ኮሮናቫይረስ፦ በሴቶች የሚመሩ አገራት ወረርሽኙን በተሻለ ሁኔታ እንዴት ተቆጣጠሩት?

ሶስት ሴት መሪዎች ቫይረሱን ለመቆጣጠር ሳይንሳዊ መንገድ ከመጠቀም ባሻገር፤ በፍጥነት ምላሽ ሰጥተዋል።

በኒውዚላንድ፣ ጀርመን፣ ታይዋንና ኖርዌይ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው የተነጠቁ ሰዎች ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ነው።

እነዚህን አገራት የሚያመሳስላቸው ይህ ብቻ ሳይሆን መሪዎቻቸም ሴቶች መሆናቸው ነው።

እኚሁ ሴት መሪዎች በዚህ ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ወቅት የቫይረሱን መዛመት እንዲሁም የሟቾችን ቁጥር መቆጣጠር በመቻላቸው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሙገሳን እያገኙ ይገኛሉ።

በመገናኛ ብዙሀን ዘንድም 'ምሳሌ መሆን የሚገባቸውም' በሚል እየተሞካሹ ነው። በቅርቡ ፎርብስ ባወጣው አንድ ፅሁፍ "የእውነተኛ መሪነት ተምሳሌት" ብሏቸዋል።

"ሴት መሪዎች በዚህ ቀውስ ወቅት እንዴት አድርገን የሰውን ልጅ ህይወት መታደግ እንደሚቻል ለዓለም እያስተማሩ ነው" በማለት የፎርብስ ጽሁፍ አትቷል።

አገራት እየወሰዷቸው ባሉ እርምጃዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠትና፣ የሰውን ልጅ ህይወት እየታደጉ ያሉ መሪዎች በሴት የሚመሩ አገራት ቢሆኑም፤ በዓለማችን ያሉ ሴት መሪዎች ሰባት በመቶ ብቻ ናቸው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመታገል ሴት መሪዎች እንዴት ሊሳካላቸው ቻለ?

የቀደመ ምላሽ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሆኑን ተከትሎ የአይስላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ካትሪን ጃኮብስዶቲር በፍጥነት ተግባራዊ ያደረጉት እርምጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝባቸውን መመርመር ነው።

ሦስት መቶ ስድሳ ሺህ ብቻ የሕዝብ ቁጥር ባላት አገራቸው ውስጥ በሽታውን ችላ ያሉት ጉዳይ አልነበረም። እርምጃ መውሰድ የጀመሩት ጥር ወር መጨረሻ አካባቢ ነው። በአገሪቷ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መኖሩ ከመረጋገጡ በፊት ሃያና ከዚያ በላይ ሰዎች ሆኖ መሰብሰብ ተከለከለ።

በአይስላንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መኖሩ ከመረጋገጡ በፊት ሃያና ከዚያ በላይ ሰዎች ስብሰባ ተከለከለ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአይስላንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መኖሩ ከመረጋገጡ በፊት ሃያና ከዚያ በላይ ሰዎች ስብሰባ ተከለከለ።

እነዚህንም እርምጃዎች ተከትሎ አስከ ትናንትና ሚያዝያ 13፣ 2012 ዓ.ም በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ዘጠኝ ብቻ ነው።

በታይዋንም ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ ዌን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ማዕከል ያቋቋሙት ቀድመው ነው። በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ወይም ግንኙነት አለባቸው የተባሉ ሰዎችንም ክትትል ማጠናከርም በከፍተኛ ሁኔታ ሰርተውበታል።

በሽታውም ከሰው ወደ ሰው እንዳይዛመት የሚያገለግሉ ፊት ጭምብልን የመሳሰሉ የመከላከያ ቁሳቁሶችንም ማምረቱንና ማሰራጨቱን በእሳቸው መሪነት የተከናወነ ነው። ሃያ አራት ሚሊዮን የሕዝብ ቁጥር ባላትና የቻይና አካል በሆነችው ታይዋን የሞተው ሰው ቁጥር ስድስት ብቻ ሆኖ ዓለምን አስደምሟል።

