"በአንድ ምሽት ቤታችን ወደ ኮሮናቫይረስ ማዕከልነት ተቀየረ"

ሙኩልና አስራ ሰባቱ የቤተሰብ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Mukul Garg

የምስሉ መግለጫ, የነ ሙኩል ቤተሰቦች አስራ ሰባት ናቸው

እንደ ህንድ ባሉ አገራት ከተለያየ ትውልድ የተወጣጡ ቅድመ አያት፣ አያት፣ አጎት፣ አክስት ልጆች፣ ዘመድ አዝማዱ ተሰባስቦ የሚኖርበት ሁኔታ በቅድመ ኮሮናቫይረስ ወቅት የሲሳይ፣ ደስታና መፈቃቀር ጊዜ ነበር።

ማን ያውራ የነበረ እንዲሉ የእነ ሙኩል ጋርግ አስራ ሰባት አባላት ያሉት ቤተሰብም፤ ደስታና ሃዘን ሲፈራረቅ፣ ሠርጉ በዓሉን፤ ክፉውን ደጉን እያዩ መከራም ሆነ ሌላው ሳይፈትናቸው አብረው ኖረዋል።

መቼም የሰውን ልጅ አኗኗር ስር ነቀል ለውጥ እያስከተለ ያለው የኮሮናቫይረስ፤ መሰባሰብን ከሩቁ እንዲሸሽ ብዙዎችን አስገድዷል። ለእነ ሙኩል ቤተብም በሽታው ሌላ አደጋን ጋርጦ ነበር፤ ከአኗናራቸው፣ ከትውፊታቸው ሊነቅል የሚችል አደጋ።

ዕለቱ አርብ ሚያዝያ 16/2012 ነበር። ሙኩል የሃምሳ ሰባት ዓመት አጎቱ ሙቀት፣ ሙቀት ሲላቸው ብዙም አላስጨነቀውም ነበር። ሆኖም ነገሩ በእሳቸው አልተወሰነም በአርባ ስምንት ሰዓታትም ውስጥ ሌሎች ሁለት የቤተሰቡ አባላትም ታመሙ።

ከፍተኛ የሙቀት መጠን፤ የድምፃቸው መሻከር፣ መጎርነንና ሳልም መከታተል ጀመረ። ሙኩልም ያው የወቅቱ ጉንፋን ነው ብሎ ችላ አለው፤ ኮሮናቫይረስ ሊሆን ይችላል የሚለውን ማመንም ሆነ መቀበል አልፈለገም።

"በቤታችን ውስጥ አንዳንዴ አምስት፣ ስድስት ሰው ይታመማል፤ ከሰው ሰውም ይጋባል እና ምንም መረበሽ አያስፈልግም" ራሱን ለማፅናናት የተናገረው ነበር።

በቀጣዮቹ ቀናትም አምስት ተጨማሪ የቤተሰቡ አባላት የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ሲያሳዩ ልቡ መሸበር ጀመረ።

በቀናትም ውስጥ ከአስራ ሰባቱ ውስጥ አስራ አንዱ ታመሙ፤ ሲመረመሩም አስራ አንዱም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ።

"ከውጭ ያገኘነው ሰው የለም፤ ወደ ቤታችን የመጣም ሰው የለም። ሆኖም ኮሮናቫይረስ ቤታችን ገብቶ በርካታ የቤተሰባችን አባላት ታመዋል" በማለት በድረገፁ ላይ የፃፈው ሙኩል በመቶዎች የሚሆኑ አስተያየቶችን ከአንባቢዎች ተቀብሏል።

ህንድ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አስገዳጅ የቤት ውስጥ መቀመጥ ውሳኔን ያስተላለፈችው መጋቢት 16/2012 ዓ.ም ሲሆን እስከዚህ ሳምንትም ድረስ እየተራዘመ ቆይቷል።

አርባ በመቶ የሚሆኑት ህንዳውያን ከተለያየ ትውልድ የተውጣጡ ቤተሰቦች በአንድ ጣራ ነው የሚኖሩት።

በአንድ ቤት ውስጥ እንዲሁ በተለያየ እድሜ ያሉ ቤተሰቦች ሰብሰብ ብለው ከመኖራቸው አንፃር ድንገት አንድ ሰው እንኳን በቫይረሱ ቢያዝ ሌሎችም የመጋለጣቸው ዕድል በጣም ከፍተኛ ነው።

እንዲህ እንደ ሙኩል ላሉ ትልቅ ቤተሰቦች ደግሞ አካላዊ ርቀት መጠበቅ የማይታሰብም ቅንጦትም ነው። ከውጪው ዓለም ተነጥለው ቤት ውስጥ ተቀምጠው ባሉበት ሰዓት ሰው እንዴትስ ከቤተሰቡ ይርቃል?

