ያዩታል።

ነገር ግን ቀኑን ሙሉ ቤት ስለማይውል የእፎይታ አፍታ ነበራቸው። አሁን ኮሮናቫይረስ ከመጣ በኋላ እያንዳንዱ ቀን ጭንቅ ሆኗል።

አንዳንድ ጊዜ ወደ ግድግዳው እያላጋ የሚሰብረው ነገር ሲያጣ የእኔን ጸጉር እየጎተተ ከግድግዳው ጋር ያላትመኛል። ልጆቼ ፊት ነው ታዲያ ይሄ ሁሉ የሚሆነው።

የጊታና የልጆቿ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, JAMES MOBBS/BBC

ባሌ ለመጀመርያ ጊዜ የደበደበኝ የሠርጋችን ዕለት ነበር። ነገሮች ይሻሻላሉ ስል ቆየሁ። በኋላ አምርሬ ጥዬው ልጠፋ ስል ልጆቼን አልሰጥም አለኝ። ልጆቼን ለእሱ ጥዬ ወዴት እሄዳለሁ? አርፌ ተቀመጥኩ።

የምንኖረው ሞሃላ በሚባል የድሆች ሰፈር ነው። ውሃ ለማምጣት በየቀኑ ሩቅ ኪሎ ሜትር እጓዛለሁ። ከዚያ ትንሽ ከጎረቤቶቼ ጋር አወራና አትክልት ቸርቻሪዎች ሲመጡ ከእነሱ አስቤዛ እገዛለሁ።

ለዚያች ቀን ብቻ የሚሆን አስቤዛ ከገዛሁ በኋላ ምግብ አበስላለሁ። ባሌን ቁርስ አብልቼው ወደ 1 ሰዓት ገደማ ወደ ሥራ ይሄዳል። ከዚያ ለምሳ ይመለሳል። በልቶ ትንሽ ከተኛ በኋላ ወደ ሥራ ይወጣል።

ነገሮች መለወጥ የጀመሩት ከኮሮናቫይረስ በኋላ ነው። ልጆቼ ቤት መዋል ሲጀምሩ እሱም ነውጠኛ ሆነ። ልጆቹ ሲጫወቱ ይበሳጫል። ብስጭቱን የሚወጣው ግን በእኔ ላይ ነው፡፡ መጀመርያ እነሱ ላይ ይጮኻል። ፈርተውት ጸጥ ይሉና እንደገና ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ። የልጅ ነገር!

ከዚያ ብስጭቱን አጠረቃቅሞ እኔ ላይ ይወጣዋል። በትንሽ ነገር ነው የሚናደደው። ለምሳሌ የሻይ ኩባያው ለምን ከጠረጴዛው አልተነሳም ብሎ አገር ይያዝልኝ ሊል ይችላል። ልጆቹ ላይ ሲጮኽ ትኩረቱን ለማስቀየር አውቄ የባጥ የቆጡን አወራለሁ። ልጆቼ እንዳይደነግጡብኝኮ ነው. . . .

እንደዛሬው በኮሮናቫይረስ ምክንያት አብረን መዋል ከመጀመራቸው በፊት ልክ እግሩ እንደወጣ ወደ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። የምማረው ልብስ ስፌት ነው። በተጨማሪም ማንበብና መጻፍ ያስተምረኛል ሰፈሬ ውስጥ ያለ አንድ ማኅበር፡፡

እኔ እየተማርኩ እንደሆነ ባሌ ቢያውቅ ይገድለኛል።

አሁን ምኞቴ የራሴ ገቢ ኖሮኝ ልጆቼን ይዤ ከእርሱ መለየት ብቻ ነው። ኮሮናቫይረስ እንዲጠፋ የምመኘውም ባሌ ቀን ቀን ወደ ሥራ እንዲሄድ ከመሻት ነው፡፡

2. ካይ፤ ኒው ዮርክ

አባቴ ማታ ማታ የወሲብ ፊልም ያያል. . .