የታይዋን መሪ ብቻ አይደሉም የኒውዚላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደንም ኮሮናቫይረስን ለመግታት ፈታኝ የሚባለውን ውሳኔ በማስተላለፍ አገራቸውን ከወረርሽኙ ታድገዋታል።

የተለያዩ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየወሰዱት ባለው እርምጃ፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ደረጃ ላይ ደርሶ እንዲመለስ የሚያደርግ ውሳኔ ላይ ቢደርሱም ጠቅላይ ሚኒስትሯ ግን ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ የማስቆም ሥራ ላይ ነበር ያተኮሩት።

አገራት ሙሉ በሙሉ የመዝጋትም ሆነ አስገዳጅ የቤት መቀመጥ ውሳኔ የሚወስኑት በኮሮናቫይረስ የተያዘው ሰው ቁጥር ከፍ ሲል ነው።

እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ከሌሎች አገራት በተለየ ሁኔታ የሟቾች ቁጥር ስድስት ሲደርስ ሙሉ በሙሉ አገሪቷን ዘጉ፤ ዜጎች ቤታቸው እንዲቀመጡ ተወሰነ። እስከ ትናንትና ሚያዝያ 13፣ 2012 ዓ.ም ድረስ የተመዘገበው የሟች ቁጥርም 12 ነው።

የታይዋኗ ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ ዌን ከባለስልጣኖቻቸውና ከወታደሮቻቸው ጋር የፊት ጭምብል አጥልቀው

የፎቶው ባለመብት, SAM YEH/AFP

የምስሉ መግለጫ, የታይዋኗ ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ ዌን ከባለስልጣኖቻቸውና ከወታደሮቻቸው ጋር የፊት ጭምብል አጥልቀው

ከኮሮና ቀውስ ጋር ተያይዞ በፍጥነትና፣ በተሳካ ሁኔታ ምላሽ የሰጡ አገራት በሴቶች ከመመራታቸው በተጨማሪ ሌላም ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ይጋራሉ።

አገራቱ ያደገ የምጣኔ ሃብት ባለቤት ሲሆኑ ለዜጎቻቸውም የደኅንነትና ማኅበራዊ ድጋፍ ሥርዓት ዘርግተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

በዓለም ላይ ባሉ አገራትም ዘንድ ማኅራዊ ልማት ተብሎ በሚጠራው ዘርፍ ከፍተኛ ነጥብን ማስመዝገብ ችለዋል።

ለኮሮናቫይረስ ቀውስ የይድረስ ይድረስ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ጠንካራ የጤና ሥርዓት ዘርግተው ድንገተኛ ሁኔታዎችንም የማከም ብቃት ያላቸው ከመሆናቸው አንፃር የኮሮናቫይረስ ትግል አልከበዳቸውም።

እናም ነገሩ ከመሪዎቹ ነው፤ ሴት መሪዎች መሆናቸው ነው ቁም ነገሩ። ስለዚህም አንዲት አገር ሴት መሪ ሲኖራት ስለአገሪቱ ሁኔታ የሚጠቁመው ነገር ይኖር ይሆን?

ሴቶች ተመርጠው በፖለቲካው ውስጥ የሚሳተፉበት መንገድ የራሱን ሚና እንደሚጫወት ተንታኞች ይናገራሉ።

"ሴቶች ከወንዶች የተለየ አይነት አመራር አላቸው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ሴቶች በመሪነት ቦታ ሲቀመጡ ውሳኔ ላይ ለየት ያለ ሁኔታ ሊያመጡ ይችላሉ" የሚሉት በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በታዳጊና በሴቶች ላይ የሚያጠነጥነው 3ዲ ተብሎ የሚጠራው ፕሮጀክት ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።

