በኢትዮጵያ የሰሞኑ አለመረጋጋት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተባለ

ምርመራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው ሳምንት ከሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰልፈኞች ላይ የታየው መዘናጋት በቀጣይ ወራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋት መኖሩ ተገለፀ።

በተለያዩ ምክንያቶች የሚታዩ መዘናጋቶች አሳሳቢ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ትናንት በነበራቸው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር ከ15 ቀን በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት በነበረው አለመረጋጋትና የተለያዩ ሁኔታዎች በሚፈለገው መጠን የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ አልተቻለም ነበር ያሉት ሚኒስትሯ በዚህም የተነሳ የምርመራው ቁጥር በከፍተኛ ሁናቴ ቀንሷል ብለዋል።

ሚንስትሯ አክለውም በተደረጉ ሰልፎችም ሆኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎች የኮሮና መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃ ባለመወሰዱ በቀጣይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት መኖሩን ተናግረዋል።

ዶ/ር ሊያ ታደሰ ቸልተኝነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ጠቅሰው "ከጥቂት ወራት በኋላ ወደኋላ የማንመለስበት ዋጋ ሊያስከፍለን ስለሚችል" በማለት ወጣቶች ጥንቃቀ እንደያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶች የተጓዳኝ ሕመሞችና ላለባቸውና ለአረጋውያን ቫይረሱን አስተላልፈው ከባድ ችግር ሊከሰት ይችላል በማለት የጥንቃቄ መልእክቶች እነዲተገበሩ ሲሉ ተናግረዋል።

ሰሞኑን አለመረጋጋት ተስተውሎባቸው በነበሩ አካባቢዎችም በትኩረት ምርመራ እንደሚደረግ ዶ/ር ሊያ ጨምረው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ከ260 ሺህ በላይ ናሙናዎች ተመርምረው 6 ሺህ 774 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

ኮሮና
Banner