ኮሮናቫይረስ፡ ትራምፕ የእንቅስቃሴ ገደቡን የማስነሳት ሙሉ ስልጣን አለኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ትራምፕ ከአሜሪካ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች እና የሕግ ባለሙያዎች አረዳድ በተጻረረ መልኩ በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ተጥሎ የሚገኘው የእንቅስቃሴ ገደብ የማንሳት ሙሉ ስልጣን አለኝ አሉ።
"ውሳኔውን የሚሰጠው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ነው" ሲሉ ተናግረዋል፤ ፕሬዝደንት ትራምፕ ትናንት በሰጡት ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ።
የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ግን በግዛቶች ውስጥ ሕግ እና ሥርዓት መከበሩን የሚያረጋግጡት ግዛቶቹ እራሳቸው ናቸው ይላል።
በምሥራቅ እና በምዕራብ አሜሪካ የሚገኙ 10 ግዛቶች ጥብቅ የሆነውን ከቤት ያለመውጣት ትዕዛዝን ለማንሳት እያሰቡ ይገኛሉ።
በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2 ሚሊዮን ለመድፈን ተቃርቧል። ከእነዚህም መካከል 1/3ኛው የሚገኙት በአሜሪካ ነው።
ትራምፕ ያሉት ምንድነው?
ሪፐብሊካኑ ፕሬዝደንት ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ላይ ትናንት በተሰጠው ዕለታዊ መግለጫ ላይ፤ አስተዳደራቸው የአሜሪካንን ምጣኔ ሃብት መልሶ ለመክፈት የሚያስችል ዕቅድ እያጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ትራምፕ ጨምረውም የፈረንጆቹ ሜይ 1 (ሚያዚያ 23) የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ታልመው ተፈጻሚ ሲደረጉ የነበሩት ጥብቅ መመሪያዎችን ማላላት የሚጀምሩበት ዕለት እንደሚሆን ተናግረዋል።
አሜሪካውያን ወደ ምግብ ቤቶች አትሂዱ፣ እጅግ አስፈላጊ ካልሆኑ በስተቀር ከጉዞዎች እራሳችሁን ቆጥቡ እንዲሁም ከ10 ሰዎች በላይ በአንድ ቦታ አትሰባሰቡ የሚሉት ጥብቅ መመሪያዎች የሚያበቁት ሚያዚያ 22 ነው።
ግዛቶች ያስተላለፏቸው መመሪያዎችን ትራምፕ ማንሳት ስለመቻላቸው ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፤ "አንድ ሰው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሲሆን' ስልጣኑ የተሟላ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ጨምረውም "ሙሉ ነው [ስልጣናቸው]። ገዢዎቹም ያውቁታል" ብለዋል።
ይሁን አንጂ የሕግ ባለሙያዎች ፕሬዝደንቱ የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ ሲባል በግዛቶች እና በታችኛው የአስተዳደር ክፍል የተላለፉ መመሪያዎችን ማንሳት አይችሉም ይላሉ።
ትራምፕ አሜሪካውያን ማኅበራዊ ርቀታቸውን መጠበቃቸው የቫይረሱን ስርጭት እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።
በዕለታዊ መግለጫው ላይ ዋይት ሐውስ ፕሬዝደንት ትራምፕ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታት እየወሰዱት ስላለው አመርቂ እርምጃዎች እና የግዛቶች አስተዳዳሪዎች ለፕሬዝደንቱ ያላቸው አድናቆት የሚያሳይ ቪዲዮ አጫውቷል።
ይሁን እንጂ ዕለታዊ መግለጫውን በቀጥታ ሲያስተላልፉ የነበሩ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዋይት ሐውስ ቪዲዮን ማሳየት ሲጀምር የቀጥታ ስርጭታቸውን አቋርጠዋል።