"ሴቶችን እንዲሁም ወንዶችንም ማሳተፍ ስለሚችል ጥሩ ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻላል" በማለት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በተቃራኒው ደግሞ ዓለማችን የሳይንስን እውነታ የካዱ፣ እንዲሁም በማን አለብኝነት በተወጠሩ እንደ አሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የብራዚሉ ጄይር ቦልሶናሮ አይነት መሪዎችንም አይታለች። የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ኮሮናቫይረስ ጉንፋን ነው በማለት አጣጥለው አካላዊ ርቀት አያስፈልግም እስከ ማለት ደርሰዋል።

የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ጀይር ቦልሶናሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእነዚህ መሪዎች ሁኔታ ከወንድነታቸው ጋር የተያያዘ ጉዳይ ይኖረው ይሆን?

በለንደን ኮሌጅ የሴቶች አመራር ተቋም ዳይሬክተር ሮዚ ካምቤል፤ አመራር ከሴትነት እንዲሁም ከወንድነት ጋር የሚያይዘው ጉዳይ የለም ይላሉ "የአመራር ብቃት አብሮ የሚወለድ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን ማኅበራዊ አኗኗራችን የሚፈጥረው የራሱ ተፅእኖ አለው። ሴቶች ሃዘኔታ ሲኖራቸው እንዲሁም በመተባበር መመራት ተቀባይነት አለው። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አብዛኞቹ ወንድ መሪዎች ብልጣብልጥ፣ ራስ ወዳድ፣ ማን አለብኝ ባይ ናቸው።"

ይህም እንዴት ሆነ ለሚለውም ምሁሯ ምላሽ አላቸው "በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ባለው የወንዶች አመራር እነዚህ ባህርያት ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘታቸው እወደድ ባይ መሪዎች በዝተዋል።"

እወደድ ባይ መሪዎች ያንን ሕዝብ ለማስደሰት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፤ የሚሉት ፕሮፌሰር ሮዚ ወረርሽኙንም የመቆጣጠሩንም ሂደት ዋጋ አስከፍሏቸዋል ይላሉ።

ለመጥቀስም ያህል የአሜሪካ፣ የብራዚል፣ የእስራኤልና የሃንጋሪ መሪዎች ችግሮቻቸውን ከመቅረፍ ይልቅ ጥፋታቸውን በሌሎች ላይ ለማላከክ ሲሯሯጡ ተሰምተዋል። በተደጋጋሚም የውጭ አገራት ዜጎች ቫይረሱን እንዳስገቡት እንዲሁም አገራትን ጥፋተኛ አድርገዋል።

"ለምሳሌ ያህል ትራምፕና ቦልሶናሮን እንውሰድ የማን አለብኝነት ባህርይ ያሳያሉ። ምንም ከአፈጣጠራቸው ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ የለም። እንዲህ ለመታበይ መርጠው ነው" ይላሉ።

"አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች በሕዝብ እወደድ ባይ የመሆን እንዲሁም ፅንፈኛና ወግ አጥባቂ አክራሪ መሪዎች አይሆኑም። ግን ሆኖም አንዳንድ አይታጡም ለምሳሌ የፈረንሳይዋ መሪ ማሪን ለ ፔን" በማለት ያስረዳሉ።

አንጌላ መርኬል

የፎቶው ባለመብት, Clemens Bilan - Pool/Getty Images

ኮሮናቫይረስን ለመግታት አገራት እየወሰዱት ያለው እርምጃ የተለያየ ነው፤ ምክንያቱም የየአገራቱ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እውነታ መለያየቱ ለወረርሽኙ የሚሰጡትም ምላሽም ተመሳሳይ እንዳይሆን አድርጎታል። እዚህ ላይ ፆታ ብቻውን የሚጫወተው ሚና ላይኖር ይችላል።