"የብቸኝነት ስሜት ተሰማን"

በሰሜናዊ ደልሂ በተጨናነቀ ሰፈር ኑሯቸውን ያደረጉት እነ ሙኩል ቤታቸው ሦስት ፎቅ ነው።

የ33 ዓመቱ ሙኩል፣ የ30 ዓመት ባለቤቱ፣ የስድስትና ሁለት ዓመት ልጆቻቸው፣ ወላጆቹና ከአያቶቹ ጋር ሆነው በሦስተኛ ፎቅ ላይ ይኖራሉ።

ከእነሱ በታች ባሉት ሁለት ፎቆች ደግሞ የአባቱ ወንድሞች (አጎቶቹ) ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይኖራሉ። በአጠቃላይ አስራ ሰባት አባላት ያሉት ቤተሰብ በእድሜ ደረጃ ቢታዩ ከአራት ወር ጨቅላ እስከ 90 ዓመት አያት የሚኖሩበት ነው።

በደልሂ የሚገኝ የአትክልት መሸጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንዲህ ሰብሰብ ብለው የሚኖሩበት ነው ሲባል የተጨናነቀ ሊመስል ይችላል። ነገሩ ወዲህ ነው።

ቤታቸው የተንጣለለና ሰፊ ነው። እያንዳንዱ ፎቅ አንድ የቴኒስ ሜዳ እጥፍ በሚባል ሁኔታ 250 ካሬ ሜትር የሚሸፍን፣ ሦስት መኝታ ክፍሎች ከመታጠቢያ ቤቶች ጋርና በርካታ ማዕድ ቤቶችን የያዘ ነው።

በተንጣለለ ቤት ቢኖሩም ቫይረሱን በፍጥነት ከመዛመት አላገደውም። ከፎቅ፣ ፎቅም ተሻግሮ ሁሉንም ትልልቅ ሰዎች ሊያጠቃ ችሏል።

በቫይረሱ መጀመሪያ ተያዘ የተባለው የሙኩል አጎት ሲሆን እንዴት ቫይረሱ እንደያዘውም ለቤተሰቡ ግልፅ አይደለም፤ ከጥርጣሬ በስተቀር።

"ምናልባት ከአትክልት መቸርቸሪያ ቦታ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ እቃ ልንገዛ መደብር በሄድንበት ወቅትም ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ወቅቶች ብቻ ነው ከቤት የወጣነው" ይላል ሙኩል።

መታመም ሲጀምሩ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም በመጀመሪያው ወቅት በፍራቻና በእፍረት ተሸብብው አልተመረመሩም።

"አስራ ሰባት ብንሆንም የብቸኝነት ስሜት ተሰማን። በቫይረሱ ተይዘን ብንሞት ቀብራችን ላይ ማንም አይመጣም የሚለውን ስናስበው ጭንቀት ነው የለቀቀብን። ከኮሮናቫይረስ ጋር ተያይዞ የመጣው መገለልና አድልዎ በቀላሉ የሚታይ አይደለም" ብሏል።

እናም ሳምንታትም ቆዩ ፤ የሃምሳ አራት ዓመቷ አክስቱ ትንፋሽ ሲያጥራት ሆስፒታል ለመውሰድ ተገደዱ። እነሱም መመርመር እንዳለባቸውም ወሰኑ።

"የህመም ወር"

የግንቦት ወርን ሙሉ ከቫይረሱ ጋር እየታገሉ ነው ያሳለፉት።

ሙኩል ዶክተሮች ጋር በየቀኑ ይደውላል፤ ረዥም ሰዓትም ያወራል። በተቻለ መጠንም ቤተሰቡ እንዳይገናኝ በማድረግም በዋትስአፕ ያወራሉ።

"የህመም ምልክታቸውን እያየን የቤተሰቡን አኗኗር መቀያየር ጀመርን። ለምሳሌ ባልና ሚስትም ቢሆኑ ከፍተኛ ሙቀት ካላቸው በአንድ ክፍል ውስጥ እንዳይሆኑ ማድረግ ነበረብን" በማለት ያስረዳል።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በቫይረሱ ከተያዙት ከአስራ አንዱ ውስጥ ስድስቱ ላይ ስኳር፣ የልብ ህመምና፣ የደም ግፊት መኖሩም አሳሳቢ ነበር።

"በአንድ ምሽትም ነው ቤታችን ወደ ኮሮናቫይረስ ማዕከልነት የተቀየረው። እየተፈራረቅንም እንደ ነርስ በመሆን አንዳችን አንዳችንን መንከባከብ ነበረብን" ይላል ሙኩል።

በህንድ፣ ጋዚባድ የሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"በተለያየ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በአንድ ጣራ ስር ሲኖሩ አደጋ የሚሆነው በእድሜ ለገፉት ነው" በማለት ዶክተር ፓርቶ ሳሮቲ ሬይ ያስረዳሉ።

ሙኩልንም በጣም ያስጨነቀው የዘጠና ዓመቱ አያቱ ጉዳይ ነበር።

ነገር ግን የቫይረሱ ሁኔታ በበርካታ የጤና ባለሙያዎች ዘንድ እንኳን ሚስጥራዊነቱ ቀጥሎ ለነ ሙኩል ቤተሰቦችም አንዳንድ ያልተጠበቁ ክስተቶችን አስተናግደዋል።

በሰላሳዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙት እሱም ሆነ ባለቤቱ ምንም ምልክት የማያሳዩ ህሙማን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡን ያስደነቀው አያቱ ምልክት አለማሳያታቸው ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ተደራራቢ ህመም ያለባቸው የቤተሰቡ አባላት ህመሙ ሳይጠናባቸው ምንም ችግር የሌለባት አክስቱ ጠንቶባት ወደ ሆስፒታል ተወሰደች።

ሙኩል በድረገፁ ላይ የጻፈው ጦማር አላማም ከሚያነቡት ሰዎች የሃሳብ እርዳታን በመሻት ቤተሰቡ የደረሰበትን ጭንቀት ለማጋራት ብሎ ነው።

"መጀመሪያ አካባቢ ሰዎች ምን ያስባሉ በሚል ብዙ ተጨንቀን ነበር። ነገር ግን ከጽሁፌ በኋላ የተሰጡትን አስተያየቶች ሳነብ ብዙዎች በቫይረሱ መያዝ የሚያሳፍር አይደለም፤ አይዟችሁ የሚሉም ማፅናኛ ስለነበር ቀለል አለን" ይላል።

ግንቦት በገባ ሁለተኛ ሳምንትም ምልክቶች መጥፋት ጀመሩ፤ ብዙዎቹም ሲመረመሩም ነፃ ሆኑ። ሆስፒታል የገባችው አክስቱም ነፃ ተብላ ወጣች። ክፉውን ጊዜም አለፉት፤ እፎይም ማለት ጀመሩ።

ግንቦት ሦስተኛ ሳምንት አካባቢም እሱን ጨምሮ ሦስት የቤተሰቡ አባላት ከኮሮናቫይረስ ነፃ አልነበሩም። ሆኖም ግንቦት 24/2012 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ ሲመረመሩ ነፃ ተባሉ።

"ክፉና ደጉን ያየንበት ጊዜ"

በህንድ ያሉ ትልልቅ ቤተሰቦች የድጋፍና እንክብካቤ ምንጭ ቢሆኑም ከሃብት ክፍፍልም ጋር በተያያዘ ግጭቶችም ይነሳሉ። በዚህ ክፉ ወቅት ግን አንዱ ላንዱ መቆሙ፣ እንክብካቤም በቀላሉ ማግኘት መቻል መልካም ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።

"የእድሜ ባለፀጋ የሆነ ሰው ያለምንም እርዳታ በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት እንዴት ይታሰባል? ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም በአንድ ቤት ውስጥ አብሮ መኖር ትንሾች ትልልቆችን የሚንከባከቡበት እድል ይፈጥራል፤ ይህም መኖሩ መልካም ነው" ይላሉ ዶክተር ጆን።

በህንድ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ250 ሺህ መብለጡን ተከትሎ ወረርሽኙ ለእንዲህ አይነት ቤተሰቦችም ስጋት ደቅኗል። ወጣቶች በዕድሜ ጠገብ ያሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ በሽታውን እንዳያዛምቱ ፍራቻ አድሮባቸዋል።

የደልሂ ጎዳና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ለምዕተ ዓመታት ዘመድ አዝማድና ቤተሰብ አብሮ ኖሯል። ይህንንም የምዕራባውያን እሴቶችም ሆነ ቅኝ ግዛት ሊሸረሽረው አልቻለም" በማለት በካንፑር በሚገኘው ሲኤስጄኤም ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኪራን ላምባ ጅሃ ያስረዳሉ።

"ኮሮናቫይረስም ይህንን የኑሮ ዘያችንን፣ ትውፊታችንን አይሸረሽርም" ብለዋል ፕሮፌሰሯ።

እነ ሙኩልም በፕሮፌሰሯ ሃሳብ ይስማማሉ። ቫይረሱ ፈትኗቸዋል፤ አስተምሯቸዋል እንዲሁም ሌላም፣ ሌላም ግን በአንድነትም ተወጥተውታል።

ከቫይረሱ በፊት የነበረው የቤተሰቡ አኗኗርና ሃብት የ90ዎቹን የቦሊውድ ፊልም ይመስል እንደነበር ሙኩል በመቀለድ ያስታውሳል።

"በዚህ አንድ ወር ውስጥ አንድ ላይ እንዳሳለፍነው ወቅት መቼም ቢሆን አብረን ሆነን አናውቅም ነበር። ቤተሰቡ በህብረት መሆኑ አስደሳች ነበር" ለሚለው ሙኩል በየተራ ሲታመሙ ማየት ግን ቀላል አልነበረም።

"ቤተሰቡ ክፉውንም ደጉንም ያየበት ወቅት ነው፤ ጠንካራም አድርጎናል" ይላል።

አክሎም "ምንም እንኳን ለሁለተኛ ጊዜ በቫይረሱ መያዝ ሁኔታ እንዳለ ብንረዳም፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ቫይረሱን መርታት በመቻላችን የተሰማንን ደስታ አብረን እያከበርን ነው" ብሏል።

ኮሮና
Banner