በአፍሪካ ስላለው የኮሮናቫይረስ ዘገምተኛ አካሄድ ምን ማለት ይቻላል?

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL TEWELDE
የኮሮናቫይረስ በቻይናዋ ዉሃን ከተነሰባት እለት ጀምሮ የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ በርካታ መላምቶች ስለ አህጉሪቷ እናውቃለን ከሚሉ አካላት ተሰምቷል።
በአህጉሪቷ ቫይረሱ በግብጽ ከተመዘገበበት የካቲት 6/2012 ዓ.ም በፊትም ለምን አህጉሪቷ ውስጥ ለመግባት ዘገየ? ብለው ከሚጠይቁ ወረርሽኙ በአህጉሪቷ ውስጥ ከተዛመተ የአፍሪካውያን መጥፊያ እንደሆነም ተተንብይዋል።
ወረርሸኙ በተለያዩ አገራት መዛመት ሲጀምሩ 'አፍሪካውያን ሊያልቁ ነው' የሚሉ ቃለ መጠይቆችም ተሰምተዋል። በሚያዝያ ወር ላይ ሜሊንዳ ጌትስ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የአፍሪካውያን አስከሬኖች በጎዳናዎች ላይ እንደሚረፈረፉም ታይቷቸው ነበር።
ምንም እንኳን በኮሮናቫይረስ በሚያዙ ሰዎች ሆነ በሟቾች ቁጥር አሜሪካ እንዲሁ አውሮፓውያን ቢመሩም፤ የምዕራቡ ዓለም ተቋማትም ሆነ የጤና ልኂቃን ትንበያ መስጠትም አልደፈሩም።
በአስር ሺህዎች እያለቁ ላሉት አውሮፓውያን መላምቶች ሳያስቀምጡ መቶዎች ባልሞቱባት አህጉር ሚሊዮኖች ሊያልቁ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽንም ሆነ ሌሎች ሪፖርቶች ሲያወጡ ታይተዋል።
የጤና ልኂቃኑ የሃምሳ አራት አገራትን ሁኔታ እንደ አንድ አገር እንዲሁም መንደር አድርገው የጤና ሥርዓት የላሸቀ መሆኑንም አስተያየታቸውን ሲሰጡ፤ አፍሪካውያን በራሳቸው ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ተደርገው የእርዳታ ጥሪ ሲጎሰምላቸው፤ የኮሮናቫይረስን መዛመት ለመግታት የጤና ሥርዓታቸውም ሆነ ማዕከላቱ ብቁ ናቸው ብለው በሚያሞካሿቸው አውሮፓ አገራት ወረርሽኙን መቆጣጠር ተስኗቸዋል።
በርካታ የአፍሪካ ምሁራንም ሃምሳ አራት አገራት ታሪክ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚ የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የሁሉም በተናጠል ሊታይ ይገባል። እንደዚህ አይነት ሪፖርቶች ማውጣት ፖለቲካዊ ትርጉም እንዳለውና መላው የአፍሪካ አገራትን እንደ አንድ መንደር አድርጎ ማየት ከቅኝ ግዛት እሳቤም ጋር የተመሳሰለና "አፍሪካውያንን ኋላ ቀርና እርባና የሌላቸው" የሚለውን አስተሳሰባቸውን ያንፀባረቁበት ነውም በማለትም ተችተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በመጀመሪያው ዓመት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከ83ሺህ አስከ 190 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉና፤ ከ29 እስከ 44 ሚሊዮን ሰዎችም ሊጠቁ እንደሚችሉ ቢገምትም፤ በአፍሪካ ውስጥ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በርካታ የምዕራባውያን ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች ከሰጧቸው መላ ምቶች ተቃራኒ መሆኑ ብዙዎች ላይ ተስፋን አጭሯል።
በአህጉሪቷ ውስጥ እስካሁን ባለው መረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 125 ሺህ 640 ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 51 ሺህ 462ቱ አገግመዋል፤ 3 ሺህ 709 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት አህጉር ቁጥሩ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ትንሽ ነው የተባለ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ ሌሎች የአህጉሪቷን ሁኔታ የሚተነብዩ ባለሙያዎች በአፍሪካ እንደተፈራው ላይሆን ይችላል እያሉ ነው።
በአፍሪካ የተመዘገበው ቁጥር ለምን አነሰ ለሚለው የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጠ ሲሆን፤ ለዚህም በርካታ የአፍሪካ አገራት የጉዞ እገዳን ጨምሮ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድ፣ የሰዓት እላፊ መመሪያ እንዲሁም ድንበሮቻቸውን መዝጋት፣ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ማስገባት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ጠቅሟቸዋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የአህጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር አብዛኛው ወጣት መሆኑ እንደ ምክንያትነት የተገለፀ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላስመዘገበችው የምርመራ ቁጥሯ ትንሽ በመሆኑ እንደሆነም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የምርመራ ቁጥር ትንሽ መሆን በቫይረሱ ለተያዙት ቁጥር ላለመጨመር እንደ ምክንያትነት ቢገለጽም በሆስፒታሎች የሚመዘገበው የህሙማን ቁጥር አለመጨመሩ፣ እንዲሁም ከሆስፒታሎች ውጪ ሞቶች አለመመዝገባቸውም አገራቱ ወረርሽኙን ተቆጣጥረውታልም እየተባለ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዴት ናቸው?
