ኮሮናቫይረስ የቀሰቀሳቸው የአና የሚበሉ ሥዕሎች

አና ሆይኒትዝካ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, አና ሆይኒትዝካ

አና ሆይኒትዝካ ለ4 ዓመታት ኢትዮጵያ ከኖረች በኋላ ወደ ትውልድ አገሯ እንግሊዝ የተመለሰችው ከጥቂት ወራት በፊት ነበረ። 

እርሷ ከወራት በፊት ከኢትዮጵያ ትውጣ እንጂ "ኢትዮጵያ ከውስጤ አልወጣችም" የምትለው አና ትንሽ ከባህሉም ትንሽ ትንሽ ደግሞ ከቋንቋው በውስጧ እንዲቀር አሁንም ጥረት እያደረገች ነው።

አልፎ አልፎ ስታወራ 'እሺ' እና 'እንዴ' የሚሉት ቃላት ከአፏ እንደማምለጥ እያሉ በእንግሊዝኛ ንግግሯ መሃል አግራሞቷን የምትገልፅባቸው ጊዜያትም ብዙ ናቸው። በተለይ በሐበሾች በምትከበብባቸው ጊዜያት ላለመርሳት ይመስል በንግግሯ መካከል የምታውቀውን አማርኛ ጣል ጣል ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም። 

አና ባለፈው እሁድ የተከበረውን የፋሲካ በዓል ባታከብረውም እንኳ 'ጣፋጭ' የምትላቸውን ጊዜያት አብሬያቸው አሳልፌያለው የምትላቸውን ጓድኞቿን በማሰብ፤ በግሏ ማኅበራዊ ድረ ግፅ ላይ መልካም ምኞቷን ገልጻላቸዋልች፤ ለዚያውም ባልተለመደ ሁኔታ በሙዝ ላይ የመስቀል ስዕል ሰርታ በአማርኛ 'መልካም ፋሲካ' በማለት። 

'መልካም ፋሲካ' የተሳለበት ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, ፋሲካ

አና በሙዝ ላይ ስዕል መሳል የጀመረችው ግን ሙዝ መመገብ አስጠልቷት ወይንም በጥበብ ጎዳና ተመርታ ልዩ ሥራ በማቅረብ ፍላጎት ተነሳስታ አልነበረም። አና ከወር በፊት የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ታይተውባት ለ10 ቀናት በመኝታ ቤቷ እራሷን አግልላ በቆየችበት ወቅት ነው።

"ወላጆቼ ዕድሜያችው ከፍ ያለ ስለሆነ እንዳይታመሙ በጣም እሰጋ ነብር። ለ10 ቀናት ሳላገኛቸው በክፍሌ ውስጥ እራሴን ሰወርኩኝ። ህመሙ ሻል እያለኝ ሲመጥጣ ግን ላብድ ትንሽ የቀረኝ መሰለኝ" የምትለው አና ከቤተስቦቿ ጋር የምትኖረው ገና ከኢትዮጵያ መመለሷ ስለነበረ እንደሆነ ታስረዳለች።

'ለንደን' የተሳለበት ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, ለንደን

ሕይወትን እንዳዲስ እስክትጀምር ወላጆቿ ጋር የተቀመጠችው አና በዕድሜ የገፉት እናትና አባቷ በኮሮናቫይረስ እንዳይታመሙ በጣም ትሰጋ እንደነበር ትናገራለች። ብቻዋናም መኝታ ቤቷን ዘግታ የተቀመጠችው አና፤ ወላጆቿ የማይጋሩትን መታጠቢያ ቤት ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ከክፍሏ አትወጣም። 

አና እራሷን ለይታ በቆየችባቸው የመጀመሪያዎቹን ቀናት ተኝታ ብታሳልፍም ቀኑ እየጨመረ ሲሄድና የህመሙ ምልክት ሻል ሲላት ቁጭ ብላ መመገብ ጀምራ ነበር። ታዲያ በአንዱ ዕለት ለምሣ ቀርቦላት የነበረው የሙዝ ሽፋን ላይ እንደ ቀልድ መሞነጫጨር ጀመረች።

የጠረጠረችው የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክቶች ለይተው ወይ ነጻ እስክትሆን ካልሆነም የህክምና ድጋፍ እንድታገኝ እስኪደረግ ምንም ሳትሠራ በአንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፎ መቀመጡ ከበሽታው በላይ ህመም የሆነባት አና ይህን አዲስ ግኝት በየዕለቱ ሥራዬ ብላ ተያያዘችው። 

ከዚያ ጊዜ ወዲህ ታዲያ እንደ ኤሚ ዋይንሃውስ እና ዘ ቢትልስ የተሰኙትን ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ በልጅነት የተጫወተቻቸውን ጨዋታዎች፣ የምትወዳቸውን እንስሶችና ከኢትዮጵያ የሚናፍቋትንም ነገሮች በሙዝ ላይ ሙንጭር ሙንጭር አርጋ በመሳል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ለዘመድ ወዳጆቿ ማጋራት ጀመረች። 

