ኮሮናቫይረስ፡ ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት ፊቱን ወደ ህንድ ያዞራል

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፔዮ አገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከህንድ ጋር በመሆን ለኮሮናቫይረስ የሚሆን ክትባት በማዘጋጀት ላይ መሆኗን አሳውቀዋል።

የሰውየው ንግግር ብዙም ያልተጠበቀ አልነበረም።

ህንድና አሜሪካ ለ30 ዓመታት ያክል መድኃኒትና ክትባት በጋራ ሲያመርቱ ከርመዋል። የወባ መድኃኒት፣ ታይፎይድ ክኒን፣ ኢንፍኡዌንዛና የቲቢ በሽታን የሚያክሙ መድኃኒቶችን በጋር አምርተዋል። የወባ ክትባት ለማዘጋጀትም በጋራ እየሠሩ ነው።

ህንድ መድኃኒትና ክትባት በማምረት በዓለማችን ቁንጮ ከሚባሉ አገራት መካከል ናት። የፖሊዮ፣ የማጅራት ገትር፣ የሳንባ ምች፣ የኩፍኝን ጨምሮ የሌሎችም በሽታዎች ክትባቶችን የሚያመርቱ ድርጅቶችም አሏት።

የኮሮናቫይረስ ክትባትን ለማግኘት ደፋ ቀና ከሚሉ ድርጅቶች መካከል ስድስቱ ህንድ ነው የሚገኙት። ከእነዚህም አንዱ ሴረም የተባለው ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ክትባት አምርቶ በመሸጥ በዓለም የሚስተካከለው የለም።

ይህ በሥራው ላእ ከ50 ዓመት በላይ የቆየ ድርጅት በዓመት 1.5 ቢሊዮን መድኃኒቶችና ክትባቶች ያመርታል። ፋብሪካው ህንድ ውስጥ ሁለት ትላልቅ ፋብሪካዎች አሉት። ኔዘርላንድስና ቼክ ሪፐብሊክም ውስጥ ማምረቻዎች ገንብቷል። ድርጅቱ 7 ሺህ ያህል ሠራተኞች እንዳሉት ይነገራል።

ኩባንያው 20 የክትባት ዓይነቶችን ለ165 አገራት ያቀርባል። 80 በመቶ ምርቶቹ በጣም ተመጣጣኝ በሚባል ዋጋ የሚቀርቡ ናቸው።

ኮሮና
Banner

ድርጅቱ አሁን ኮዳጄኒክስ ከሚባል የአሜሪካ ባዮቴክ ኩባንያ ጋር 'ላይቭ አቴንዌትድ' የተሰኘ ክትባት ለማምረት እየጣረ ይገኛል። ክትባቱ የቫይረሱን ጎጂ ባሕሪ መቀነስ ወይም ማስወገድ ነው ሥራው።

''በወርሃ ሚያዚያ መጨረሻ ክትባቱን እንስሳት ላይ ለመሞከር ነው ዕቅዳችን'' ይላሉ የሴረም የህንድ ኃላፊ አዳር ፑናዋላ።

ድርጅቱ ከዚህም አልፎ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ እየሠራው ያለውን ክትባት በገፍ ለማምረት እየተዘጋጀ ነው። ባለፈው ሐሙስ የኦክስፎርድ ተመራማሪዎች ክትባቱን ሰው ላይ መሞከር ጀምረዋል። ሁሉም ነገር እንደውጥናቸው ከሄድ የሳይንቲስቶቹ ዕቅድ መስከረም ላይ አንድ ሚሊዮን ክትባቶች ማምረት ነው።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሰቲው ፕሮፌሰር አድሪያን ሂል ''በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ክትባቶች እንደሚያስፈልጉን እርግጥ ነው። በያዝነው ዓመት መጨረሻ [2020] ይህንን ወረርሽኝ ማስወገድ ነው ዋናው ዓላማው፤ ከዚያም በነፃነት መንቀሳቀስ ነው'' ይላሉ።

የሕንዱ ኩባንያው ሴረም እስከ 500 ሚሊዮን ክትባቶች የማምረት አቅም አለው። ሌላኛው የህንድ ኩባንያ ባሃራት ባዮቴክ የአሜሪካው ዊስኮንሲን ዪነቨርሲቲ የሚሠራውን ክትባት 300 ሚሊዮን አምርቶ ለመላው ዓለም ለማከፋፈል ተዋውሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ለህንድ መድኃኒት ተቋማት ያለውን አድናቆት ለመግለፅ ቃላት የሚያጥረው ይመስላል። መድኃኒት በጥራትና በብዛት ማምረት ከመቻላቸው በላይ ይህንን ወረርሽኝ በማጥፋት ለዓለም በጎ መዋል ይፈልጋሉ ሲል ይገልፃቸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ግን እንዲህ ይላሉ - ክትባት እንዲሁ በቀላሉ አይሠራምና በሁለት በሦስት ወራት ገበያ ላይ ይገኛል ብላችሁ እንዳትጠብቁ።

በዓለም በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን እየተጠጋ ነው። የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ200 ሺህ በላይ ሆኗል። አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ ክትባት አግኝቶ በብዛት ማምረትና ማከፋፈል ቢያንስ አንድ ዓመት ሊወስድ ይችላል። ቢሆንም ክትባት ማግኘታችን አይቀሬ ይመስላል።