ኮሮናቫይረስ የዓለም የምግብ አቅርቦት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዙ አገራት እንቅስቃሴ ገተዋል። ይህን ተከትሎም በመደብሮች የምግብ እጥረት መከሰቱ እየተነገረ ነው።
በሌላ በኩል ሬስቶራንቶችና ሌሎችም የመስተንገዶ አገልግሎት ሰጪዎች በመዘጋታቸው፤ ምግብ አምራቾች ክምችታቸው ሊበላሽ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በምግብ አቅርቦት ዘርፍ ላይ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ከነዚህ አምስቱን እንመልከት።
1. ወተት ተትረፍርፏል
አንዳንድ አገራት ካፌዎቻቸውን ዘግተዋል። ቡና እተሸጠ አለመሆኑ ደግሞ የወተት ምርት እንዲትረፈረፍ ምክንያት ሆኗል።
የአሜሪካ የወተት ተዋጽኦ አምራቾች እንደሚሉት፤ ከገዢዎች ጋር እየተገናኙ ስላልሆነ በየቀኑ ወደ 14 ሚሊዮን ሊትር ወተት ለመድፋት ተገደዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የወተት ተዋጽኦ አምራቾች ማኅበር ኃላፊ ፒተር ኤሊቪስ፤ በየሳምንቱ አምስት ሚሊዮን ሊትር ወተት ከጥቅም ውጪ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
አርሶ አደሮች ምርታቸውን መሸጥ አለመቻላቸው ገቢያቸውን እንደሚያናጋውም ኃላፊው ይናገራሉ።
የስኮትላንድ አርሶ አደሮች የወተት ምርታቸውን እንዲቀንሱ ተነግሯቸዋል።
2. ሰብል እየባከነ ነው
አንዳንድ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በቀጥታ ለመደብሮች ለማስረከብ ቢሞክሩም፤ የገበያ ፍላጎት በመቀየሩና ምርት ከመጠን በላይ በመከማቸቱ ውጤታማ አልሆኑም።
ኒው ዮርክ ታይምስ ያነጋገረው ዶሮ አምራች፤ በየሳምንቱ 750,000 እንቁላል ለማሶገድ ተገድጃለሁ ይላል።
አንድ አርሶ አደር ደግሞ የሽንኩርት ምርታቸው ባለበት በስብሶ ወደ ማዳበሪያነት እንዲለወጥ ትተውታል።
የሕንድ ሻይ አምራቾችም የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል።
3. በቂ ሠራተኞች የሉም
ከምርት መትረፍረፍና ለገበያ ማቅረብ አለመቻል በተጨማሪ፤ ሠራተኞች አለማግኘትም አርሶ አደሮችን እየፈተነ ነው።
አገር አቀፍ እንቅስቃሴ የማቆም ውሳኔና ማኅበራዊ ርቀትን የመጠበቅ ሕግ ብዙዎች ሥራ እንዲያቆሙ ምክንያት ሆኗል።
ባለፈው ሳምንት፤ ጀርመን በሺዎች የሚቆጠሩ የሮማንያ እና ፖላንድ ሠራተኞች ሰብል እንዲሰበስቡ ፍቃድ ሰጥታ ነበር።
4. የሸማቾች ባህሪ ተቀይሯል
በወረርሽኙ ሳቢያ ሸማቾች የሚገዟቸው የሸቀጥ አይነቶች ተቀይረዋል።
ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ብዙዎች ቤት እያበሰሉ ስለሆነ የዱቄት ፍላጎት ጨምሯል።
ፈረንሳውያን በበኩላቸው የፋብሪካ ውጤት የሆኑ ምግቦችን ቀንሰዋል። ይህም ጤናማ አመጋገብ ማዘውተር በመጀመራቸው አልያም ከአነስተኛ ቸርቻሪዎች መግዛት ስለጀመሩም ሊሆን ይችላል።
የፈረንሳይ የግብርና ሚንስትር የምግብ መደብሮች እንዲከፈቱ ጠይቀዋል። ቀድሞ የተዘጉት ማኅበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ አይቻልም በሚል ፍራቻ ነበር።
5. የተከማቸው ምግብ ጥቅም ላይ አልዋለም
የመስተንግዶ ዘርፎች መዘጋት የተከማቹ ምግቦች እና መጠጦች ጥቅም አልባ ለመሆናቸው ምክንያት ነው።
በእርግጥ የአንዳንድ ምግቦች ሽያጭ ጭማሪ አሳይቷል።
ለአብነት ያህል በ38 በመቶ ቀንሶ የነበረው የአሜሪካ የብርቱካን ጭማቂ ገበያ አሁን ላይ መሻሻል አሳይቷል።
የ ‘አግዚክሮፕ’ የገበያ ጥናት ባለሙያ ስቴፈን ኢንስ እንደሚሉት፤ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያሳድጉ ምግቦች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ነገር ግን በረራዎች መታገዳቸው የብርቱካን ጭማቂ የመሰሉ ምርቶች በስፋት እንዳይከፋፈሉ አድርጓል።