'ኤሚ ዋይንሃውስ' የተሳለችበት ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, ኤሚ

አና ከህመሙ በደንብ እንደተሻላት ስታውቅ ለቀናት እራሷን ለይታ ከቆየችበት መኝታ ቤቷ ወጥታ በሽታው እንዳይዛቸው ከተጠነቀቀችላቸው አዛውንት ከወላጆቿ ጋር ተቀላቀለች።

ነገር ግን አና ካጋጠማት ህመም ብታገግምም የብሪታኒያ መንግሥት የበሽታውን መዛመት ለመቆጣጠር ሲል ባወጣው ሕግ መሠረት ከቤት በመውጣት ሌላ ቦታ መሄድ አልቻለችም። በዚህም ምክንያት የምታያቸውንና በምናቧ የሚከሰቱ ነገሮችን በሙዝ ላይ መሳሏን ቀጠለች። 

አናም "ሙዝ ላይ ሥዕል አሰፍራለሁ ብዬ መቼም አስቤ አላውቅም ነበር። ልጅ እያልሁ እስል እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ግን ዕድሜ እየገፋ ሲመጣ እንደሚረሱ ልማዶች ሁሉ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ የሥዕል ዝንባሌዬ ትቼው እንደነበረ በዚህ ጊዜ ታወሰኝ። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ስላልተረሳኝ ብዙዎችን ያስደሰቱ ሥዕሎችን ቢያንስ በማህበራዊ ገፆች ለዕይታ ማቅረብ ችያለሁ" ትላለች። 

ቡና የተሳለበት ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, ቡና

ከሙዝ ሌላ ምንም ዓይነት ፍራፍሬም ሆነ አትክልት ላይ ስዕሎችን የማትሞክረው አና "ለሙዝ የተለየ ፍቅር ወይም ጥላቻ ኖሮኝ አይደለም። በአጋጣሚ እጄ ላይ ሙዝ ስለተገኘ ብቻ ነው አሁን ርዕስ ለመሆን የበቃው" ትላለች።አክላም "ብዙ ሰዎች ሙዞቹ ላይ በብዕር የምስልባቸው ይመስላቸዋል ነገር ግን እየሳልኩባችው ሳይሆን ስጫንና ስቧጭራችው መጀምሪያ ምንም ምልክት ባይኖርባቸውም ብዙም ሳይቆዩ ግን የተጫሩበት ቦታ ላይ መበለዝ ይጅምራሉ።

"እኔ ባውጣሁላቸው መስመሮች መሠረት ቀስ በቀስ እየበለዙ ቅርፁን ተከትለው የሣልኩባቸውን ነገሮች አጉልተው ያወጣሉ" በማለት በቅርብ ያካበተችውን ችሎታ እንዴት እንደምታቀናብር ታስረዳለች። ሙዞቹ ሽፋን ላይ አና በምታሳርፍባቸው የመጫን ኃይል መሠረት ሲበልዙ፤ ወይ ጠቆር ወይም ደግሞ ፈዝዝ እያሉ ማሳት የምትፈልገውን ምስል ያወጡላታል።

በዚህም መሰረት በየቀኑ አልያም አለፍ አለፍ እያለች የተለያዩ ለዓይን ደስ የሚሉና ሙዞቹን ለመብላት የሚያሳሱ ሥዕሎችን ታሰፍርባቸዋለች። "ሙዞቹ ከቧጨርኳቸው በኋላና አንዴ መበለዝ ከጀመሩ ጊዜ አንስቶ ብዙም አይቆዩም። እንደውም ሥዕሎቹ እንደዛ በውበት እንዳልደመቁት ጭራሽ ምንነታቸው እስኪጠፋ ሙሉው የሙዞቹ ሽፋን መበለዝ ይጀምራል።

ዘ ቢትልስ የተሳሉበት ሙዝ

የፎቶው ባለመብት, Anna Chojnicka

የምስሉ መግለጫ, ዘ ቢትልስ

"አንዳንዶቹ ብቻ አንድ ሁለት ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ" የምትለው አና ሆን ብላ ሙዞቹን ታበልዛቸው እንጂ ምንም ቢብልዙ ከመብላት እንደማትቆጠብ ትናገራለች።

"ሲጀመር ይህን ማድረግ የጀመርኩት ሥዕሎቹ ለዕይታ እንዲቅርቡ ወይንም ሙዞቹ እንዲቀመጡ አይደለም። ለእዕምሮዬ ሰላም ስል ብቻ ነበር። መሞነጫጭሩ ሃሳቤን ስብስብ አድርጎ እጆቼ ከሚሰሩት ሥራ ውጪ ሌላ ነገር እንዳላስብ ስለሚያግዝኝ ብቻ ነው። በተለይ በአሁን ሰዓት" ትላለች።

እነዚህ በሙዝ ቆዳ ላይ በአና የሚሰሩት ሥዕሎች እድሜያቸው ከጥቂት ቀናት የዘለለ ባይሆንም ፎቶ በማንሳት ለጓደኞቿ ታጋራቸዋለች። ከሁሉ በላይ ግን በኮሮናቫይረስ ምክንያት እራሷን ለይታ በአንድ ክፍል ውስጥ በቆየችባቸው ጊዜያት ብቸኝነቷን እንድትቋቋም ከማድረግ ባሻገር በውስጧ ተዳፍኖ የነበረውን የሥዕል ዝንባሌ እንድታወጣ ረድቷታል።