ኮሮና ቫይረስ፡ በኒውዮርክ የመድኃኒት መደብሮች የኮሮና ምርመራ ሊጀመር ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኮሮና ክፉኛ እየተጠቃች ባለችው የአሜሪካዋ ግዛት ኒውዮርክ የኮሮናቫይረስ ምርመራ በመድኃኒት መደብሮች (ፋርማሲዎች) ሊጀመር መሆኑን የኒውዮርክ አስተዳዳሪ አሳውቀዋል።
የኒውዮርክ አስተዳዳሪ አንድሪው ኩሞ እንዳሉት አምስት ሺህ ያህል የመድኃኒት መደብሮች ምርመራውን ለማድረግ የተመረጡ ሲሆን፤ በከተማው ያለውን የምርመራ ቁጥርም ወደ 40 ሺህ ያህል ለማድረስም ያለመ ነው።
በከተማዋ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው፤ የቀውሱ ማብቂያ ሊሆን ይችላልም ብለዋል። ሆኖም ሰዎች እንዳይዘናጉና ጥንቃቄያቸውን እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል።
በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 938 ሺ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከ53 ሺህ 751 አንድ ሶስተኛው ሞት የተመዘገበው በኒውዮርክ ነው።
በተያያዘ ዜና በየቀኑ በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች እያወዛገቡ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትናንትናው እለት መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በትናንትናው እለት በትዊተር ገፃቸው ላይ ሚዲያውን የወነጀሉ ሲሆን ጋዜጠኞች የሚጠይቁት ጥያቄ "ግጭት የተሞላባቸው" ናቸው ብለዋል።
ከሰሞኑ ለኮሮናቫይረስ በሽታው ፈውስ የረቂቅ ተህዋስያን ማጥፊያ (ዲስ ኢንፌክታንት) ኬሚካል በመርፌ የሚሰጥበት ምርምር እንዲደረግ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ውግዘትንና ትችትን እያስተናገዱ ነው።
በህክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች የረቂቅ ተህዋስያን ማጥፊያ ለሰውነት መርዛማ የሆነና ህይወትንም በከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ እንዲህ አይነት ሃሳብ እንዴት ይቀርባል ሲል ቁጣቸውን ገልፀዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ሃሳባቸውን መናገራቸውንም ተከትሎ በርካቶች የረቂቅ ተህዋስያን ማጥፊያን መውሰዳቸውን በኒውዮርክ ድንገተኛ ጥሪዎችን የሚያስተናግዱ አሳውቀዋል፤ ሰላሳ ሰዎችንም አስተናግደዋል ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የኮሮና ቫይረስ ግብረ ኃይል በጥምረት የሚያደርጓቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ከሁለት ሰአታት በላይ የሚቆዩ ቢሆኑም በዚህ ሳምንት ሃሙስ ላይ ፕሬዚዳንቱ የሰጡት አስተያያት ተቃዋሚዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቻቸውንን ያሳፈረና ያሸማቀቀ እንደሆነ የቢቢሲ የአሜሪካ ዘጋቢ ፒተር ቦውስ ገልጿል።
በነገታውም የፕሬዚዳንቱ መግለጫ ከተለመደው ውጭ አጭር የነበረ ሲሆን፤ ለሃያ ደቂቃ ብቻ ነበር የቆየው፤ በጋዜጠኞችም ለመጠየቅ ፈቃደኛ አልነበሩም።
ምንም እንኳን የጤና ባለሙያዎችም ቤት መቀመጡ መቀጠል እንዳለበትና፣ ወረርሽኙም እንደሚዛመት ቢያስጠነቅቁም በአሜሪካ የሚገኙት ጆርጂያ፣ ኦክላሆማና አላስካ የተወሰኑ የንግድ ቦታዎች እንዲከፈቱ ተወስኗል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጀምሮ ከሃያ ስድስት ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ስራ ያጡ ሲሆን ይህም የአገሪቷ 15 በመቶ ሰራተኛ ኃይል ነው ተብሏል። የተለያዩ ግዛቶችም ኮሮና ያስከተለውን ጫና መቋቋም አቅቷቸዋል።
ለስራ ብቻ ሳይሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በፍሎሪዳና ካሊፎርንያ ግዛቶች ለመዝናናት ወደ ባህር ዳርቻዎች እንዳቀኑም ሮይተርስ ዘግቧል።













