በኮሮናቫይረስ ከተቀጠፉ ኢትዮጵያውያን መካከል ጥቂቶቹ

በኮሮና ሀይወታቸውን ያጡት ወገኔ ደበሌ፣ አቶ መንግሥቴ አስረሴና አቶ ዮሴፍ ሲቡ

የፎቶው ባለመብት, Go fund me pages/ Ethiopian Community Association

የምስሉ መግለጫ, በኮሮና ሀይወታቸውን ያጡት ወገኔ ደበሌ፣ አቶ መንግሥቴ አስረሴና አቶ ዮሴፍ ሲቡ

ከጥቂት ዓመታት በፊት በቫይረስ ምክንያት የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ይቆማል፣ ሰዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ቤት ይቀመጣሉ፣ አገራት ድንበሮቻቸውን ይዘጋሉ፣ የአምልኮ ቦታዎች ወና ይሆናሉ፣ የሰው ልጅ የአኗኗር ዘዬውን ይቀይራል፣ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የመጡ ትውፊቶች ቦታ አይኖራቸውም ብንባል ምናልባት ማመን አስቸጋሪ ይሆናል።

ሆሊውድ የሚሰራቸውን ሳይንሳዊ ልብወለድ የፊልም ሃሳቦችን ይመስላሉ ብሎ የሚያጣጥለውም አይታጣም።

የኮሮናቫይረስ ግን የሰው ልጅ ባልጠበቀበት ሁኔታ የማንነካ ነን የሚሉ ታላላቅ አገራትን አንበርክኳል፣ የሰው ልጅ ደረስኩበት የሚለውን የሳይንስ ልህቀት ፈትኗል፣ ለዘመናት ሰዎች የእኔ ናቸው የሚሏቸውን ባህል እንዲሁም የባህል መገለጫዎች መቅረት እንደሚችሉ አሳይቷል።

ከዚህም በላይ የሰውን ልጅ የወደፊት እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፣ በምጣኔ ሃብቱ፣ በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ያለውን አሰላለፍን እንደሚቀይር እንዲሁም አዲስ የዓለም ሥርዓት ያመጣል እየተባለ ነው።

በዚህ ሁሉ ውስጥ በርካቶች የሚወዷቸውን ቤተሰቦች አጥተዋል፤ ቤተ ዘመድ ተሰባስቦ ሐዘኑን አላወጣም፣ በክብርም አልቀበረም። ሐዘናቸውን ለብቻቸው በቤታቸው ይዘው በራቸውን ቆልፈው የተቀመጡትን ቤቱ ይቁጠራቸው።

በተለይም የተወለዱበትን ቀዬ ለቀው፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ፣ ከስር መሰረታቸው ተነቅለው በአሜሪካ ያደረጉ ከመቶ በላይ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸው እየተነገረ ነው፤ በርካቶችም በቫይረሱ ተይዘዋል።

ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሰደር አቶ ፍፁም አረጋ ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ እንደተናገሩት በአብዛኛው ቁልፍ ተብለው በሚጠሩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ከመቶ የማያንሱ በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን ነው።

ከእነዚህም መካከል በአብዛኞቹ ነርሶች፣ የአረጋውያን መጦሪያ እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ የሚሰሩ፣ በሥጋ ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና የመሳሰሉ ዘርፎች የተሰማሩ ናቸው።

ቢቢሲ አማርኛ በተለያዩ አገራት በኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን ህይወትና ኑሮ በመዳሰስ ለመዘከር አቅዷል። በዚህም ሳምንት ካገኘናቸው ውስጥ የተወሰኑትን እነሆ፡

የሦስት ሳምንት ልጇን ሳታይ የሞተችው ወገኔ ደበሌ

ታሪኳን የሰማ ሁሉ በሐዘን ልቡ ተሰብሯል። እንደወጣች የቀረችውን፣ በተገላገለች በሦስት ሳምንቷ የጨቅላ ልጇን አይን ሳታይ የተነጠቀችውን ወገኔ ደበሌን በማስታወስ። በቀብሯ ላይ የባለቤቷን አቶ ይልማ አስፋውን የመረረ ሃዘን፣ ለቅሶና ዋይታን በቪዲዮ ማየት ልብን ይሰብራል።

