በኮቪድ - 19 የሞተ ሰው የቀብር ሥነ- ሥርዓት እንዴት መፈጸም አለበት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሦስት ወራት በፊት ተቀስቅሶ መላውን ዓለም ባዳረሰው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ የተጠጋ ሲሆን፤ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ ደርሷል፡፡ አሃዙም በፍጥነት እየጨረ ነው።
ለመሆኑ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች መቀበር ያለባቸው እንዴት ነው? ምን አይነት ጥንቃቄዎችስ መደረግ አለበት? በኮሮናቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬንስ ቫይረሱን ያስተላልፋል?
እነዚህን ጥያቄዎች በስዊድን አገር በሚገኘው ማላርዳሌንስ ዩኒቨርሲቲ ‘የግሎባል ኸልዝ’ መምህር እና የማሕበረሰብ ጤና ባለሙያ ለሆኑት አቶ በንቲ ገለታ አንስተንላቸው ነበር፡፡
አቶ በንቲ ጥናቶችን ጠቅሰው እንደሚሉት፤ አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከሞተ/ች በኋላ በሽታውን አያስተላልፍም/አታስተላልፍም፤ ነገር ግን ግለሰቡ/ቧ ከሞተ/ች በኋላ የሞቱበት አካባቢ እንዲሁም የተጠቀሙባቸውና የነካኳቸው ዕቃዎች በቫይረሱ ሊበከሉ ይችላሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ከተለያዩ የሰውነት ቀዳዳዎች ፈሳሾች ሊወጡ ይችላሉ፡፡ በእነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች አማካኝነት ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል፡፡
በመሆኑም አንድ ሰው በኮቪድ-19 ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ግብዓተ መሬቱ በጥንቃቄ ሊፈጸም ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡
ባለሙያው እንደሚሉት አንድ ሰው በኮቪደ-19 ሲሞት አሸኛኘቱ ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡
1. አዘገጃጀት
በአገራችን በሁለት ዓይነት ሁኔታ አስክሬን ሊዘጋጅ እንደሚችል ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ በህክምና ተቋማት እና ከህክምና ተቋም ውጭ የሚከናወን ነው፡፡
“አንድ ሰው በህክምና ተቋማት ሲሞት አስክሬኑ እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት የህክምና ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና ስለሚኖራቸው፤ እዚያ ላይ ትኩረት ማድረግ አልፈልግም” የሚሉት ባለሙያው በቤት አሊያም ከህክምና ተቋም ውጭ የሞተን ሰውን እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡
በቅድሚያ ግለሰቡ ሕይወቱ እንዳለፈ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ደውሎ ማሳወቅና የጤና ተቋሙ በዚህ ያሰለጠናቸውን ሰዎች መላክ ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡
ባለሙያው በዚህ ረገድ የሰለጠኑ ሰዎች በየቀበሌው መኖር አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም በኮቪድ-19 የሞተ ሰው በሌላ በሽታ እንደሞተ ሰው ሳይሆን አስክሬኑ በጥንቃቄ መዘጋጀት አለበት፡፡
በመሆኑም አስክሬኑን የሚያዘጋጀው ሰው የእጅ ጓንቶች፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) እንዲሁም ገዋን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አካባቢውንም በጸረ ተህዋስ ኬሚካል መርጨት ያስፈልጋል፡፡
ግለሰቡ የተጠቀመባቸው ቁሳቁሶች፣ የለበሳቸው አልባሳቶች በበረኪና ወይም ኬሚካል ማጠብና መገልገል ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ዕቃዎቹ ወይም ቁሳቁሶቹ በዚህ መልክ ከጸዱ ማቃጠል ላያስፈልግ ይችላል፡፡
2. አሸኛኘት
በኮቪድ -19 የሞተን ሰው አስክሬን ከማዘጋጀት በተጨማሪ አስክሬን አሸኛኘት ዋናው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡
አቶ በንቲ እንደሚሉት በተለይ በእኛ አገር ባህል መሠረት ሰው በብዛት ወጥቶ አስክሬን መሸኘት የተለመደ ነው፡፡
በዚህም ምክንያት ሳታወቅ የሟች አስክሬን በሰዎች ሊነኩ ይችላሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር ከእርስ በርስ በሽታው ሊተላለፍ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት አስክሬን የሚሸኙ ሰዎች ቁጥር እጅግ ማነስ እንዳለበት ይመክራሉ፡፡
በሽኝቱ ላይም በተቻለ መጠን ቤተሰብና የቅርብ ወዳጆች ብቻ ቢገኙ፤ እነርሱ ቢሆኑ አካላዊ ርቀታቸውን ጠብቀው በርቀት ቢሸኙ ይመረጣል፡፡
3. ግብዓተ መሬት አፈጻጸም
አንድ በኮቪድ -19 የሞተ ሰው አስክሬን ከተዘጋጀና ከተሸኘ በኋላ ግብዓተ መሬት ይፈጸማል፡፡ በዚህ ሂደት ቀብር የሚፈጽሙ ሰዎች ቢያንስ ጓንት ማድረግ አለባቸው፡፡
በሃይማኖትም ሆነ በሌላ ምክንያት አስክሬኑ በሳጥን የማይቀበር ከሆነ በአስክሬን ሻንጣ (በላስቲክ ተጠቅልሎ )መቀበር አለበት፡፡
ከሟቹ የሚረጩ አንዳንድ ፈሳሾች አለ ብለው የሚገምቱ ከሆነም ተደራቢ ጋዎን እና ማስክና ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡














