"የምናውቀው ሰው እስኪሞት መጠበቅ የለብንም" ዶ/ር ፅዮን ፍሬው

የፎቶው ባለመብት, Twitter
የድንገተኛ ክፍል እና የኅብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስቷ ዶ/ር ፅዮን ፍሬው የጤና ጥበቃ አማካሪ ናቸው። በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በሆነባት የአሜሪካዋ ኒው ዮርክ የሚሠሩት ዶ/ር ፅዮን የኮሮናቫይረስ ይዟቸው እንዳገገሙ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ስለ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል እየወሰደች ስላለችው እርምጃ ዶ/ር ፅዮንን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አነጋግረናቸው ነበር።
የወረሽኙን ስርጭት በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ምን ላይ ትገኛለች?
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሁለት ሚሊዮን አልፏል። ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 85 መድረሳቸውን ጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።
ዶ/ር ፅዮን እንደሚሉት፤ በምጣኔ ሃብት እንዲሁም በጤና ሥርዓትም የተሻሉ አገሮችን እየፈተነ ያለው ቫይረስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለአቅመ ደካማ አገሮች የበለጠ አስጨናቂ መሆኑ አያጠያይቅም።
ነገር ግን ከጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ላይ የቫይረሱ ምርመራ መጀመሩ ጥሩ እርምጃ እንደነበር ያስረዳሉ። በወቅቱ አየር መንገድ ላይ የሰዎች የጉዞ ታሪክ መጠየቁ (ቫይረሱ ወደተሰራጨባቸው አገሮች ሄደው እንደሆነ ለመለየት) የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚደረግው ጥረት እንደ ጥሩ ምሳሌ ይጠቅሱታል።
የፅኑ ህሙማን ማቆያና ሌሎችም የህክምና መሣሪያዎች ኢትዮጵያም ይሁን ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች በበቂ ሁኔታ የላቸውም። “አሜሪካ እና አውሮፓ ውስጥ እየሄደበት ባለው ፍጥነት አፍሪካ ውስጥ ቢሄድ በጣም ያስፈራል፤ ያስጨንቃል” ይላሉ ዶክተሯ።
አህጉሪቱ ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የያዙት ወጣቶች መሆናቸው መጠነኛ ተስፋ እንደሚሰጥ ይናገራሉ። ይህ ማለት ወጣቶች በኮሮናቫይረስ አይያዙም ማለት ሳይሆን፤ ቢያዙም ከአዛውንቶች አንጻር የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ ነው ማለት ነው።
ምርመራን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በዋነኛነት ምርመራ እየተካሄደ ያለው ከተለያየ አገር ወደ አገሪቱ ለመጡና በቫይረሱ ከተያዙ ወይም ተይዘዋል ተብለው ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር ንክኪ ላላቸው ሰዎች ነው።
መመርመሪያው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በሚፈለገው መጠን አለመኖሩ ምርመራውን ከባድ እንደሚያደርገው የሚናገሩት ዶክተሯ፤ “በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ እተሰራጨ ሲመጣ ግን በብዛት መመርመር ይኖርብናል” ይላሉ።
ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ ነው?
በእርግጥ በመላው አገሪቱ በሽታውን ለመከላከል ዜጎች እየወሰዱ ስላሉት እርምጃ አንዳች ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ሰፊ ጥናት ቢያስፈልግም፤ በአደባባይ ከሚታዩ እንቅስቃሴዎች አንጻር፤ ከኮሮናቫይረስ ራስን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ ነው ማለት ይቻላል ወይ? ስንል ዶ/ር ፅዮንን ጠይቀን ነበር።

የፎቶው ባለመብት, @DrTsion/twitter
እሳቸው እንደሚሉት፤ በሽታው ስር ሳይሰድ በፊት መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋሞች (ጤና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት) የሚያወጧቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ዜጎች መከተል አለባቸው።
“ሰው አላግባብ መደንገጥ ሳይሆን የሚነገረውን ማድረግ አለበት፤ በማኅበራዊም ይሁን በማንኛውም ጉዳይ አትሰብሰቡ እየተባለ ሰው መሰብሰብ ካላቆመ በሽታው ይስፋፋል” ይላሉ።
በተለይም በአሁን ወቅት “መዘናጋት ትክክል አይደለም” ሲሉም በአጽንኦት ይናገራሉ። “የምናውቀው ሰው እስኪሞት መጠበቅ የለብንም፤ ቁጥሩ 40 ሺህ ወይም 60 ሺህ እስኪደርስ መጠበቅ የለብንም። በጣም የምወደው ሰው ከዚህ በሽታ ሊሞት ይችላል ብለን ማሰብ አለብን” በማለትም ዶ/ር ፅዩን ያክላሉ።
መዘናጋት በበሽታው የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ከማድረጉም ባሻገር፤ ቫይረሱ ስጋት የሚሆንበትን ጊዜም እንደሚያራዝመው ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ቤት መቀመጥና እጅ መታጠብን የመሰሉ ተግባሮች ቀላል ቢመስሉም የበርካቶችን ሕይወት ይታደጋሉ ይላሉ።
ቤት ውስጥ ስለማገገም
ዶ/ር ፅዮን እንደሚሉት፤ ወደ ህክምና መስጫ ሳይሄዱ ቤታቸው ማገገም የሚችሉ ሰዎች አሉ።
"ሆስፒታል መሄድ የሚያስፈልጋቸው ከ10 በመቶ በታች ናቸው። በእድሜ የገፉ ሰዎችና የተለያየ ህመም ያለባቸው ሰዎች ሆስፒታል መሄድ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ቤት እንዲሆኑ ይመከራል" ይላሉ።
በተለይም የህክምና መስጫ ተቋሞች ሁሉንም ሰው ማስተናገድ በማይችሉበት ወቅት ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ እንደሚደረግ ያስረዳሉ።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በአጠቃላይ ሆስፒታል እየገቡ መሆኑን የሚያጣቅሱት ዶ/ር ፅዩን፤ ቁጥሩ እየበዛ ከሄደ ግን ሆስፒታሎች መቋቋም እንደማይችሉ ይናገራሉ።
በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአውሮፓ አገራትም አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ የተደረገውም ቁጥሩ በመጨመሩ መሆኑንም ያስረዳሉ። ሆኖም ግን መተንፈስ የሚቸገሩ ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እንዲከታተሉ እንደሚደረግም አያይዘው ያነሳሉ።
"ቤታቸው ሆነው እንዲያገግሙ የሚጠበቁ ሰዎች ሌላ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸው ለራሳቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንዲያደርጉም ይመከራል። ትኩሳት እና ሳል የሚያስታግስ ነገር በቤታችን ማድረግ እንችላለን" ይላሉ።