በአፍሪካ ቀንድ ካሉ አገራት መካከል አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ባላት ጂቡቲ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ ሦስት ሺህ ደርሷል። አገሪቱም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ ምርመራ ያደረገች ሲሆን፤ ይህም ከሕዝብ ቁጥሯ ጋር ሲነፃፀር እንደነ ፈረንሳይ ካሉ አገራት በልጣ አቅሟ 25 ሺህ 600 በሚሊዮን አድርሷታል። ጂቡቲ 20 ዜጎቿንም በኮሮናቫይረስ አጥታለች።
የኮሮናቫይረስ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረባት ካለችው ጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ድንበር አቋራጭ አሽከርካሪዎችም በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዪት የወጡ መረጃዎችም ያሳያሉ።
የኮሮናቫይረስ የመርመር አቅሟን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረች ያለችው ኢትዮጵያም ቫይረሱ ከተገኘበት እለት ጀምሮ በመቶዎች ከመርመር ጀምራ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን በቀን መመርመር ችላለች።
ኢትዮጵያ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎችን ብትመረምርም ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ባለቤት ከመሆኗ አንፃር በሚሊዮን ሲሰላ 842 ነው። ኢትዮጵያ የመርመር አቅሟን በመጨመር በቀን ከአስር ሺህ በላይ ሰዎችን የመርመር እቅድ እንዳላት ተገለጿል።
በተጨማሪም አገሪቷ አርባ ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የሙቀት ልኬት በማድረግ አመርቂ ሥራ እየሰራች እንደሆነ ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል። ከዚህም በተጨማሪ ለሃምሳ ሺህ ሰዎች የሚሆን የለይቶ ማቆያ ማዘጋጀቷን ዘገባው አክሎ ገልጿል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት በዘፈቀደ የማይመረምሩ ሲሆን ለመርመር የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የላብራቶሪ ናሙናዎች የምትመረምረው ይበልጥ ተጋላጭ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ከጤና ተቋማት፤ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ካላቸው ሰዎች እንዲሁም በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች በመውሰድ ነው።
በሶማሊያ 1 ሺህ 741 ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፤ 67 ዜጎቿንም በበሽታው አጥታለች። አገሪቱ ምን ያህል ሰዎችን እንደመረመረች ግን መረጃ የለም። በኤርትራም እንዲሁ በቫይረሱ የተያዙት 39 ሰዎች ሙሉ በሙሉ ማገገማቸው ተገልጿል። አዳዲስ የሚመዘገቡ ሰዎችም እንደሌሉ ቢገለፅም እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደተመረመሩ የተገኘ መረጃ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
ማኅበረሰቡ ማዕከል የሆነበት የመከላከል ሥራ
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራት መከላከሉ ላይ ማተኮራቸው የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሙቀት ልኬት መደረጉ፣ ከመንግሥት በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ማዕከል የተደረገበት የመከላከል ሥራም እየተከናወነ ይገኛል።
ማኅበረሰቡ በራሱ ፈቃደኝነት እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ እንዲሁም መመሪያዎችንም በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየሰራ ይገኛል።
በኢትዮጵያም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ፀረ-ተህዋሲያንንና የፊት ጭምብሎችን በነፃ ማደል እንዲሁም የቬንትሌተርም ሆነ ሌሎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁሶች ፈጠራ የተሞላባቸው አስተዋፅኦዎች ተስተውለዋል።