ምንም እንኳን ትራምፕና ቦልሶናሮ ከእወደድ ባይነታቸው አንፃር የማን አለብኝነትና ራስ ወዳድ ቢሆኑም እንዲህ አይነት ባህርይ ያልተላበሱ ወንዶች ፕሬዚዳንቶችም በአገሮቻቸው ከፍተኛ እመርታን ማሳየታቸውን ፕሮፌሰር ሮዚ ይናገራሉ።

ለምሳሌነት ከሚጠቅሷቸው መካከል ጥቂት ሞት የተመዘገበባትን የደቡብ ኮሪያ መሪ ሙን ጄን ነው።

ፕሬዚዳንቱ በአገራቸው ላሳዩትም የአመራር ብቃት በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ተቀናቃኞቻቸውን በከፍተኛ ድምፅ ልዩነት ማሸነፍ ችለዋል።

የግሪኩም ጠቅላይ ሚኒስትር ክይሪያኖስ ሚትሶታኪስ ሌላኛው ፕሮፌሰሯ በምሳሌነት የሚጠቅሷቸው መሪ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወረርሽኙ እንዳይዛመት ከፍተኛ ሚናን በመጫወት እንዲሁም የሟቾች ቁጥርም እስከ ሚያዝያ 13/2012 ዓ.ም ድረስ በ114 እንዲገታ የላቀ ጥረት አድርገዋል ተብሏል።

አገሪቷ 11 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሲሆን በተቃራኒው 60 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ጣልያን 22 ሺ ሞት ተመዝግቧል።

ግሪክ በወረርሽኙ መነሻ ወቅት የታወቁ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አካላዊ ርቀትን አስገዳጅ እንዲሆን ውሳኔ ያሳለፈችው የመጀመሪያው ሞት ከመመዝገቡ በፊት ነበር።

አንዲት ሴት አበባ ስትሸጥ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በኮሮና ቫይረስ በማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያርፍባቸዋል።

ሁሉም በሴቶች የሚመሩ አገራት አይደሉም ወረርሽኙን መግታት የቻሉት አንዳንድ ሴት መሪዎች አሁንም ያላሰለሰ ትግል ላይ ናቸው።

ለምሳሌም ያክል የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለባት አገራቸው የቫይረሱን መዛመት መግታት ችለዋል። ሆኖም አገሪቷ ባላት የመመርመር ብቃት ማነስ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ባለባቸው የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት የተነሳ ስጋቶች አልተቀረፉም።

አስቸጋሪ ውሳኔዎች

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት አገራት ፈታኝ የሚባሉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ አለባቸው። ወረርሽኙ ገና ከመዛመቱ በፊት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ማገድ ወይም መዝጋትን አስገዳጅ ሊያደርጉ ይገባል።

እነዚህ ውሳኔዎች አጠር ላለ ጊዜ ምናልባት ፖለቲካዊ ዋጋ ሊያስከፍሏቸው እንደሚችሉ ፕሮፌሰሯ ይናገራሉ "የእወደድ ባይ መሪ ተቃራኒ ይህ ነው። መሪዎችም ተግባራዊ ሊያደርጉት የሚገባ ነው።"

በተቃራኒው ሴቶች መሪዎች ግልፅነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ ለዜጎቻቸው የወረርሽኙን ስጋት በማሳወቅና አገሮቻቸው የገጠሟቸውን ፈተናዎችንም በመወያየት በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፍ ችለዋል።

የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኮቪድ-19 "ከባድ ስጋት" መሆኑን ያሳወቁት በፍጥነት ነው።

ይህንንም ተከትሎ አገራቸው በከፍተኛ ሁኔታ የምርመራ ጣቢያዎችን አቋቋመች፣ ከአውሮፓ የሚመጡም ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደረጉ። በሌሎች አውሮፓ አገራት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሲያልቁ 83 ሚሊዮን ባላት ጀርመን የሟቾች ቁጥር 4600 ሆኗል።