በሜሪላንድ ታኮማ ፓርክ በተባለ ቦታ ነዋሪ የነበረችው ወገኔ ደበሌ ሳል፣ የምግብ ፍላጎት ማጣትና ድካም ተጫጭኗት ዶክተር ጋር በምትደውልበት ወቅት ምናልባት ኮሮናቫይረስ ሊሆን ስለሚችል ሆስፒታል ሄዳ እንድትመረመር መከሯት።

ወደ ሆስፒታልም ብትሄድም የተሰጣት ምላሽ የኮሮናቫይረስ ለመመርመር ብዙ የታመመች ስለማትመስልና እርግዝናው ሊሆን ስለሚችል በሚል ማስታገሻ ሰጥተው ሸኟት።

ከቀናት በኋላ መተንፈስ ሲከብዳት ወደ ሆስፒታል መጣች ስትመረመርም በኮሮናቫይረስ መያዟ ተረጋገጠ። ልጇንም መገላገል እንዳለባት ዶክተሮች በመወሰናቸው ከወር በፊት ያለጊዜው ህፃኑ በህክምና ተወለደ።

ከሁለት ቀናት በኋላም እየደከመች ስለመጣች ፅኑ ህሙማን ክፍል እንደትገባና ቬንትሌተር እንዲገጠምላት ወሰኑ። ምንም እንኳን ከቀናት በኋላ ጤናዋ ቢሻሻልም ልቧና ኩላሊቷ በቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቃታቸው ሚያዝያ 11/ 2012 ዓ.ም ይህችን ዓለም ተሰናበተች። ልጇም ከሦስት ሳምንታት በኋላ ወደ ቤት በተወሰደ በሁለተኛው ቀን ነው ወገኔ የሞተችው።

ወገኔ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ከመጣች ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ወገኔ ቤት ውስጥ ሆና ልጆች የምታሳድግ ሲሆን ባለቤቷ አቶ ይልማ ደግሞ የትምህርት ቤት የአውቶብስ አሽከርካሪ ናቸው። ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት ወገኔ በላብራቶሪ ቴክኒሺያንነት ታገለግል የነበረች ሲሆን አቶ ይልማ ደግሞ የላብራቶሪ ተቆጣጣሪ ነበሩ።

ታኮማ ፓርክ በሚባለው አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ተወዳጅ ነበረቸው ወገኔ ስትሞትም፤ የታኮማ ፓርክ ከንቲባ ኬት ስቲዋርት በሞቷ የተሰማቸውን ሐዘን ገልፀዋል። በምክር ቤቶች ስብሰባም ላይም የህሊና ፀሎት አድርገውላታል።

ቤተሰቦቿም የገንዘብ እርዳታ በማሰባሰብ ላይ ሲሆኑም ከ257 ሺህ ዶላር በላይ ተሰባስቧል።

ቸርና ከኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን በመርዳት የምትታወቀው ወገኔ በተቻላት አቅም ከአገሯ በሺህዎች ኪሎ ሜትር ርቃ ትንሿን ኢትዮጵያ ለመፍጠርም ትሞክር ነበር።

እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ እንጀራው፣ ቡናው እንዳለ ሆኖ ዘመንና ሰንሰለት የተባሉትን ድራማዎችንም ትወድ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።

በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበር መስራች- አቶ መንግሥቴ አስረሴ

አቶ መንግሥቴ አስረሴ በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበር መስራችና የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ነበሩ። ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ፣ ለማኅበረሰቡ የቅርብ ደራሽ የነበሩት አቶ መንግሥቴ በቺካጎ የኢትዮጵያውያንን ማኅበር የመሰረቱትም ከ36 ዓመታት በፊት ነበር።

በቺካጎ አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋልታ በመሆንና ድጋፍን በመቸር ይታወቁ ነበር የተባሉት አቶ መንግሥቴ፤ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይሉ ከሁሉ ጋር በመቀራረብ አንድነትን፣ ህብረትን በማምጣት በብዙዎች ዘንድ መወደድ የቻሉ ናቸው ተብሏል። በብዙዎችም ዘንድ "ጋሽ መንግሥቴ" ተብለው ይጠሩ እንደነበርም ማኅበሩ አስታውሷል።

