ኮሮናቫይረስ፡ ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱት ስደተኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከሳኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ እየተደረጉ ያሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም አለ።
በውጪ ጉዳይ ሚንስትር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ዮሐንስ ሾዴ፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳኡዲ መንግሥት ጋር ባለው ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ሲመለሱ ነበር ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ በሆነበት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ ከተገነባቸው ሰዎች መካከል በርካታዎቹ ከውጪ አገራት በተለይ ደግሞ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በዋናነት በዱባይ በኩል የመጡ መሆናቸው በስፋት ሲነገር ቆይቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሳኡዲ አረቢያ በአገሯ የሚገኙ 'ሕገ ወጥ' ያለቻቸውን ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገች መሆኑ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።
አገሪቱ በግዛቷ ውስጥ የሚታየውን የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ባለችበት በዚህ ወቅት ስደተኞችን መመለሱ እየተደረገው ባለው ጥረትና በጤና ሥርዓቷ ላይ ተጨማሪ ጫናን ሊፈጥር ይችላል የሚሉ ስጋቶች መነጋገሪያ ሆኗል።
ነገር ግን ባለፈው ዓመት በርካታ ስደተኞች ከሳኡዲ እና ከሌሎች አገራት መመለሳቸው የሚጠቅሱት አቶ ዮሐንስ ስደተኞቹ አሁን እተመለሱ ያሉት “ኮሮናቫይረስ ስለተከሰተ አይደለም” ብለዋል።
አቶ ዮሐንስ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች መመለሳቸውንም ያስታወቁ ሲሆን፤ ከሳኡዲ መንግሥት ጋር በሚደረግ ግነኙነት መሠረት ስደተኞቹ ከሳኡዲ ከመነሳታቸው በፊት ለ14 ቀናት ተለይተው የሚቆዩበት ቦታ ዝግጁ ሲሆን እንደሚመጡ ተናግረዋል።
የሰደተኞቹ ወደ አገር ቤት መመለስ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት እንዲሁም የኮሮናቫይረስ መከላከል አቅም ላይ ጫና አያሳድርም ወይ ተብለው የጠየቁት አቶ ዮሐንስ፤ ሰደተኞቹ የሚመለሱት ከሳኡዲ መንግሥት ጋር የሚደረግ ንግግርን ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞቹ ማረፊያ ቦታ ካዘጋጀች በኋላ እንደሚላኩ ጠቅሰዋል።
አቶ ዮሐንስ ጨምረውም “የሳኡዲ መንግሥት በተቻለው አቅም እዚያ ለሚገኙት ድጋፍ እያደረገ ነው። ምርመራም እያደረገ ነው። ወደዚህ የሚመጡትም ተመርምረው ነው እየተላኩ ያሉት” ብለዋል።
በዚህ ወቅት ስደተኞችን አንቀበልም ለማለት አስቸጋሪ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ዮሐንስ “አንድ ሉዓላዊ አገር በሕገ-ወጥ መንገድ የሄደውን ዜጋህን ውሰድ ሲልህ ‘አይ አንቀበልም’ ማለት አንችልም” ብለዋል።
ሰደተኞቹ በሳኡዲ መንግሥት ወጪ በልዩ በረራ እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመው፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተቋቋመው ግብረ ኃይል ደግሞ ስደተኞቹ ወደተዘጋጁላቸው ስፍራዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።
ተመሳሽ ስደተኞቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 6 ኪሎ ካምፓስ ጨምሮ በሆቴሎች እንዲያርፉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በቻናይ በሚገኙ አፍሪካውያን ላይ ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ መገለል እና መድሎ እየደረሰ ነው የሚሉ ሪፖርቶች በስፋት ተሰምተዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚንሰቴር በቻይና በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰ መገለል ካለ የተጠየቁት አቶ ዮሐንስ፤ በቻይና ከ100-150 የሚገመቱ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ብዙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አለመኖሩን ተናግረዋል።
“ገና መጀመሪያ ላይ የቫይረሱ ስርጭት ሲጀምር የቻይና መንግሥት ከዜጎቹ በላይ ለኢትዮጵያውን ተማሪዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ጥበቃ ተደርጎላቸው አንድም ተማሪ በቫይረሱ አልተያዘም" ብለዋል። "በዚህም የቻይና መንግሥት ሊመሰገን ይገባል” ብለዋል።














