ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19ን በመቆጣጠር በኩል እየተሳካላት ያለችው አገር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በምድራችን የሰሜን ዋልታ ጫፍ ላይ የምትገኘው አይስላንድ ደሴት የኮሮናቫይረስን መስፋፋት ለመከላከል ከዓለማችን አገራት የተለየ እርምጃን እየወሰደች ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከአገር አገር እየተዛመተ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በመያዝ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በየዕለቱ ሕይወታቸውን እያጡ ባለበት በዚህ ወቅት አይስላንድ የተለየች ሆናለች።
ኖርዲክ በሚባለው አካባቢ የምትገኘው አይስላንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በግዛቷ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ለመቆጣጣር እንደቻለች ተመስክሮላታል።
ባለፉት ሁለት ወራት በሚሆን ጊዜ ውስጥ 1500 በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያገኘች ሲሆን አራት ሰዎች ብቻ በበሽታው ለሞት ተዳርገዋል።
አይስላንድ በሽታውን ለመቆጣጠር የቻለችው በርካታ አገራት እያደረጉት እንዳለው ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ በማድረግ ወይም እራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ በማድረግ አይደለም።
እንዲያውም ተቋማትና መደብሮች ክፍት ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ ሲሆን በተወሰነ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ነገር ግን ከ20 ሰዎች በላይ የሚገኙባቸው ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ታግደዋል።
አይስላንድ በሽታውን ለመቆጣጠር ያስቻላት እርምጃ የዓለም ጤና ድርጅት የሚያዘውን መርምራ በስፋት ማድረጓ እንደሆነ ይነገራል።
በአይስላንድ ከሌሎች አገራት በተለየ ምርመራ የሚደርገው በበሽታው የተያዙትን፣ የተጠረጠሩትን ወይም ተጋላጭ የሆኑትን ብቻ ሳይሆን፤ ማንም የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ የሚፈልግ ሰው በነጻ ምርመራውን ማድረግ ይችላል።
አገሪቱ በሽታውን ለመዋጋት በዋናነት የምትከተለው ስትራተጂ አጠቃላይ ሕዝቡ የቫይረሱን ምርመራ በነጻ እንዲያገኝ ማድረጓ በሽታውን ለመለየትና ለመቆጣጠር አስችሏታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኮሮናቫይረስ ምርመራን ለሁሉም ክፍት ከማድረግ በተጨማሪ በበሽታው የተያዙ አዳዲስ ሰዎችን በመለየት የሚያስፈልጋቸውን ህክምና በማድረግ በኩልም አይስላንድ የተከተለችው መንገድ ለስኬቷ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ባለፈው የካቲት ወር ላይ አይስላንድ የመጀመሪያዋን በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ከማግኘቷ ቀደም ብላ ነበር ምርመራ ማድረግ የጀመረችው። በዚህም ለሳምንታት ወደ አገሯ የሚገቡ ቱሪስቶችንና ከተለያዩ ቦታዎች የሚመለሱ ዜጎቿ ላይ ምርመራ ስታደርግ ቆይታለች።
ባለሙያዎች እንደመሰከሩትም ቫይረሱ በሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ከመስፋፋቱ በፊት አይስላንድ የወሰደችው ይህ ወረርሽኙን ቀድሞ የመለየት ሥራ ወሳኝ እርምጃ ሆኖ ነው በሽታውን ለመቆጣጠር ያስቻላት።
የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባለስልጣናት እንዳሉት በበሽታው የተያዘ ሰው ከማግኘቷ በፊት ምርመራ በመጀመር አይስላንድ ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር ሳትሆን አትቀርም።
ሰዎች ከታመሙ በኋላ ወደ ሐኪም ቤት ከሚሄዱባቸው ሌሎች የዓለማችን አገራት በተለየ አይስላንድ፤ ወደ ግዛቷ የሚገቡ ሰዎች ምንም ምልክት ባይታይባቸው እንኳን ወደ ጤና ማዕከላት በመቅረብ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ በባለስልጣናት ይጠየቃሉ።