አቶ መንግሥቴ አስረሴ ህዳር 9/1930 በጎንደር ከተማ እንደተወለዱና ገና በለጋነት እድሜያቸውም የቤተ-ክርስቲያን ትምህርት ጀምረው ዲያቆንነትም ማገልገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ገብተው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሐረር መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመርቀው በወቅቱ ክፍለ ሃገር በነበረችው ኤርትራ ውስጥ በምፅዋና በአሥመራ አስተምረዋል።

በተለያዩ የመንግሥት የሥራ ድርሻዎች ላይ የነበሩት አቶ መንግሥቴ በአዲስ አበባም በአገር ግዛት ሚኒስቴር በሕዝብ ደህንነት ክፍል ተመድበው ለበርካታ ዓመታት እንዳገለገሉም በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማህበር በፌስቡኩ ላይ ካወጣው የአጭር የህይወት ታሪካቸው መረዳት ይቻላል።

የ1966 የመንግሥት ለውጥንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሕብረትን ተቀላቀሉ። በኢዲዪ የፖለቲካም ሆነ የትግል ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ ነበራቸው የተባሉት አቶ መንግሥቴ በድርጅቱም ውስጥ በአመራርና የኃላፊነተ ቦታም ላይ ነበሩ።

አቶ መንግሥቴ ለመፃህፍት በተለይም ለሼክስፒር ድርሰቶች ለየት ያለ ፍቅር ነበራቸው ይባላል። 'ብላክ ኤንድ ዋይት' የተሰኘውን የሲድኒ ኩክና ጋርትሊን ድርሰትንም ወደ አማርኛ ተርጉመዋል።

ከቀድሞ ጓደኛቸውና ባለቤታቸው ወይዘሮ ጆርጅጋ ግደይ ጋርም ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፤ እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2006 በሞት እስከተለይዋቸውም ድረስ አብረው ኖረዋል።

በስደት በመጡበት አሜሪካ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሊረዳዱበት የሚችሉበትን የማሰባሰብና የማደራጀት ሥራ ጀምረው በጎርጎሳውያኑ 1986 በችካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበርን (Ethiopian Community Association of Chicago) ከመሰረቱት አንዱ ናቸው። እስከሞቱባት ዕለት ድረስም በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች በቦርድ ፕሬዚዳንትነት፣ በአማካሪ ቦርድና በበጎ ፈቃደኝነትም አገልግለዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በቺካጎ በሚገኘው ደብረፅዮን መድኃኔዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንም ውስጥ በዲቁናና የተለያዩ አገልግሎቶችንም ሲሰጡ ነበር።

በፌስቡክ ላይ ሐዘናቸውን የገለፁ የችካጎ ነዋሪዎች ለሰው ችግር ቀድሞ ደራሽ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ አዋቂ፣ ተጫዋች፣ የተጣሉትን አስታራቂ፣ መካሪና አስተባባሪ በማለትም እየዘከሯቸው ይገኛሉ።

አቶ መንግሥቴ በኮሮናቫይረስ በመጠቃታቸው በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ82 ዓመታቸው ሚያዝያ 12/2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የአንዲት ልጅ አባት የነበሩት አቶ መንግሥቴ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ሚያዝያ 19/2012 ዓ.ም ከባለቤታቸው ጎን ተቀብረዋል።

ካፕቴን ዮሴፍ ሲቡ- የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አሰልጣኝ

የላስቬጋስ ከተማ ነዋሪ የነበሩትና በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ በአሰልጣኝነት ያገለገሉት ካፕቴን ዮሴፍ ሲቡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች አንዱ ናቸው።

የ60 ዓመቱ ካፕቴን ዮሴፍ ከፍተኛ ድካም፣ ላብና፣ ሳልም ሲደራረብባቸው ወደ ህክም አምርተው ብሮንካይትስ መሆኑ ተነግሯቸው ነበር። በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ሐኪሞች ውጤቱን ከቀናት በኋላ እንደሚያሳውቋቸው ነግረዋቸው ነበር።

ቤትም ከተመለሱ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ህመሙ አገረሸባቸው፣ መተንፈስም አዳገታቸው፤ የህክምና እርዳታም ተጠርቶ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱም ወደቤታቸው ግን አልተመለሱም በወጡበት ህይወታቸውም ሚያዝያ2/2012 ዓ.ም በዚያው አለፈ። አስከሬናቸውም በሆስፒታል ውስጥ ይገኛል።

ባለቤታቸው ወ/ሮ አበራሽ ኦሮሞም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን በትዳርም ለአስራ ሁለት ዓመታት ቆይተው ሦስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን ሶስቱም ከአስር ዓመት በታች መሆናቸው ተነግሯል።

በስማቸው የተቋቋመው የጎ ፈንድ ሚ ገፅ እንደሚያስረዳው ካፕቴን ዮሴፍ በኢትዮጵያ አየር ኃይል በካፕቴንነት ለዘመናት እንዳገለገሉና በኋላም ላስ ቬጋስ በሚገኘው ቤላጂዮ ሆቴል ለአስራ ሁለት ዓመታት ሰርተዋል።

ካፕቴን ዮሴፍን በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎችም በፃፉት መሰረት የተወለዱት ሲዳማ ውስጥ ቦሪቻ በሚባል አካባቢ ሲሆን ከአየር ኃይል ካፕቴንነታቸው በተጨማሪ በተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከላትም ለዓመታት አሰልጥነዋል።

ካፕቴን ዮሴፍ "የሰብአዊ መብት ተሟጋች፣ የብሔሮችን ጭቆና የሚፀየፉ እንዲሁም የሲዳማንም ሕዝብ በራስ የመተዳደር መብት በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፉ እንደነበርም" ተጽፏል።

በኮሮና ህይወታቸውን ያጡት አቶ ዳዊት ግዛው፣ አቶ ሊሻን ወንዳፍራሽ፣ አቶ ምንውየለት መሐሪና አቶ አሸናፊ ተፈራ

የፎቶው ባለመብት, Tasew Melakehiwot

የምስሉ መግለጫ, በኮሮና ህይወታቸውን ያጡት አቶ ዳዊት ግዛው፣ አቶ ሊሻን ወንዳፍራሽ፣ አቶ ምንውየለት መሐሪና አቶ አሸናፊ ተፈራ

አቶ ዳዊት ግዛው፡ በዋሽንግተን ዲሲ ካሉት የኢትዮጵያውያን ማኅበራት መካከል የአንዱ ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፤ በርካታ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ያበረከቱ በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጤና ኢንሹራንስ እንዲያገኙ ብዙ የለፉ እንደሆኑም ተነግሯል።

አቶ ሊሻን ወንዳፍራሽ፡ የቨርጂኒያ ነዋሪ፣ ባለትዳር፣ በቤተክርስቲያን በርካታ አስተዋፅኦዎችን ያደርግ የነበረ አገልጋይ።

አቶ ምንውየለት መሐሪ፡ የአየር ኃይል ቴክኒሺያን፣ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ ኮሎራዶ በቅርቡ የሄደ፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ሲሆን ቤተሰቦቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ።

አቶ አሸናፊ ተፈራ፡ የሜሪላንድ ነዋሪ፣ ባለትዳርና የአንዲት ህፃን ልጅ አባት፤ ለንደን ቆይቶ ከተመለሰ በኋላ በኮሮናቫይረስ ተይዞ በቀናት ውስጥ ህይወቱ አልፏል።

ምንጭ፦ ዋሽንግተን ፖስት፣ ቪኦኤ አማርኛ፣ የዲሲ ግብረ ኃይል ተወካይ አቶ ጣሰው መላዕከሕይወት፣ በችካጎ የኢትዮጵያውያን ማህበርፌስቡክ፣ ጎፈንድ ሚ ገፆች፣ የተለያዩ ሰዎች የፌስቡክ ገፅ

ኮሮና
Banner