ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ ጥላ የወጣቻቸው የዓለም ድርጅቶች እነማን ናቸው?

ዶናልድ ትራምፕ ዋይት ሐውስ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጋር ሆድና ጀርባ እየሆነች ነው። የዚህ አንዱ መገለጫ ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቷ ነው።

የቅድመ ትራምፕ አሜሪካ የምትታወቀው ዓለም አቀፍ ተቋማትን በመደገፍና ዓለም አቀፍ ወሳኝ ኩነቶችን በማስተባበር፣ የትብብር ማዕቀፎችን በማርቀቅና በማዋቀር ነበር።

ትራምፕ ግን በተቃራኒው እየሄዱ ይመስላሉ። እንዲያውም አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራትን ተሰሚነት ጥያቄ ውስጥ እየከተቱት መጥተዋል የሚሉም ድምጾች ይሰማሉ።

ለዚህ ማሳያ ደግሞ የአውሮፓ አገራት ናቸው።

ለአሜሪካ የማያወላዳ ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁት የአውሮፓ አገራት የትራምፕ አካሄድ እያስኮረፋቸው በመምጣቱ ከእርሳቸው ጋር መስማማት ከባድ ነው እስከማለት ደርሰዋል። ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአውሮፓ አገራት በበቂ ገንዘብ አያዋጡም በሚል ሲተቹ ነበር።

ጥምረቱ ትራምፕ ከመጡ በኋላ የድሮ የትብብር ጥንካሬው እርቆታል ይላሉ ታዛቢዎች።

ዛሬ ዶናልድ ትራምፕ ከዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ጋር በይፋ መኳረፋቸውን አሳውቀዋል።

ሆኖም ግን እርሳቸው ከምድራችን አገራት የትብብር መድረክ አገራቸውን ሲያርቁ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ለምሳሌ P5+1 በሚል የሚታወቀው የ2015 የኢራን የኒክሌየር ስምምነት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያና ቻይና የፈረሙት ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ የተናጥል እርምጃ በመውሰድ ከስምምነቱ ሲወጡ አንዳቸውም ድጋፍ አልሰጧቸውም።

ከዚያ ይልቅ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮንና የጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ትራምፕን ለማሳመንና ወደ ስምምነቱ እንዲመለሱ ለማድረግ ደፋ ቀና ብለው ነበር። ዶናልድ ትራምፕ ግን አልሰሟቸውም።

ስምምነቱንም "የኦባማ ኮተት" ሲሉ አጣጥለውታል።

ዶናልድ ትራምፕ "አሜሪካ ትቅደም" በሚለው መርሃቸው እየተገዙ ከብዙ አገራትና ተቋማት ጋር መቃቃራቸው እሙን ነው።

አሁን ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም ጋር መካረር መግባታቸው ለፖለቲካ ተንታኞች ሌላ ትርጉም የሰጠ ነው።

ሰውየው በቤት ውስጥ በጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ "ለወረርሽኙ መዘናጋትን አሳይተዋል" በሚል ክፉኛ እየተተቹ ሲሆን ይህን ተከትሎ እፎይታ ለማግኘት ትራምፕ በእርሳቸው ላይ የሚወርደውን ውርጅብኝ ወደ ዓለም ጤና ድርጅት ለማሸጋገር የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

በርካታ የዓለም መንግሥታትም ትራምፕ ለድርጅቱ መዋጮ ላለማድረግ መወሰናቸውን አውግዘዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ጊዜውን ያልጠበቀ ውሳኔ" ሲሉ እርምጃውን ነቅፈውታል።

አሜሪካ ዶ/ር ቴድሮስ ለሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት የገንዘብ መዋጮ አላደርግም ብላ ከጸናች ከአባልነት ትሰረዛለች ማለት ነው።

ሆኖም አሜሪካ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጥላ ስትወጣ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም። በትንሹ ከምስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም ስምምነቶች ወይም ማዕቀፎች ራሷን አግልላች።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

1ኛ. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን

አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስልን በሠኔ 2018 ጥላ ወጥታለች። ምክንያቷ ደግሞ ካውንስሉ የምንጊዜም አጋሬን እስራኤልን አስቀይሞብኛል በሚል ነው። ካውንስሉ እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምታደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲተች ቆይቷል።