ምርመራው በስፋት መደረጉ በሽታውን ለመከላከል መንግሥት ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ወሳኝ ግብአት ነው። በዚህም አንድ ሰው በሽታው ከተገኘበት፤ የጤንነታቸው ሁኔታ ምንም ሆነ ምን ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ተለይተው አስፈላጊው ክትትል ይደረግባቸዋል።
አዳዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለመለየት የአይስላንድ ባለስልጣናት ፖሊስ ወንጀለኞችን ለማደን የሚጠቀመበትን ዘዴ ጥቅም ላይ አውለዋል።
ይህ ዘዴ ሴንጋፖርን የመሳሰሉ የእስያ አገራት በወንጀል ምርመራ ላይ የተሰማሩ የፖሊስ አባላትን በመጠቀም በበሽታው ተይዘው ሊሆን ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን በመከታተል ያሉበትን ቦታ ለመለየት ተጠቅመውበታል።
ይህ ዘዴም ውጤታማ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ የበሽታውን ምልክት ሳያሳዩ ምርመራ ከተደረገላቸውና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግማሽ ያህሉ በዚህ መንገድ ነው ሊለዩ የቻሉት።

የፎቶው ባለመብት, EPA
አስካለፈው ሰኞ ድረስ አይስላንድ ካለት ሕዝብ ለስድስት በመቶው ምርመራ አድርጋለች። የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ይህ አሃዝ በዓለም ከሕዝብ ብዛት አንጻር ምርመራው ከተደረገላቸው ሰዎች ከፍተኛው ሆኗል።
በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እየተዛመተባት የምትገኘው አሜሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ቢኖራትም እስካለፈው አርብ ድረስ መመርመር የቻለችው ከሕዝቧ 0.4 በመቶውን ብቻ ነው። ለዚያውም አብዛኞቹ የበሽታው ምልክቶች የታዩባቸው እንደሆኑ ተነግሯል።
ብዙ ምርመራ አድርጋለች የምትባለው ደቡብ ኮሪያ አምስት መቶ ሺህ ሰዎችን ብተመረምርም ከአጠቃላይ ሕዝቧ 0.7 በመቶውን ብቻ ነው መድረስ የቻለችው። አሁንመ ምርመራዋን ብትቀጥልም ትኩረት የሰጠችው ምልክቶችን ላሳዩና ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ብቻ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም አገራት ምርመራውን በስፋት መስጠት ስላልቻሉ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚያጋጥመውን ህመምና ሞት የሚመለከት አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት እንደሚቸግር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚህ አንጻር እስካሁን ባለው ሂደት ከዓለም አገራት ሁሉ አስፈላጊው መረጃ ያላት አይስላንድ ብቻ እንደሆነች ይታመናል።
በአይስላንድ ላለፉት ሦስት ሳምንታት ለሁሉም ዜጎች በነጻ የቀረበው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በበሽታው የመስፋፋት ሂደት ላይ ውጤት እንዳስገኘ የአገሪቱ የሳይንስ ማኅበረሰብ አባላት ገልጸዋል።
በቀጣይም አይስላንድ የሕዝቧን ኑሮና እንቅስቃሴ የሚገድቡ እርምጃዎችን መውሰድ ሳያስፈልጋት በሽታውን ለመቆጣጠር በሚያስችላት አቅጣጫ ላይ እንደሆነች ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም አይስላንድ የተገበረችው ዘዴ ከፖለቲከኞች ተጽዕኖ ነጻና በሳይንሳዊ መንገድ የተመራ እንደሆነ በማመልከት፤ ፖለቲከኞች ወረርሽኙ ማስከተሉ የማይቀረውን ምጣኔ ሐብታዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖዎችን ለመቆጣጠር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እየጣሩ ነው።
"ዓለም አይስላንድ ከተከለተለችው ዘዴ መውሰድ ያለበት በጣም ጠቃሚው ነገር፤ ውሳኔዎች ሁሉ ሳይንስን መሰርት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ነው" ብለዋል ባለሙያዎች።