ካይ ወጣት ሴት ናት። ጥቃት የሚያደርስባት ደግሞ አባቷ ነው። ስልኳን መዥረጥ አድርጋ አወጣችና "ማሚ ካንተ ጋር እንድቆይ ብላኛለች" የሚል ጽሑፍ ላከች። ከአባቷ ፈጣን ምላሽ አገኘች።

"ምንም ቸግር የለም፤ ነይ" የሚል።

ካይ ታሪኳን እንዲህ ትቀጥላለች።

ባለፈው ሳምንት መቼም አልመለስበትም ወዳልኩበት የአባቴ ቤት ተመለስኩ። ልክ እንደገባሁ መላ ሰውነቴ እንደ ሬሳ ቀዘቀዘ። ስሜት አልባ ሆንኩ። አልናገር አልጋገር።

አባቴ ለዓመታት በስሜትም በአካላዊ ጥቃትም ሲጎዳኝ ነው የኖረው።

መጀመርያ ኮሮናቫይረስ መጣ ሲባል ተራ ጉዳይ ነበር የመሰለኝ። ቫይረሱ ኒው ዮርክ መድረሱ ሲዘገብ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ።

እናቴ አንድ መደብር ውስጥ ነበር የምትሰራው። ከብዙ ደንበኞች ጋር መገናኘት ትገደዳለች። ወዲያውኑ ግን የምትሰራበት መስሪያ ቤት በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሥራ መዝጋቱን አስታወቀ።

ድርጅቱ ሲዘጋ እናቴ በሰዓት 15 ዶላር ገቢዋን አጣች። የጤና መድኅኗ ሊቃጠል አምስት ቀናት ብቻ ነበር የቀሩት። ምን ተሻለ?

በጭንቀት የአእምሮ ታማሚ ሆነች። ድሮም አለፍ አለፍ እያለ ይነሳባት ነበር።

የካይ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, JAMES MOBBS/BBC

ከኮሮናቫይረስ በኋላ ግን እየባሰባት መጣ። ድንገት ትጮኻለች። "ውጪልኝ፤ አባትሽ ጋ ሂጂ፤ ውጪ!" እያለች።

ወደ አባቴ በፍጹም መሄድ አልፈለኩም። አንድ ክፍል ቆልፌ ተቀመጥኩ። ሆኖም ልታስቀምጠኝ አልቻለችም። በሩን እየደበደበች "አሁንም እዚህ ነው ያለሽው? ውጪልኝ አላልኩም! አይንሽን እንዳላየው" ትለኛለች።

እናቴ አእምሮዋን ስለሚያማት ነው እንጂ አባቴ የሚያደርስብኝ ጥቃት ጠፍቷት አይደለም። አባቴ ገና ድክ ድክ ማለት ሳልጀምር ነበር ሁሉን አይነት ጥቃት ይፈጽምብኝ የነበረው። ጠባሳው አሁንም አለ። ሆኖም ያደረሰብኝን ሁሉ ለእናቴ ነግሪያታለሁ ማለት አልችልም።

ኮሮናቫይረስ ከመምጣቱ ቀደም ብሎ በልጅነቴ አባቴ ያደረሰብኝን ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ለማከም ቴራፒስት ሐኪም ጋር እመላለስ ነበር። ጥሩ መሻሻል እያሳየሁ ሳለ ነው ይህ ወረርሽኝ የመጣው። ሐኪም ቤቱም ተዘጋ። ምንም አማራጭ የለም፤ መውደቂያ ስላጣሁ ወደ አባቴ ሄድኩ።

እዚህ አባቴ ጋ ከመጣሁ ጀምሮ አውርተን አናውቅም። ቀን ላይ በኮምፒውተሩ ዜና ሲያይ ይውላል። ማታ ማታ ደግሞ የወሲብ ፊልሞችን ሲያይ እመለከተዋለሁ።

ጠዋት መነሳቱን የማውቀው የፍራፍሬ ጭማቂ ማሽኑ ሲጮኸ ነው። ይህ የማሽን ድምጽ ለእኔ በጣም አስቀያሚ ደውል ነው። ምክንያቱም የአስጨናቂው ቀን መጀመርን ስለሚያረዳኝ።

ቀኑ ብቻ ሳይሆን ማታም ጭንቅ ነው። የክፍሌ በር አይዘጋም። ስለዚህ እንቅልፍ አልባ ሌሊት ነው የማሳልፈው። አባቴ በማንኛውም ሰዓት ገብቶ ጥቃት ሊፈጽምብኝ እንደሚችል አውቃለሁ።

ከክፍሌ የምወጣው ወይ ለሽንት ነው ወይም ደግሞ ሲርበኝ ማዕድ ቤት ምግብ ለማብሰል ነው። ከአባቴ ጋር በፍጹም ላለመነጋገር እሞክራለሁ፡፡ ምክንያቱም ጥቃት የሚሰነዝርብኝ ብዙውን ጊዜ ተነጋግረን ሳንግባባ ስንቀርና ሲናደድብኝ ነው።

የኮሮና ወረርሽኝ ቶሎ እንዲቆም እሻለሁ። ለሌላ አይደለም። ቶሎ ወደ እናቴ ለመመለስ። አባቴን ማየት አልፈልግም! ሕመም ነው!

ኮሮና
Banner