ማኅበረሰቡ ራሱን አስተባብሮ ወረርሽኙን ለመግታት የሚያደርገው ጥረት፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶችንም በመተግበር እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ በርካታ በአፍሪካ ላይ ጨለምተኛ አቋም ያላቸው ተቋማት እያዩት አይደለምም ተብሎ ይተቻል።
በዚህም አፍሪካ ለሌሎች አህጉራት ማስተማር የምትችለውም ልምድ አለ እየተባለ ነው። እነዚህም ተግባራት ወረርሽኙን በመቆጣጠር ምን ያህል እያገዙ እንደሆነም ከግምት ውስጥ ሊገቡ እንደሚገባም አስተያየት ሰጭዎች ይናገራሉ።
በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንደ ኤችአይቪ፣ ቲቢና የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር የተዘረጉ ዘዴዎችንም እየተጠቀሙ ሲሆን፤ ተጋላጭ የሆነውን ማኅበረሰብ መለየት እንዲሁም ህዝቡን የማስተባበር ሥራም እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።
ሆኖም በተለያዩ አገራት ውስጥ የተስተዋለው የውሃ፣ መብራት፣ የመፀዳጃ ቤቶችና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችም እጥረት ችግር ደቅነዋል። ማኅበረሰቡ አካላዊ ርቀትንም ለመጠበቅም ሆነ ንፅህናውን ለመጠበቅ በተጨናነቁ ሰፈሮችስ ውስጥ እንዴት ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎች በርክተዋል።
መንግሥታት አካላዊ ርቀትን እንዲጠበቁ እንዲሁም እንቅስቃሴ የሚገድቡ መመሪያዎችን ሲያወጡ የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ፣ በየቀኑ የዕለት ጉሮሮውን ለመድፈን የሚያደርገውን ሩጫ ከግምት ውስጥ ያስገባም አይደለም ተብለውም ተተችተዋል።
ምንም እንኳን በአብዛኛው በሕዝቡ ውስጥ ቸልተኝነት እንዳለ ሆኖ መንግሥታት ለሚያወጧቸው መመሪያዎች ከሕዝቡ ጋር መጣጣሙን ሊያጤኑት ይገባልም ተብሏል። በተለያዩ አገራት ችግሮች ቢስተዋሉም ቫይረሱን ለመቆጣጠር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውም ልብ ሊባል እንደሚገባ ተንታኞች ይናገራሉ።
በተለያዩ አገራት ያለው የመርመር አቅም
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር በመመርመር ደቡብ አፍሪካ የአንበሳውን ድርሻ የያዘች ሲሆን ከዊንዶ ሜትር በተገኘ መረጃ ከ634 ሺ በላይ ሰዎችን መርምራለች።
በዚህም መሰረት የመመርመር አቅሟ ከፍተኛ ከሚባሉት 10 ሺህ 720 በሚሊዮን እንደሆነም መረጃዎች ያሳያሉ። ጋናም ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን የመረመረች ሲሆን፣ ሴኔጋልና ሞሪሽየስም ከፍተኛ ቁጥርን አስመዝግበዋል።
አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ ባለባት ሞሪሺየስ አስር በመቶ ሕዝቧን መርምራ 334 ሰዎችን ያገኘች ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አስሩ ሞተዋል፤ 322ቱ አገግመዋል። በአገሪቱ ውስጥ አዲስ ህሙማን መመዝገብ ካቆመች ከወር በላይ ቢያስቆጥርም ከሰሞኑ ከህንድ የመጡና በለይቶ ማቆያ ያሉ ሁለት ግለሰቦች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሮን፣ ሞሪታንያ፣ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የቤት ለቤት ቅኝቶችን በማድረግ፤ የሙቀት ልኬት ሥራዎች ሰርተዋል። በበርካታ ትንንሽ የአፍሪካ አገራትም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውንም ዜጎቻቸውን ለመመርመር ችለዋል።
ለምሳሌ በሲሽየልስ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው የመዘበችበት የመጨረሻው ቀን ሚያዝያ 3/2012 ዓ.ም ሲሆን ሁሉም አገግመዋል። በናሚቢያም እንዲሁ ለመጨረሻ ጊዜ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የተገኙት ከወር በፊት ሲሆን፤ በለይቶ ማቆያ የነበሩ ከጎረቤት አገር ደቡብ አፍሪካ የመጡ ሁለት ሴቶች ካገገሙ በኋላ የተመዘገበ ቁጥር የለም።
የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ ከሁለት ሳምንት በፊት የነበረን መረጃ ጠቅሰው 1.3 ሚሊዮን ሕዝብ በአህጉሪቱ ተመርምረዋል ብለዋል።
ምንም እንኳን ለሁሉም አገራት ተመሳሳይ አይነት ማጠቃለያ መስጠት ቢያዳግትም በጦርነትና ግጭት የተናጡ አገራት የመርመር አቅም ዝቅተኛ መሆኑ አሳሳቢ ነው ተብሏል።
ከኢንተርናሽናል ሬስኩዩ ኮሚቴ የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳው በአፍሪካ ውስጥ ዝቅተኛ ከመረመሩ አገራት መካከል ቻድና ማሊ የሚጠቀሱ ሲሆን በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ናይጄሪያ እስካሁን የመረመረችው ሰው ቁጥር 44 ሺህ 458 ነው።
ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ በተያዙባት ናይጄሪያ የመርመር አቅምምም 216 በሚሊዮን ነው ተብሏል። ናይጄሪያ ዋነኛ ትኩረቷ በከፍተኛ ቁጥር መመርመር ሳይሆን ከወረርሽኙ ጋር ንክኪ ያላቸውን እንዲሁም የተነሳባቸውን አካባቢዎች በማተኮር እየመረመረች መሆኑን አስረድታለች።
እንደ ታንዛንያ የመሰሳሰሉ አገራት ምን ያህል ሰዎችን እንደመረመሩ ይፋ ከማድረግ የተቆጠቡ ሲሆን ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በተደጋጋሚ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ብለዋል።
ሆኖም ወደ ኬንያና ዛምቢያ የሚሻገሩ የታንዛንያ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ መያዝ እሳቸው ከሚሉት ተቃራኒ ነው። ይህንንም ተከትሎ ኬንያን የመሳሰሉ ጉረቤት አገራት ከታንዛንያ ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ዘግተዋል።
ምንም እንኳን አንዳንዶች በተለያዩ አገራት ያለው የምርመራ ቁጥር ትንሽ መሆኑ በማህኅረሰቡ ውስጥ መዛመቱን አያሳይም፤ እንዲሁም በሽታው የመሰራጨት ሁኔታው ተደብቆ ሊሆን ይችላል ቢሉም ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ በዚህ አይስማሙም።
ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚሰጡት በበርካታ አገራት በማኅበረሰቡ ውስጥ ሞቶች አለመጨመራቸው፤ ምክንያት የሌላቸው ሞቶች አለመመዝገባቸው፤ እንዲሁም ድንገተኛ ወረርሽኝ አለመከሰቱን እንደ ምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
"በአህጉሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታን ስንገመግም በከሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ሆስፒታሎች አልተጨናነቀቁም" ብለዋል። ቢሆንም አሁን ያለውን ሁኔታ በማየት ሁሉ ነገር አዎንታዊ ነው ማለት ባይቻልም፤ አገራት የመርመር አቅማቸውን እንዲጨምሩም በርካታ የጤና ባለሙያዎች እየመከሩ ነው።
ምንም እንኳን የመመርመሪያ መሳሪያዎች እጥረት በአንዳንድ አገራት ቢያጋጥምም አማራጭ የፈጠራ ዘዴዎችን እያጎለበቱ የሚገኙ አገራት አሉ።
ለምሳሌ በሴኔጋል በፓስተር የምርመራ ተቋም እየተሰራ ያለው በፈጣን ሁኔታ መመርመር የሚያስችሉ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ከአርባ ብር ባነሰ ዋጋ እየሰሩ ነው። የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማዕከልም የመርመሪያ መሳሪያዎችን አቅም ለመጨመር የተለያዩ ጅምሮችን ጠንስሷል።
ቫይረሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ መዛመቱን ሪፖርት ባደረጉ አገራት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በመረመሩ ቁጥር በበሽታው የተያዙ ሰዎችመጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፤ አገራቱ እስካሁን በወሰዷቸው እርምጃዎች የቫይረሱን ሁኔታ መቆጣጠር ቢችሉም ከዚህ በኋላ በቀጣዮቹ ወራት ሊወስዷቸው የሚችሉ እርምጃዎች የወረርሽኙን ስርጭት የሚወስኑት ይሆናል ተብሏል።














