"ያስጨንቀኝ የነበረው ከእኔ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ጤንነት ነበር" የኮሮናቫይረስ ታማሚዋ ከባህር ዳር

ባህር ዳር ከተማ
የምስሉ መግለጫ, ባህር ዳር ከተማ

በባህር ዳር ከተማ የኮሮናቫይረስ ታማሚ የሆነች ግለሰብ መገኘቷ የተረጋገጠው ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ ሁለት ሳምንት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ነበር። ቫይረሱ የተገኘባት ግለሰብ በወቅቱ ከዱባይ የተመለሰች እንደነበር ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር የለይቶ ህክምና ማዕከል ውስጥ የምትገኘው በክልሉ የመጀመሪያዋ በሽታው እንዳለባት የተረጋገጠው ግለሰብ በቫይረሱ መያዟን ካወቀች ሃያ ቀን ሊሆናት ነው።

አሁን ስላለችበት ሁኔታና ለቫይረሱ የተጋለጠችበትን አጋጣሚ በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራት ሠናይ [ስሟ ለዚህ ታሪክ ሲባል ተቀይሯል] ስለበሽታው ከሰማችበት ጊዜ አንስቶ በቫይረሱ እንዳትያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጓን ታስታውሳለች።

ነገር ግን ወደ አገሯ ከተመለሰች በኋላ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በተለይ ጉምሩክ አካባቢ "ከበርካታ የውጪ አገር ዜጎች ጋር ተቀራርበን እንድንቆም በመደረጋችን ያኔ በተፈጠረው ንክኪ ቫይረሱ እንደያዘኝ እጠረጥራለሁ" ትላለች።

ከዚያ ጊዜ ቀደም ብሎ የፊት መሸፈኛ ጭምብልና ጓንት ታጠልቅ እንደነበር አስታውሳ፤ ከሰዎች ጋርም ሆነ ከሌሎች ነገሮች ጋር የነበረኝን ርቀት በሚገባ ጠብቄያለሁ ትላለች።

ከዱባይ ወደ ኢትዮጵያ የገባችው መጋቢት 10/2012 ዓ.ም መሆኑን የተናገረችው ሠናይ፤ በዚያው ዕለት በግል መኪና ተሳፍራ ባህር ዳር መግባቷን ተናግራለች።

መኪና ስትሳፍርም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ "ከውጪ መምጣቴን ተናግሬ ከመኪናው የኋላ መቀመጫ ከሻንጣ ጋር እንድቀመጥ ተሳፋሪዎቹን ጠይቄ፤ 'አንችን ከተመቸሽ ተቀመጭ' ብለውኝ ባህር ዳር ድረስ በዚህ ሁኔታ መጣሁ" በማለት አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጌያለሁ ትላለች።

ባህር ዳር ከደረሰች በኋላ አብሯት የሚኖረውን ልጇን ሌላ ቦታ እንዲሄድና ለጊዜው ራሷን ማግለል እንዳለባት ብትነግረውም ልጇ ባለመስማማቱ በቤቷ ውስጥ አንድ ክፍል አዘጋጅታ ራሷን ማግለሏንና ከዱባይ መመለሷንም ለማንም አለመናገሯን ታብራራለች።

ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናት ውስጥ ለእራሷም ሆነ ለሌሎች ጥንቃቄ ለማድረግ "የፊት መሸፈኛ ጭምብልና የእጅ ጓንት አድርጌ ስለነበር፤ ሰው በጥርጣሬ ይርቀኝ ነበር" በማለት ከሰዎች ጋር የነበራት ግንኙነት የተገደበ እንደነበር።

ከዱባይ ከተመለሰች በኋላ በስፋት የሚታወቁት እንደ ደረቅ ሳል፣ ትኩሳትና የሰውነት ድካም የመሳሰሉት የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ባይታዩባትም "የምግብ ጣዕም መለየት አለመቻሌና ነገሮችን ማሽተት ሲሳነኝ፤ እራሴን ተጠራጥሬ ወደ ሆስፒታል ሄድሁ።"

በወቅቱ ወረርሸዕኙን በተመለከተ የነበረው ግንዛቤና ዝግጅት ከዚህ ግባ የሚባል ስላልነበረ የምርመራ ናሙና ለመስጠት ከስድስት ሰዓታት በላይ መጉላላቷን ታስታውሳለች።

በመሆኑም አርብ ቀን [መጋቢት 18/2012 ዓ.ም] የተደረገላት ምርመራ ሰኞ [መጋቢት 21/2012ዓ.ም] ውጤቱ ሲመጣ በበሽታው መያዟ አረጋገጠ።

ሠናይ የተደረገላት ምርመራ ይዞት ሊመጠ ስለሚችለው ውጤቱ እራሷን አዘጋጅታ ነበር። "በበሽታው ብያዝም ሆነ ከዚያ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ምን ሊባል እንደሚችል ቀድሜ የሥነ ልቦና ዝግጅት አድርጌ ስለነበር ሳልደናገጥ ወደ ማገገሚያ ማዕከል ሂጃለሁ" ብላለች።

በሽታው እንዳለባት ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በእርሷና በልጇ በኩል ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችን አድራሻ በመስጠት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ አስደርጋለች።