የስካንድኔቪያኖቹ ኖርዌይና ዴንማርክ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸውም በማን አለብኝነት ሲንጠራሩ ከነበሩ አቻ ወንድ መሪዎቻቸው በበለጠ ቫይረሱን መቆጣጠር ችለዋል።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልድበርግና የዴንማርኳ ሜት ፍሬዴሪክሰን
የምስሉ መግለጫ, የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልድበርግና የዴንማርኳ ሜት ፍሬዴሪክሰን

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልድበርግና አቻቸው የዴንማርኳ ሜት ፍሬዴሪክሰን ትልልቅ ሰዎች እንዳይገቡ በማድረግ ለህፃናት ብቻ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር።

የኒውዚላንድ መሪ ጃሰንዳ አርደንም እንዳቻዎቻቸው ሁሉ ህፃናትን ችላ አላሉም፤ በአገራቸው እንደተለመደው የትንሳኤ በዓል ላይ በሚደረገው ባህል መሰረት ኮሮናቫይረስ እንደማያቋርጠው አሳውቀው በየቤታቸውም የቸኮሌት እንቁላል እንዲደርሳቸው አድርገዋል።

ሴት መሪዎች የሚያደርጉትንም በማስተዋል ከዚህ ቀደም እንደ ቀልድ ወይም ችላ ተብለው የነበሩ ጉዳዮችን በማንሳት ፖለቲካ በህፃናት ላይ የሚያደርገውን ጫና ቦታ መስጠት እንደቻሉ ፕሮፌሰሯ ያስረዳሉ። በተለይም የግል ጉዳይ ተብለው ወደ ጎን የተተዉ እንደ የቤት ውስጥ ጥቃቶችንና የህፃናት እንክብካቤ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን እንዳሳዩ ፕሮፌሰሯ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

የተሻሉ ውሳኔዎች

በዓለም ላይ 70 በመቶ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ሴቶች ቢሆኑም፤ በመሪነት ቦታ ላይ ከሚገኙት 153ቱ መካከል ግን አስሩ ብቻ ሴቶች መሆናቸውን ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ መረጃ ጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ የፓርላማ አባላትን በምናይበት ወቅት ሴቶች ሩብ ብቻ ናቸው።

የፊት ጭምብል ያጠለቁ ሴት መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአለም ላይ 70 በመቶ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ሴቶች ቢሆኑም፤ በአለማችን ካሉ 153 መሪዎች መካከል አስሩ ብቻ ሴቶች መሆናቸውን ከሁለት አመት በፊት የወጣ መረጃ ጠቁሟል።

በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በጤናው ዘርፍ የሴቶች አመራር ሚናን ለመጨመር የሚሰራውን ውሜን ሊፍት ሄልዝ ቦርድን የሚመሩት ዶ/ር ጉፕታ በአመራር ላይ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር መጨመር የተሻለ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ መድረስ እንደሚያስችል ይናገራሉ።

"ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችንም ሆነ ውሳኔዎችን መስጠት ይችላሉ" በማለት ያስረዳሉ።

"ምክንያቱም ሴት መሪዎች በተለያየ የሥራ ድርሻ እንዲሁም የመሪነት ቦታ ሆነው ህይወትን ያውቁታል። አብዛኛውንም ጊዜ የሚሰጣቸው የሥራ ድርሻ በማኅበረሰቡ ዘንድ ለሴቶች ተብለው የተተው ናቸው። በመሪነት ቦታም ሲመጡ ያካበቱትን ልምድ፣ ያለውንም ክፍተት ስለሚረዱ የተሻለ ፖሊሲ እንዲሁም ውሳኔ ላይ መድረስ ይችላሉ" ይላሉ።

ዶ/ር ጉፕታ አክለውም ኮቪድ-19 ሊያስከትለው የሚችለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ልብ ሊባል እንደሚገባ አስታውሰው፤ በተለይም የቤት ውስት ጥቃት መጨመር እንዲሁም በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለው ክፍያ ልዩነት እንዳያንሰራራ ባለድርሻ አካላት ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባም መክረዋል።

ኮሮና