በዚያን ጊዜ በተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ ቋሚ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ካውንስሉ ለእስራኤል ጥላቻ አለው፤ በዚያ ላይ ግብዝ ነው ስለዚህ አባል መሆን አንሻም ብለው ነበር። እስራኤልም ይህንን የዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ በደስታ ነበር የተቀበለችው።

አሜሪካ የዚህ ካውንስል አባል የሆነችው በፕሬዝዳንት ኦባማ ጊዜ ነበር።

2ኛ. የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት

አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት የወጣቸው ባለፈው ዓመት ቢሆንም ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ነው።

የፓሪሱ ስምምነት አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የፈረሙት እጅግ ወሳኝ የሚባል ስምምነት ነው። ስምምነቱ ላይ 195 አገራት ፊርማቸውን አኑረዋል። ስምምነቱ አሜሪካ በ2025 የበካይ ጋዝ ልቀቷን በ28 በመቶ እንድትቀንስ የሚያግባባ ነበር።

3ኛ. የኢራን የኑክሌር ስምምነት

ዶናልድ ትራምፕ ይህ በብዙ ጥረት የተገኘን ስምምነት "የላሸቀ ስምምነት" ሲሉ ያጣጥሉታል። "ኦባማ በሰራው ሥራ ሊያፍር ይገባል" ሲሉም ቀዳሚውን ፕሬዝዳንት በነገር ይሸነቁጣሉ።

4ኛ. ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት

አሜሪካ የዚህ ፍርድ ቤት አባል ሆና አታውቅም። ነገር ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለፍርድ ቤቱ ትብብር አትነፍግም ነበር። በ2018 የዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆን ቦልተን እንዲያው ምንም አይነት ትብብር አናደርግም ብለው ያልገቡበትን ማኅበር ተችተው ከትብብሩ ወጥተዋል።

5ኛ. ትራንስ ፓስፊክ የትብብር ማዕቀፍ

ገና ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው ትራምፕ ፍጹማዊ ፊርማቸውን ተጠቅመው ከዚህ ማዕቀፍ ወዲያውኑ ነው አገራቸውን ያስወጡት። ይህ ከ12 አገራት ጋር የተደረገው የንግድ ስምምነት በባራክ ኦባማ ዘመን ነበረ የተፈረመው።

የንግድ ማዕቀፉ 40 ከመቶ የሚሆነውን ዓለም አቀፍ ንግድ የሚሸፍን የነበረ ሲሆን ጃፓን፣ ማሌዢያ፣ አውስትራሊያ፣ ኒው ዚላንድ ካናዳና ሜክሲኮን ያካተተ ነበር። በዚህም በአገራቱ መካከል ታሪፍ በመቀነስ ንግድን ለማጧጧፍ ያለመ ነበር።

6ኛ. የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)

አሜሪካ ወደ ዩኔስኮ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ገብታ ወጥታለች። መጀመሪያ በፈረንጆች 1984 ድርጅቱ ነጻ ድርጅቶችን ይጨፈልቃል በሚል ለቀቀች።

ከዚህ በኋላ በጆርጅ ቡሽ ዘመን ወደ ድርጅቱ ተመለሰች። በ2011 የአባልነት መዋጮ አቆመች፤ ምክንያቱ ደግሞ ፍልስጤም አባል ሆናለች በሚል ነበር።

በ2013 አሜሪካ በዩኒስኮ ድምጽ የመስጠት ስልጣኗን ተነፍጋ ቆየች። በመጨረሻም በ2017 አሜሪካ ዩኒስኮን ጸረ እስራኤል ድርጅት ነው በሚል እስካሁን እንደወጣች ቀርታለች።

አሁን ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ከኮሮናቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከአገራቸው ሕዝብ እየቀረበባቸው ባለው ጠንካራ ትችትና ተቃውሞ ምክንያት በተራቸው የዓለም ጤና ድርጅትና ዋና ዳይሬክተሩን ሲወቅሱ ቆይተው ለድርጅቱ የሚሰጡትን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ገልጸዋል።

ይህ ውሳኔያቸው በዚህ ወሳኝ ወቅት ድርጅቱ ወረርሽኙን ለመቆጠጠር በሚያደርገው ጥረት ላይ ከባድ ጫናን የሚፈጥር ሲሆን፤አሜሪካ በተቋሙ ውስጥ በሚኖራት ሚና ላይ የእራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው። ይህም ምናልባት በሌሎች ተቋማት ላይ እንዳደረገችው ድርጅቱን ለቃ ለመውጣት የሚያበቃት ሊሆን ይችላል።

ኮሮና
Banner