ኮሮና
Banner

"ያንን ሁሉ ጥንቃቄ ያደረግሁት በእኔ ምክንያት አንድም ሰው መጎዳት ስለሌለበትና ከዚያም በተጨማሪ በዙሪያዬ የሚገኙ ቤተሰቦቼም ስኳር፣ የደም ግፊትና ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸው በመሆናቸው በሽታውን እኔ ባስተላልፍባቸው መጀመሪያ የሚያልቀው የእኔ ቤተሰብ መሆኑን በመረዳትና ለከተማዬም እኔ መነሻ መሆን ስለሌለብኝ ነው" ብላለች ሠናይ።

በመሆኑም ከእርሷና ከልጇ ጋር ግንኙነት ነበራቸው የተባሉ ሰዎች ልጇን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ሁለት ጊዜ ምርመራ አድርገው ከቫይረሱ ነጻ ሆነው እንደተገኙ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ መሃሪ ታደሰ (ዶ/ር) ለክልሉ ቴሌቪዥን ገልጸዋል።

ሠናይ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነዋሪነቱ በሌላ ቦታ የሆነና የማታውቀው ሰው ከእርሷ ጋር ንክኪ እንደነበረው ተጠቅሶ ወደቤቱ ከተመለሰ በኋላ በጠና ታሞ ወደ ጎንደር ሆስፒታል መግባቱ ሲነገር ነበር።

ሠናይ ግን ከተባለው ሰው ጋር እንዳልተገናኘች፤ እንደማታውቀውም ገልጻ፤ ከእርሷ ጋር የቀረበ ግንኙነትና ንክኪ የነበራቸው ሰዎችን ለደኅንነታቸው ሲባል ክትትል እንዲደረግላቸው ወደለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማስደረጓን ትናገራለች።

አሁን "በመልካም ጤንነት ላይ ነኝ" የምትለው ሠናይ፤ በቅርቡ አገግማ እንደምትወጣ ተስፋዋን ገልጻለች።

ትኩሳቱና ሳሉ ሙሉ በሙሉ እንደቆመና የጤና ባለሙያዎችም አቅማቸው በፈቀደው መልኩ እየረዷት መሆኑን የምትናገረው ሠናይ፤ በእርግጥም ከቢቢሲ ጋር በነበራት ከ25 ደቂቃ በላይ የቆየ የስልክ ቆይታም ምንም አይነት ሳልም ሆነ ማስለጠስ አልነበረባትም።

ነገር ግን የበሽታው ምልክቶች ቢወገዱላትም ለበሽታው ማስታገሻነት የምትወስደው መድኃኒት ግን ጨጓራ ላይ ጉዳት እያደረሰ በተወሰነ መልኩ በጨጓራ ህመም መሰቃየቷን ትናገራለች ።

"ከእኔ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ውጤት ነጻ መሆኑ ደግሞ ተጨማሪ አቅም ሆኖኝ በሽታውን በፍጥነት ድል እየነሳሁት ነው" ብላለች።

የእነዚህ ሰዎች ውጤት ከመታወቁ በፊት ግን በጭንቀት እንቅልፍ እንደማትተኛና ይህም በሽታውን ያባብስባት እንደነበር ታስታውሳለች። በሽታው በባህሪው እረፍትና መረጋጋትን ስለሚፈልግ የውጤቱ መታወቅ አቅም እንደጨመረላት ታምናለች።

በአማራ ክልል ሁለተኛው የኮሮናቫይረስ ታማሚ የተገኘው በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አዲስ ቅዳም ከተማ ውስጥ ነው።

ግለሰቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ወደ አዲስ ቅዳም ከተማ በገባ በተወሰኑ ቀናት ውስጥ በተደረገለት ምርመራ ቫይረሱ እንዳለበት ተረጋግጧል።

ይህ ታማሚም ወደ ባህርዳር የለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተወስዶ በአሁኑ ወቅት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ጋሻዬ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ ቢያንስ 63 ሰዎች ተለይተው በእንጅባራ ሆስፒታል የለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙና አብዛኞቹ ምርምራ ተደርጎላቸው ነጻ መሆናቸው ቢረጋገጥም ሁለተኛ ምርመራ እሰከሚደረግላቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ናቸው።

ከእነዚህ ሰዎች መካከል የታማሚው ባለቤትና ልጅን ጨምሮ ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸው የ8 ሰዎች የምርመራ ውጤት በቅርቡ የታወቀ ሲሆን አንደኛው ግለሰብ ብቻ ቫይረሱ እንዳለበት መረጋገጡን አቶ አዲሱ አስረድተዋል።

በመሆኑም ከሁለተኛውም ሰው ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል የተባሉ ግለሰቦችን በመለየት እስካሁን 91 ሰዎችን በለይቶ ማቆያ ማስገባታቸውንና በአጠቃላይም 154 ሰዎች በእንጅባራ ሆስፒታል በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገርም ከመጀመሪያው ሰው ጋር ንክኪ የነበራት የቤተሰቡ አባል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አምርታ ስለነበር መረጃ በመለዋወጥ ወደ በለይቶ ማቆያ ገብታ ምርመራ ተደርጎላት ነጻ መሆኗን አቶ አዲሱ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።